Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኢኮኖሚው ብርድ ገብቶት እንዳይሆን!

ከሁለት ዓመታት በፊት በአገሪቱ የተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት አኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በቀላሉ የማይገመት ንብረት ወድሟል፡፡ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎም ለአሥር ወራት የፀናው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢኮኖሚው ውስጥ ያሳደረው ተፅዕኖም ሲገለጽና ሲተነተን እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከዚህ ክስተት ጥቂት እፎይ በተባለበት ወቅት፣ የቀን ገቢ ግምት የፈጠረው መተረማመስም ኢኮኖሚው ላይ ጠባሳ አሳርፏል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴዎችን አጓቷል፡፡ በገበያ ላይ የዋጋ ለውጥና ጫና ስለማሳደሩም አይታበልም፡፡ እንዲህ ካለው አዙሪት ሳንወጣ ከምዝበራ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ባለሀብቶችና የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ የተወሰደውም ዕርምጃም ብዙዎችን አስደንብሮ የፈጠረው ውጥረትም ገበያውን ሳይነካካው አልቀረም፡፡ በሙስና ተጠርጠው የታሠሩ ግለሰቦች የሚመሯቸው ተቋማትና ኩባንያዎች የፈጠሩት መስተጓጎልም ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ ሆኖም አገራዊ ችግር አስከትሏል ማለት አይቻልም፡፡ ሙሰኞችን መቀጣት ተገቢ ቢሆንም፣ ዕርምጃው ግን ዋጋ አስከፍሏል፡፡

በቅርቡ የተደረገው የምንዛሪ ለውጥም ገበያው ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮ ያስከተለው መደነባበርም በጉልህ የሚታይ ጫና ፈጥሯል፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን መንግሥት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገቱን እንዳላቆመ እያስታወቀ ነው፡፡ እንደውም በምንዛሪ ለውጡ ሳቢያ የወጪ ንግዱ ሲነቃቃ መታየቱን፣ የቡና ወጪ ንግድና መሰሎቹ ላይ ጭማሪ መታየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሲናገሩ አድምጠናል፡፡

እንዲህ ያሉ ፈተናዎች የተደራረቡበት የግብይት ሥርዓት፣ የተጋረጡበትን ጫናዎች ሁሉ ተቋቁሞ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ አልተፈጠረም የሚለውን አገላለጽ ለመቀበል ቢከብድም፣ እውነት ኢኮኖሚው በመንግሥት እንደሚባልለት እንደወትሮው እየተጓዘ ከሆነ መልካም ነው፡፡

ነገር ግን ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፉ የሚችሉ ተጨባጭ ጉዳዮች እየታዩ ነው፡፡ የምንዛሪ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች ውስጥ አንዳንዶቹ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳርፉት ተፅዕኖ ሥጋት እየፈጠረ ለመሆኑ ምሳሌው ባንኮች እንቀደመው ጊዜ እያበደሩ አለመሆናቸው ነው፡፡ በርካታ ተበዳሪዎች የተፈቀደላቸውን ብድር ማግኘት እንዳልቻሉ እየሰማን ነው፡፡ በመንግሥት ውሳኔ አንዳንድ የቢዝነስ ዘርፎች የብድር መያዣ የተቀመጠላቸው በመሆኑ፣ ባንኮች ይህንን ጣሪያ ላለማለፍ የሚሰጡትን ብድር ለመገደብ እየተገደዱ ነው፡፡  

እርግጥ ከምንዛሪ ለውጡ ጋር ተያይዞ ባንኮች የብድር አሰጣጣቸው ላይ ገደብ እንደተደረገበት ቢታወቅም፣ ብድር እንደሚሰጣቸው ተማምነው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን ተበዳሪዎች ሥራ እያስተጓጎለ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ቀስ በቀስ የሚታይ ተፅዕኖ ማሳረፉ እንደማይቀር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

የምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ በዋናነት ታሳቢ የተደረገው የወጪ ንግድ ለማበረታት ገቢ ንግድን ለማቀዛቀዝ ወይም በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ጭምር ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር ኢኮኖሚው እንደሚባለው ጤነኛ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳው ጉዳይ፣ ለወትሮው በወር ሦስትና አራት የመንገድ ግንባታ ስምምነቶች ሲደረጉ የነበረበት ወቅት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ ሲደረግ አለመታየቱ ነው፡፡ አንድም የመንገድ ግንባታ ስምምነት ሳይፈረም የበጀት ዓመቱ አጋማሽ እየተቃረበ መሆኑንስ ኢኮኖሚያው ተፅዕኖ ውስጥ አይደለም ወይ ያስብላል፡፡ ለመንገዶች የተመደበውን በጀት ሰምተናል፡፡ ለ50 ቢሊዮን ብር ፈሪ የሆነ ገንዘብ በግምጃ ቤቱ በኩል ይፋ ሲደረግ ታዝበናል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አጽድቆታል፡፡ ግን በዚህ ዓመት አዲስ የግንባታ ስምምንት  ለምን አልተፈረመም የሚለው ጉዳይ ብዙ መላምታዊ ምክንያት ያስነሳል፡፡ መንግሥት ያጸደቀውን ያህል በጀት የሚመጣጠን ገቢ እያገኘ አለመሆኑን ሰምተናል፡፡ ለዚህ ዓመት ከተያዘው በጀት ውስጥ በዕርዳታና ብድር የሚመጣው ገንዘብ ጠቀም ያለ መጠን ቢኖረውም፣ ለበጀቱ የሚመጣጠን ገንዘብ ስለመገኘቱ እየሰማን አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ከሚያሟሙቁ ዘርፎች መካከል ግንባታ አንዱ እንደመሆኑ መጠን፣ በተለይ የመንገድ ግንባታ ኮንትራቶች አለመታየታቸው፣ ከግንባታ ስምምነቶች ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል መቀዛቀዙ በራሱ ኢኮኖሚውን ብርድ ብርድ የሚያሰኘው አይደለምን? እንዲህ ያሉ ገዳዮች በዚሁ ከቀጠሉ ከሚገመተውም ይልቅ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግር መኖሩን ሊጠቁሙ ይችላሉና መንግሥት በተገቢው መንገድ መረጃ ይስጥ፡፡ ኢኮኖሚውም ጤንነት ላይ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስችል ትንታኔ ያስደምጠን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት