Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያውያንን ከሊቢያ ለማስወጣት የመንግሥት የልዑካን ቡድን ወደዚያ ያመራል

ኢትዮጵያውያንን ከሊቢያ ለማስወጣት የመንግሥት የልዑካን ቡድን ወደዚያ ያመራል

ቀን:

‹‹37 ኢትዮጵያውያን እስረኞች ወደ ተሻለ ማቆያ እንዲዛወሩ ተደርጓል›› ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

አይኤስ የተባለው አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያውያን ላይ ሊቢያ ውስጥ የግፍ ግድያ ከፈጸመ በኋላ፣ በአካባቢው በጭንቅ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለመታደግ መንግሥት ከሱዳንና ከግብፅ መንግሥታት ጋር ተባብሮ እየሠራ መሆኑን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አስታወቁ፡፡

በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማስወጣት መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ዶ/ር ቴድሮስ፣ የአገሪቱ መንግሥትና አማፅያን ከተቆጣጠሩዋቸው ግዛቶች ኢትዮጵያውያንን በሰላም ለማስወጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን፣ ከግብፅና ከሱዳን መንግሥታት ጋርም በትብብር እየተሠራ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡

ሊቢያ በአሁኑ ወቅት በመንግሥትና በአማፅያን ቁጥጥር ሥር የምትገኝ በመሆኗ፣ ከሁለቱም ወገኖች ጋር ቅርበት ባላቸው አጎራባች መንግሥታት አማካይነት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በሰላም ለማስወጣት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለውና መቀመጫውን ቶብሩክ ያደረገውን የአገሪቱን መንግሥት ቅርበት ባለው የሱዳን መንግሥት አማካይነት ለማነጋገር እየተሞከረ እንደሆነ፣ በተቃራኒው ቤንጋዚና አካባቢውን የተቆጣጠረውን አማፂ ቡድን ደግሞ በግብፅ አማካይነት ለማደራደር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዶ/ር ቴድሮስ አመልክተዋል፡፡

ቤንጋዚ አካባቢ በሚገኘው ከይፊያ በተባለው ሥፍራ በአሰቃቂ ሁኔታ ታስረው የነበሩ 37 ኢትዮጵያውያንን በማስፈታት ወደ ተሻለ ሥፍራ እንዲዛወሩ መደረጉን፣ ዶ/ር ቴድሮስ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ከፍተኛ ዲፕሎማቶችን ያካተተ የልዑካን ቡድን ከሚያዝያ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ከግብፅ መንግሥት ጋር በመተባበር ወደ ሊቢያ እንደሚያቀናም አክለው ተናግረዋል፡፡ በሊቢያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጋር ቀጥታ የስልክ ግንኙነት ማድረግ መቻሉን ያስታወቁት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ከሁለቱም መንግሥታት በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ከፍተኛ ትብብር እያደረጉ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ለጥረቱ ስኬት ሲባል ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት የተቆጠቡት ሚኒስትሩ፣ መንግሥት በጭንቅ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ወገኖችን ለመታደግ የተቻለውን በሙሉ እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሊቢያ ውስጥ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን እንዳሉ በውል የማይታወቅ ሲሆን፣ በአገሪቱ የተፈጠረው ትርምስና ግጭት ለመረጃዎች ፍሰት አስቸጋሪ እንደሆነ ይነገራል፡፡

አካባቢውን በቅርበት በመከታተል ላይ እንደሆኑ የተነገረላቸው በግብፅ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር መሐመድ ድሪር በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት አደገኛ ወደሆኑትና ብጥብጥ ወደሚበዛባቸው ሊቢያ፣ የመንና ደቡብ አፍሪካ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...