Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የታክሲ ባለንብረቶች የከተማ አውቶቡሶች እንዲገዙ ሊገደዱ መሆኑ ተጠቆመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ታክሲዎች በከተማ ውስጥ አገልግሎት ላይሰጡ ይችላሉ ተብሏል

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ከዘጠኝ ሺሕ በላይ የሚሆኑ የታክሲ ባለንብረቶች፣ በአክሲዮን ማኅበር ተደራጅተው የከተማ አውቶቡሶች ገዝተው እንዲያሰማሩ ሊገደዱ መሆኑን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

መንግሥት በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በኩል ባደረገው ጥናትና በትራንስፖርት ሚኒስቴር በተረጋገጠው መሠረት፣ የአዲስ አበባን ትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ከ500 በላይ አውቶቡሶች እንደሚያስፈልጉ ስምምነት ላይ መደረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመንግሥት ውሳኔ መሠረት ባለሥልጣኑ ያደረገውን ጥናትና በሚኒስቴሩ የተረጋገጠው የአውቶቡሶቹን አስፈላጊነት በሚመለከት፣ ከታክሲ ባለንብረቶች ጋር ሚያዝያ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ተደርጓል፡፡

የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ባለሥልጣን ኃላፊዎች በተገኙበት በተደረገው ውይይት ላይ፣ ‹‹እናንተ ቀደም ብላችሁ ከቀረጥ ነፃ የምናስገባበት ዕድል ይሰጠን በማለት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ስታቀርቡት የነበረውን ጥያቄ፣ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶና ጥናት አድርጐ አስፈላጊነቱ ስለታመነበት ለመወያየት ጠርተናችኋል፤›› በማለት ውይይቱ መጀመሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ መንግሥት የአዲስ አበባን ትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍና ዘመናዊ የትራንስፖርት ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ 500 አውቶቡሶችን ያለ ቀረጥ ለማስገባት መወሰኑን እንደነገራቸውም ታውቋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ 13 የሚሆኑ የታክሲ ባለንብረቶች ማኅበራት እንዳሉ ተገልጾ፣ በየማኅበሩ ውስጥ ያሉ ባለንብረቶች በአክሲዮን ተደራጅተው ከ50 እስከ 100 አውቶብሶችን መግዛት እንዳለባቸው ወይም እንደሚችሉ መገለጹን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በእያንዳንዱ የታክሲ ማኅበር ውስጥ ከ500 እስከ 600 የሚደርሱ ባለንብረቶች መኖራቸውን የገለጹት ምንጮች፣ አቅም ካላቸው ሁሉም፣ አቅም ከሌላቸው ደግሞ ባለንብረቶቹ ከፍተኛ አክሲዮን በመግዛት አውቶቡሶችን መግዛት ግዴታ እንዳለባቸው መነገሩን ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡና ቅድሚያ ክፍያ 30 በመቶ ከፍለው 70 በመቶውን ከባንክ ብድር ማመቻቸቱም ታውቋል፡፡ አውቶቡሶቹ 30 ወንበሮች ያላቸውና ራሳቸው ባለንብረቶቹ ከፈለጉበት አገር መርጠውና ተከራክረው እንደሚገዙም ተገልጿል፡፡

የተወሰኑ የታክሲ ባለንብረቶች መንግሥት ጥሩ ዕድል እንደሰጣቸውና ሲፈልጉት የነበረው ተግባራዊ መሆኑ እንዳስደሰታቸው የተናገሩ ቢሆንም፣ የተቀሩት ግን ደስተኛ አይደሉም፡፡ ምክንያታቸውም የታክሲ ባለንብረቶች በዋናነት እንዲደራጁ የተፈለገው፣ አሁን የሚሠሩባቸውን ታክሲዎች በማስወገድ በአውቶቡሶች ብቻ አገልግሎት እንዲስጥ በመፈለጉ ነው ይላሉ፡፡ አቅም ኖሯቸው በአክሲዮን ማኅበር መደራጀት ካልቻሉም፣ በቀን ሠርተው ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት ነገር እንዳያጡ ሥጋት እንደገባቸው ታውቋል፡፡

በመሆኑም በተለይ ሁሉንም ያማከለ ወይም አቅም የሌላቸው ጐን ለጐን የሚሠሩበት አሠራር እንዲፈጠር የሚመለከተውን አካል ለማነጋገር እያሰቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጥናት አጥንቶና በበላይ አካላት አፀድቆ ወደ ትግበራ ለመግባት ከባለንብረቶቹ ጋር የመጀመርያውን ውይይት ያደረገው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣንን ለማነጋገር በተደረገው ጥረት፣ ለሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰሞኑን እንደሚሰጥ በመግለጽ ሪፖርተር ላነሳቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች