የኤርትራ መንግሥትን በአፋኝነትና በጨቋኝነት በተደጋጋሚ ሲወነጅል የቆየው አውሮፓ ኅብረት ለቀጣዩ አምስት ዓመታት (እ.ኤ.አ. እስከ 2020) ድረስ የ312 ሚሊዮን ዩሮ ዕርዳታ ለኤርትራ ለመስጠት ወሰነ፡፡ የመብት ተሟጋቾች ውሳኔውን በፅኑ ተቃውመዋል፡፡
በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በፕሬስ ነፃነት አፋኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወገዘው የኤርትራ መንግሥት፣ ከአውሮፓ ኅብረት የሚያገኘው ይኼው ላቅ ያለ ዕርዳታ ከዚህ በፊት እ.ኤ.አ. በ2009 ለአምስት ዓመት ከተሰጠው በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡
የአውሮፓ ኅብረት የኤርትራ መንግሥትን ዴሞክራሲያዊ ማሻሻያ እንዲያደርግ አጥብቀው ሲያሳስቡ ከነበሩት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል ሲሆን፣ ይህንን ያህል ዕርዳታ ለኤርትራ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመስጠት መወሰኑ ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረበት ነው፡፡
ኅብረቱ ይህንን ውሳኔ ከመስጠቱ ቀደም ብሎ የጣሊያን ከፍተኛ ልዑክ ባለፈው ወር ኤርትራን በመጎብኘት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን፣ የፖለቲካ ከፍተኛ አማካሪያቸው አቶ የማነ ገብረአብንና ሌሎች በርካታ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ያነጋገረ ሲሆን፣ መንግሥት በሚቀጥሉት ሦስትና አምስት ዓመታት ‹‹በራሱ መንገድ›› ዴሞክራሲያዊ ማሻሻያ ለማድረግ ቃል እንደተገባለት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ቀደም ሲል ተመሳሳይ ቃል የገባው የኤርትራ መንግሥት የሕዝቡን ነፃነት ሙሉ በሙሉ በማፈን፣ ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን በማሰር በዓለም ቀዳሚ ከሆኑ አገሮች መካከል የሚጠቀስና አንድ አራተኛ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ከአገር መሰደዱ ይነገራል፡፡
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማኅበር ውሳኔውን አጥብቀው ከተቃወሙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ዋነኛው ሲሆን፣ የማኅበሩ የአፍሪካ ዴስክ ኃላፊ ክሊ ካህን ስሪበር፣ ‹‹አውሮፓ ኅብረት ለዚሁ ፈላጭ ቆራጭ የሆነ መንግሥት ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ይህን ያህል ዕርዳታ መስጠቱ አስገርሞኛል፤›› ብለዋል፡፡
ኃላፊው በማከልም፣ ‹‹ምርጫ እንኳን አይታ የማታውቅ ይህቺ አገር በአንድ ሰው እጅ ላይ ወድቃለች፡፡ ለሕግ የበላይነትና ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች መጠበቅ እንደቆመ የሚናገረው አውሮፓ ኅብረት ይህንን ሥርዓት እንዴት ሊደገፍ ቻለ?›› በማለት ኅብረቱ ላይ ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡
የኤርትራ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2001 የግል ሚዲያ ተቋማትን በመዝጋት፣ ለእስር የዳረጋቸው አሥራ አንድ ጋዜጠኞች በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛትም ሆነ በቆዳ ስፋት ትንሿ የሆነችው ኤርትራ፣ በአኅጉሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞችን በማሰር ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት፡፡
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማኅበር ባለፈው ዓመት ባወጣው ‹‹የፕሬስ ነፃነት ኢንዴክስ›› ኤርትራን ለስምንተኛ ጊዜ የመጨረሻዋ አገር አድርጎአት ነበር፡፡