ኔፓል በ7.8 ሬክተር ስኬል በሚለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ከተመታች ቀናት ተቆጠረ፡፡ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ የመሬት መንቀጥቀጡ ስለመረጋጋቱ የተሰጠ መግለጫ የለም፡፡ ከ4,400 በላይ ሰዎች መሞታቸው ሲገለጽ፣ 8,000 ያህል ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡
ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር አንድ አራተኛ ያህሉ ማለትም ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ የችግሩ ተጠቂ ሆኗል፡፡ የሞቱት ቁጥርም አሥር ሺሕ ሊደርስ እንደሚችል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱሽል ኮይራላ አስታውቀዋል፡፡
የቱሪስት መስህብ ናት የምትባለው ኔፓል፣ አብዛኞቹ አካባቢዎቿ እንዳልነበሩ ሆነዋል፡፡ ሕንፃዎች ተደረማምሰዋል፡፡ ጐርካ በተባለው ወረዳ ብቻ 90 በመቶ ያህል ቤቶች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጡ በገጠራማው የአገሪቱ ክፍሎች ብሷል፡፡
በ39 የአገሪቱ ወረዳዎች የሚኖሩ ስምንት ሚሊዮን ዜጐች ለችግሩ ሲጋለጡ ከእነዚህ ውስጥ በ11 ወረዳዎች የሚኖሩ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ የኔፓል ዋና ከተማ ካታማንዱ ከርዕደ መሬቱ ከተመቱ ከተሞች አንዷም ናት፡፡
በገጠራማ ወረዳዎች የሚኖሩ አዛውንት፣ ወንድና ሴቶች እንዲሁም ሕፃናት የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ኔፓላውያኑም ከዛሬ ነገ ምድር ትውጠናለች በሚል ሥጋት ውሎና አዳራቸውን ከመንቀጥቀጡ ከተራረፉ ቤቶች ውጭና ገላጣማ ሥፍራ ላይ ካደረጉ ቀናትን አስቆጥረዋል፡፡
ያልተረጋጋውን ርዕደ መሬት ሽሽት አብዛኞቹ የካታማንዱ ነዋሪዎች በክፍት ቦታዎች ላይ ሰፍረዋል፡፡ ወደቤታቸው መግባትም ፈርተዋል፡፡ ርዕደ መሬቱ ከተከሰተ 72 ሰዓታት ቢያልፍም፣ አስተማማኝ መረጋጋት ባለማየታቸው ሜዳ ላይ መሆንን መርጠዋል፡፡ በከተማዋ የሚገኘው ዋና ሆስፒታል በተጐዱ ሰዎች ተጨናንቋል፡፡ የሕክምና ዕርዳታ መስጠትም ከአገሪቱ አቅም በላይ ሆኗል፡፡
በኔፓል መሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ተላለፈ በሽታ ይቀሰቀሳል የሚል ሥጋት አለ፡፡ በሽታው ከርዕደ መሬቱ ባልተናነሰም የሕዝቡን ሕይወት አደጋ ውስጠ ሊከት እንደሚችል የትሪቡቫን ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግ ሆስፒታል ባለሙያ ዶ/ር ሳሚሪ ታፖ ተናግረዋል፡፡
በኔፓል አብዛኞቹ የውኃ መስመሮች ተሰባብረዋል፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎችም ከጥቅም ውጭ ሆነዋል፡፡ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡ በዚህ አደጋ ውስጥ ለምትገኘው ኔፓል እየተደረገ ያለው ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ግን የተጠናከረ አይደለም፡፡ ዘግይቷልም፡፡ አገሪቷ ካሏት 100,000 ወታደሮች 90 በመቶ ያህሉን በነፍስ አድን ሥራው ቢሰማሩም ከየፍርስራሹ ሥር የተቀበሩ ሰዎችን ጨርሶ ለማውጣት ተቸግረዋል፡፡ ያሉዋቸው 12 ሒሊኮፕተሮችም ተጐጂዎችን መታደግ አልቻሉም፡፡
በጊዜያዊ መጠለያ ሥፍራ ለሚገኙ ዜጐች ምግብና ውኃ ማቅረቡም ፈተና ሆኗል፡፡ ከሚስታቸውና ከአራት ሴት ልጆቻቸው ጋር በመጠለያ ውስጥ የሚገኙ አባወራን ጠቅሶ አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው፣ በመጠለያ ውስጥ ላሉ ሰዎች በቂ ምግብ እየቀረበ አይደለም፡፡ በመጠለያ ውስጥ ያሉ ዜጐችም ከመጠለያ መውጣትና ወደ ቤታቸው መመለስ አይፈልጉም፡፡ በዋና ከተማው ካታማንዱ አንዳንድ ሱቆች ቢከፈቱም ሕዝቡ ወደ ሥራ ለመሄድ አይፈልግም፡፡ ካለበት መጠለያ ሆነው ርዕደ መሬቱ እስኪረጋጋ ይጠብቃል፡፡ በትራፊክ መጨናነቅ የሚገለጸው የኔፓል ዋና ከተማም ወና ሆኗል፡፡
የኔፓል መንግሥት ሐኪሞች፣ አሽከርካሪዎች፣ ሔሊኮፕተር፣ ብርድ ልብስና ምግብ ጭምር ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዕርዳታ የጠየቀ ሲሆን ህንድ፣ ቻይና፣ እንግሊዝና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገሮች ዕርዳታ መለገስ ጀምረዋል፡፡ ሆኖም እየቀረበ ያለው ዕርዳታ በቂ እንዳልሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሳውቋል፡፡
አንድ አራተኛ የሚሆነው የኔፓል ሕዝብ በርዕደ መሬቱ ሳቢያ መጐዳቱን፣ 1.4 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ ዕርዳታ እንደሚፈልግም ገልጿል፡፡ ተጐጂዎችን ለመርዳት ከድርጅቱ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ፈንድ 15 ሚሊዮን ዶላር መልቀቁን ጠቁሟል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጡ ማዕከል በሆኑ አካባቢዎች ደግሞ የተገኘውንም የምግብ ዕርዳታ ማድረስም ሆነ ነዋሪዎችን ከአደጋው መታደግ አልተቻለም፡፡ በአካባቢው ያለው ከባድ የአየር ፀባይም ለሔሊኮፕተርም አዳጋች ሆኗል፡፡ በኔፓል ከዋና ከተማዋ ውጭ ያሉትን አብዛኞቹን መንደሮች መድረስም አልተቻለም፡፡ መንገዶች ተሰነጣጥቀውና ተደርምሰው ቦታቸውን ስተዋል፡፡ የስልክ መስመሮችም ተቋርጠዋል፡፡ መኪናም ሆነ ሰው የሚገባበት መንገድ የለም፡፡ አብዛኞቹ አካባቢዎች በመደረማመሳቸውም ቦታዎችን ለመለየት አዳጋችም ሆኗል፡፡ የኔፓል መንግሥትም በሔሊኮፕተር ከሚጣሉ ደረቅ የታሸጉ ምግቦችና መድኃኒት ውጪ ሌሎች ፍላጐቶችን ለማሟላት ተቸግሯል፡፡ ርዕደ መሬቱ አካባቢዎችንና ነዋሪዎችን አለያይቷል፡፡
የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ ከጉዳቱ የተረፉ ዜጐች የኔፓል መንግሥትን መውቀስ ጀምረዋል፡፡ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ መንግሥት ፈጣን ምላሽ አለመስጠቱ የኔፓል ዜጐችን አስቆጥቷል፡፡ ውኃ፣ ምግብና መሠረታዊ ፍላጐቶች ለተጐጂዎች በበቂ ሁኔታ አልቀረቡም ሲሉም ኮንነዋል፡፡
የኔፓል ጠቅላይ ሚኒስትር ኮይራላ ግን፣ ‹‹መንግሥት በርዕደ መሬቱ በተጐዱ አካባቢዎች ያሉትን ለመታደግ የተቻለውን እየሠራ ነው፡፡ አስቸጋሪ፣ ከቁጥጥር ውጭና ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ተከስተዋል፤›› ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1934 በኔፓል በደረሰው ከባድ ርዕደ መሬት ከ8,500 ሰዎች በላይ የሞቱ ሲሆን፣ አስከፊ የተባለው የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰው ከ81 ዓመት በኋላ ነው፡፡ ተንታኞች እንደሚሉት አሁን በተከሰተው አደጋ ከአሥር ሺሕ በላይ ሊሞቱ ይችላሉ፡፡
በደቡብ እስያ የምትገኘው ኔፓል ወደብ አልባ አገር ስትሆን፣ 28 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጐችም አሏት፡፡ ከቻይናና ከህንድ የምትዋሰነው ኔፓል፣ በዓለም ትልቁን የኤቨረስት ተራራን ጨምሮ በርዝመታቸው ከታወቁት አሥር ተራራዎች ስምንቱ ይገኙባታል፡፡ ተራራማና አቀበት ሥፍራዎች የሚበዙባት አገርም ናት፡፡ የቱሪስት መስህብ ስትሆን፣ በተለይ ተራራ በሚወጡ ጐብኚዎች ትታወቃለች፡፡ አገሪቷ የተለያዩ ፊልሞች ለመሥራትም ተመራጭ እንደሆነች ይነገራል፡፡