Wednesday, April 17, 2024

የህዳሴ ግድቡና የአገሪቱ ሚዲያዎች ሚና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እዮብ ማሞ ተወልዶ ያደገው በምዕራብ ጎጃም ሰከላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከዓባይ ምንጭ ጠጥቶ እንዳደገም ይገልጻል፡፡ በልጅነቱ ‹‹ዓባይ ዓባይ የአገር ለምለም የአገር ሲሳይ›› የሚለውን መዝሙር ሲዘምር እንዳደገም ያስታውሳል፡፡ የዓባይ ወንዝ ለዘመናት አገሩን ጥሎ ሲሄድ ስለነበር እንደሚያሳስበው አሁንም በቁጭት ይናገራል፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2003 .. የዓባይን ወንዝ በመገደብኢትዮጵያ ኃይል ኤሌክትሪክ ልታመነጭ መሆኗን ሲሰማ እንደተደሰተም ያስታውሳል፡፡ የህዳሴ ግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለ ወዲህ የግብፅ አቋም አሁንም ድረስ የሚያስገርም መሆኑን ያስረዳል፡፡ የህዳሴ ግድቡ የአካባቢያዊ ተፅዕኖና የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ በተመለከተ ሦስቱ አገሮች ገና ድርድር እያደረጉ ባሉበት ወቅት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ‹‹ናይል የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው›› የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ይኮንናል፡፡ ባለፈው ሳምንት በግብፅ ሚዲያዎች እየተሠራጩ ያሉት መረጃዎች በመሉ በቀላሉ የሚታዩ እንዳልሆኑ ያስረዳል፡፡ እዮብ በአሁኑ ወቅት በአንድ የመንግሥት ሚዲያ ውስጥ ተቀጥሮ በጋዜጠኝነት እየሠራ ይገኛል፡፡ የህዳሴ ግድቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ሐሙስ ኅዳር 14 ቀን 2010 .. በነበረው ውይይት ላይ እሱም ተካፋይ ነበር፡፡

የግብፅ ሚዲዎች ፕሬዚዳንት አልሲሲን መግለጫ በመከተል የተለያዩ ዘገባዎችን እያወጡ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ለሴኮንድ እንደማታቋርጥ በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል፡፡ ሐሙስ ኅዳር 14 ቀን 2010 .ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ እንደማትጠብቅ ገልጸዋል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ረሃብን ለማጥፋት የምታከናውነው ሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ በመሆኑ ግድቡ የህልውና ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በግብፅና በሌሎች መሰል አገሮች የህዳሴ ግድቡ እንዲቆም ግፊት እየተደረገ መሆኑን ሲገለጽ ቢሰማም፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በጉባ ወረዳ 24 ሰዓት ሙሉ ሥራ እንዳለማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ እየተናገረ ነው፡፡

የህዳሴ ግድቡ ዕውን እንዲሆንና የአገሪቱ ሕዝብ ተሳትፎውን የበለጠ እንዲያጠናክር፣ ብሎም የግብፅ ሚዲያዎች የሚያስተላልፉትን መረጃ ለመመከት ያስችል ዘንድ ሐሙስ ኅዳር 14 ቀን 2010 .ም. በፋና ብሮድካስቲንግ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የግማሽ ቀን ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ ውይይቱን ያዘጋጀው የህዳሴ ግድቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ የሚዲያ ኃላፊዎች፣ ጋዜጠኞችና የማስታውቂያ ባለሙያዎች ተገኝተው ነበር፡፡

የውይይቱ ዋና ዓላማ በአገሪቱ የሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች ስለህዳሴ ግድቡ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ከማግኘት ባሻገር ጥልቀት ያላቸው ዘገባዎችን፣ ትንታኔዎችንና ፕሮግራሞችን በተሟላ ሁኔታ እንዲያቀርቡ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የህዳሴ ግድቡ መጋቢት 24 ቀን 2003 .ም. የመሠረት ድንጋይ ከተጣለ ወዲህ፣ የኢትዮጵያ ሚዲያዎችና የማስታወቂያ ባለሙያዎች ከፍተኛ የሆነ ሚና እንደነበራቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡ የግድቡ የመሠረት ድንጋይ በተጣለ ማግሥት በአገሪቱ በአራቱም አቅጣጫዎች ያሉ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ሰፊ ሥራ ሲያከናውኑ እንደቆዩና አሁንም ድረስ እየሠሩ መሆናቸው ተወስቷል፡፡

ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ንብረት መሆኑን ለማሳየት ሰፊ የዘገባ ሽፋን በመስጠት ሚዲያው የተጫወተው ሚና አበረታች እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ግድቡ የኔ ቅርስ ነው በሚል እሳቤ እንዲኖረው ከማድረግ አኳያ፣ ሚዲያው ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የሚሠሩ ዜናዎች፣ ትንታኔዎችና ዘገባዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመቀዛቀዝ ስሜት እየታየባቸው እንደመጣም ተጠቁሟል፡፡ ጥልቅ ትንታኔ ከመሥራት አኳያ፣ በራስ ተነሳሽነት ከመዘገብና ኅብረተሰቡ ከዚህ በፊት የነበረውን ስሜት ይዞ እንዲቀጥል ከመቀስቀስና ከማስተማር አኳያ ከፍተቶች እየታዩ እንደመጡ ተብራርቷል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ የኮሙዩኒኬሽንና የሕዝብ ግንኑነት ዳይሬክተር /ሮ ፍቅርተ ታምር ውይይቱን ሲከፍቱ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ሚዲያ በተለይም የህዳሴ ግድቡን ለማቀዝቀዝ እየተሠራጩ ያሉ መረጃዎችን በመመከት ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ‹‹ግድቡ ከኃይል ማመንጫነት ባሻገር አገሪቱ ጎልታ እንድትወጣ ከማድረግ አኳያ ሚዲያ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤›› ብለዋል፡፡ ይኼም ቢሆን ግን ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለኅብረተሰቡ ለማድረስ ግን ከፍተቶች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አየነው አዲስ፣ ‹‹የአገራችን መገናኛ ብዙኃን በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚሠራቸው ዘገባዎችና ያጋጣሟቸው ተግዳሮቶች›› በሚል ርዕስ አጭር የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል፡፡ አቶ አየነው እንደገለጹት፣ የዳሰሳ ጥናቱን ያዘጋጁት ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ሚዲያዎች አምስት ተመሳሳይ ጥያቄዎችን በማቅረብና እነሱ በሰጡት ምላሻ ላይ ተመርኩዘው ነው፡፡

አቶ አየነው ለሚዲያዎች ያቀረቧቸውን ጥያቄዎችንም በመድረኩ ላይ አንስተዋል፡፡ የመጀመርያው ጥያቄ የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች በመረጃ የተደገፉና ጥልቀት ኖሯቸው የሚዘጋጁ ናቸው ብለው ያስባሉ? ካልሆነ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል? የሚል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ካገኟቸው ምላሾች መካከልም ሚዲያዎች ለህዳሴ ግድቡ የሚሰጡትን ሽፋን በመረጃ የተደገፈና ጥልቅ ትንታኔ ያለው እንዳልሆነ፣ የሚተላለፉ ዘገባዎችም ቢሆኑ በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ንግግሮችና አስተያየቶች ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ፣ አንዳንዶች በመረጃ ተደግፈዋል ቢባልም ዘገባዎች የተሟሉ፣ ሳቢና ጥልቀት የሌላቸው እንደሆኑ፣ ጥልቀትና ሳቢ ዘገባ ለመሥራት በጋዜጠኞች ላይ የአቅም ክፍተቶች እንዳሉ፣ ለጉዳዩ ትኩረት እንደማይሰጠውና የተነሳሽነትና የእኔነት ስሜት አለመኖር የሚሉት እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡ እንደ ምክንያት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከልም የመገናኛ ብዙኃን በአብዛኛው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተመሥርተው የሚሠሩ መሆናቸው፣ ዘገባዎች በጥናት ላይ ተመርኩዘው የሚሠሩ አለመሆናቸውን በዳሰሳ ጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ሁለተኛው ጥያቄ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደ ግብፅ አቻዎቻቸውና ተቋማት በህዳሴው ግድብና ከግድቡ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በባለሙያ የታገዙ ዜናዎችን፣ ትንታኔዎችንና ፕሮግራሞችን ከማቅረብ አንፃር ያሉባቸው ክፍተቶች ምንድናቸው? ዋና ዋና ችግሮች ተብለው የሚጠቀሱ ጉዳዮች ካሉ ቢጠቅሱ? የሚል  እንደሆነ አስታውሰው፣ ለዚህ ጥያቄ ከተሰጡ ምላሾች መካከል በህዳሴው ግድብና ከግድቡ ጋር የተያያዘ ምርምር የሚያደርጉ ምሁራን በስፋት አለመኖር፣ ያሉት ጥቂት ሚዲያዎችም ቢሆኑ የተደራጀ የመረጃ ቋት የሌላቸው መሆኑ፣ ባለሙያዎችን አግኝቶና አወያይቶ ጥልቅና ተደማጭ ዘገባዎችን ለመሥራትቢሮክራሲ ውጣ ውረድ የበዛበትና አድካሚ መሆኑ፣ በዘርፉ ማብራርያዎችንና ንታኔዎችን የሚሰጡ ባለሙያዎች ከሚዲያው ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ አለመሆናቸው፣ አንዳንዶች ኃላፊነትን በመፍራትና ከመሸሽ አኳያ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ አለመስጠት፣ የመገናኛ ብዙኃኑ የራሳቸው የሆነና የተደራጀ የህዳሴ ግድቡ የመረጃ ቋት እንደሌላቸው፣ ሚዲያዎች አንድ ዓይነት መግባባት ፈጥረው በአንድ አጀንዳ ላይ ከመሥራት አኳያ ሰፊ ክፍተት ያለ መሆኑና የአገሪቱ ሚዲያ ዕድሜው ገና ከመሆኑ አኳያ በአቅም ውስንነት ያለበት መሆኑ፣ የግድቡ የግንባታ ጊዜ በተራዘመ ቁጥር በአንዳንድ ሚዲያዎች የመሰላቸት  አዝማሚያ መታየቱ ተጠቃሾች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ሦስተኛው ጥያቄ የመገናኛ ብዙኃን በህዳሴው ግድብ ላይ እስካሁን የሠሯቸው ሥራዎች ለኅብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ሰጥተዋል ብለው ያምናሉ? እንዴት? የሚል እንደሆነና በተሰጠው ምላሽም ጠቅለል ባለ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ የሰጡ እንዳልሆኑና ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኅብረተሰቡን እውቀትና ግንዛቤ ከግምት ውስጥ ያስገቡ አለመሆናቸው፣ መገናኛ ብዙኃን ሁነት እየጠበቁ የሚያደርሱት መረጃ የሚፈጥረው መጠነኛ መነቃቃት ቢኖርም፣ ቀጣይነት ኖሮት ከጊዜ ወደጊዜ የሚሄድና በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት በሚፈጥር መንገድ እየተሠራ አለመሆኑን አውስተዋል፡፡

አራተኛው ጥያቄ በህዳሴ ግድቡ ላይ ከግብፅና ከሌሎችም የመገናኛ ብዙኃን የሚሠራጩ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በበቂ ማብራርያና ትንታኔ ከመመከአንፃር የአገሪቱን መገናኛ ብዙኃን ምን ያህል ሠርቷል? የሚል እንደሆነ ጠቁመው፣ ከተሰጡ ምላሾች መካከልም ዘገባዎች በቂና ተከታታይነት ያላቸው ባይሆኑም አፍራሽ አመለካከቶችን በማጋለጥ ረገድ የሚዲያ ተቋማት ገንቢ ሚና እንደተጫወቱ ገልጸዋል፡፡

የግብፅ ሚዲያዎች የሚያቀርቧቸውን ዘገባዎች መነሻ በማድረግም የአገሪቱ ሚዲያዎች የግድቡን ትክክለኛ መረጃ ለአገር ውስጥና ለውጭ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ጥረት አድርገዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በየጊዜው የግብፅ ሚዲያዎች የሚያስተላልፉትን እየከታተሉ የሚያከሽፍ ሥራዎችን በመሥራት ረገድ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉም፣ በዳሰሳ ጥናቱ ማረጋገጥ እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡ ግብፆች በሚሠሩበት የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ደረጃ መጠን መሥራት እንዳልተቻለም ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

አምስተኛውና የመጨረሻው ጥያቄ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ሁነቶችን ጠብቆ ከመሥራት ባሻገር ቀጣይነትና ተከታታይነት ያላቸው  ዘገባዎችን የማይሠሩበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? የሚል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የዳሰሳ ጥናት የተሠራባቸው የግልም ሆኑ የመንግሥት ሚዲያዎች ከሰጧቸው ምላሾች መካከል የክህሎት ችግር መኖር፣ የጋዜጠኞች ፍልሰት፣ የጋዜጠኞች እጥረት፣ የመረጃ ምንጮች በሚፈልገው ጊዜና ወቅት አለመገኘት፣ ኃላፊዎች በተለያዩ ምክንያቶች መረጃ አለመስጠት፣ የተነሳሽነት ችግር መኖርና የመፈጸም አቅም ጉድለት የሚሉ እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ ለተሳታፊዎች ከቀረበ በኋላ ለአስተያየትና ጥያቄ መድረኩ ክፍት ሆኗል፡፡ በዚህም መሠረት ከተለያዩ ሚዲያዎች የመጡ ኃላፊዎችና ጋዜጠኞች ጥያቄና አስተያየት አቅርበዋል፡፡

የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅትአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰጠኝ እንግዳ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ዜናዎችን ለመዘገብ በአገሪቱ ውስጥ ያለው መረጃ የማግኘት ቢሮክራሲ በቀላሉ የሚገለጽ እንዳልሆነ አውስተዋል፡፡ በዚህም ሚዲያዎች ለሚሠሩት ዘገባና ፕሮግራም በተለይም የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ፈታኝ ሁኔታ አለ ብለዋል፡፡ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መረጃ ለማግኘት ጥያቄ በሚቀርብበት ወቀትም የመሸሽ ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ስለህዳሴ ግድቡ መረጃ ለማግኘት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየ15 ቀናት የሚሰጠውን መግለጫ መጠበቅ ግድ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከግብፅ የሚሰነዘሩ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመመከት እንዲረዳ ኃላፊነት ወስዶ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ ጉዳዩ ፈታኝ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የመጡት ባለሙያም አገር አቀፍ የመረጃ ቋት ባለመኖሩ በሚዲያዎች በኩል ችግር እየተፈጠረ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ይኼንን ለማስተካከልም የህዳሴ ግድቡ የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የራሱ የሆነ የመረጃ ቋት ቢኖረው፣ ለሚዲያዎችም ሆነ የህዳሴ ግድቡን ለታሪክ ለማስተላለፍ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የመጡት ተወካይ በበኩላቸው፣ የግብፅ ሚዲያዎች በዓባይ ወንዝ ላይ የሞት ሽረት ብለው የሚሠሩትን ያህል የኢትዮጵያ ሚዲያዎች እየሠሩ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሠራ ባለመሆኑ የህዳሴ ግድቡ ቆሟል ተብሎ ከሁለት ሳምንታት በፊት ይናፈስ የነበረውን የተሳሳተ መረጃ መሆኑን የገለጸ የመንግሥት ተቋም እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡ ሚዲያዎች እርስ በራሳቸውየተናበበ ከመሥራት አኳያም ሰፊ ክፍተቶች እንደነበሩባቸው አንስተዋል፡፡ ባለሥልጣን የተናገረውን ብቻ ከማስተጋባት ቦታው ድረስ በመሄድ ጥልቅ ትንታኔ ያለው ሥራ መሥራት እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡

በእነዚህና ሌሎች አስተያየት መሰል ጥያቄዎች የህዳሴ ግድቡ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የዳሰሳ ጥናቱን ያቀረቡት አቶ አየነው ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በሕዝቡ ዘንድ መቀዛቀዝ ታይቷል ለተባለው ሲመልሱ፣ ይኼን መቀዛቀዝም ሆነ መነሳሳት የሚፈጥረው ሚዲያው ስለሆነ በእኔነት ስሜት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ ኃላፊነቱን ወስዶ መረጃ የሚሰጥ አካል የለም የተባለው ትክክል እንደሆነ ጠቅሰውከዚህ ውይይት በኋላ ጥያቄው ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ ምላሽ እንደሚሰጥበት ተናግረዋል፡፡ በህዳሴ ግድቡ ላይ እየተሠሩ ያሉ ፕሮግራሞች ወጣ ገባነት የሚታይባቸው በመሆኑ ጉዳዩን ማስተካከል ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ግድቡ ቆሟል የሚሉና ሌሎች አሉባልታዎች እንዳሉ ጠቁመው፣ ነገር ግን ይኼን ወደ ጎን በማለት ዋናው ሥራ ላይ ማተኮር ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

/ሮ ፍቅርተ በበኩላቸው መረጃ የሚሰጥ አካል የለም ለተባለው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹ሥራ አስፈጻሚው ዘጠኝ ሚኒስትሮችን ያካተተ ነው፡፡ ስለዚህ መረጃ ማግኘት የሚቻለው ከእነዚህ ኃላፊዎች ብቻ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

 ነገር ግን ኃላፊዎቹ በሥራ መደራረብና መብዛት የተነሳ እንደተባለው በቀላሉና በተፈለገው ጊዜ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ይኼንን ጉዳይ ጽሕፈት ቤቱ ከሚመለከታቸው ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ጋር በመሆን ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

የሕዝብ ድጋፍ እየተቀዛቀዘ መጥቷል የተባለውም የተሳሳተ እንደሆነ ጠቁመው፣ መረጃው ይኼን እንደማያሳይና የሕዝቡ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ ሥራዎችን በዕቅድ ይዞ የመሥራት ክፍተት እንዳለ ጠቁመው፣ ይኼንን ለማሻሻል ጽሕፈት ቤቱ የተለያዩ ዕቅዶችን በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመረጃ ቋት መኖር አለበት ለተባለው ጥያቄም ጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስፈጻሚውን ጠይቆ ተጨማሪ በጀት እንዳገኝና የመረጃ ቋት ግንባታው እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወደፊትም አንድ አገር አቀፍ የመረጃ ቋት ንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታገል ቀኑብህ የተሰጡትን አስተያየቶች እንደሚቀበሉና መታረም ያለባቸውን ለማረም ጽሕፈት ቤቱ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም የሚዲያ ባለሙያዎችን ወደፊት ከዚህ የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ ተከታታይ ሥልጠና መስጠት ተገቢ እንደሆነ2 ጽሕፈት ቤታቸውም ይኼን ጉዳይ የቤት ሥራው አድርጎ በመውስድ የሚዲያ ባለሙያዎችን ተከታታይነት ያለው ሥልጠና በመስጠት፣ በእውቀትና በክህሎት የተሻሉና የታጠቁ እንዲሆኑ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -