Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርበድብልቅልቅ ዕውቀት የተሳሳተ ንፅፅር ከማድረግ እንጠንቀቅ

በድብልቅልቅ ዕውቀት የተሳሳተ ንፅፅር ከማድረግ እንጠንቀቅ

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ምርጫ 2007 ብዙ ነገር እየነገረንና እያስደመመንም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ መሪዎቹን በችሎታቸው ለመመዘን ጉጉት እያሳየ ነው፡፡ ተከራካሪዎች ግን የተጠበቁትን ያህል ያረኩት አይመስልም፡፡ የራሳቸውን ፖሊሲ ማብራራት ሲሳናቸውና በጋዜጠኞች በሚቀርቡ ጥያቄዎች ሲደናገጡ ይስተዋላሉ፡፡

በተለይም ሊበራሊዝምና ኒኦ ሊበራሊዝም የሚባሉ ቃላት በተደጋጋሚ ቢያጋጥሙም ተከራካሪዎች ጥርት ያለ ሙግት ሊገጥሙ አልቻሉም፡፡ በደርግ ጊዜ ይመስለኛል ሊበራሊዝም የወግ አጥባቂነት ተቃራኒ ወይም ተራማጅነት ተደርጎ ተተርጉሞ ነበር፡፡ ወግ አጥባቂነት ከነበረ አስተሳሰብ ጋር አለመላቀቅን ማሳያ ሲደረግ፣ ተራማጅነት ደግሞ አዲስ ሐሳብ ለመቀበል መፈለግን ያመለክታል፡፡

- Advertisement -

በአሁኑ ጊዜ የእንግሊዝኛ ቃላት ዓለም አቀፋዊ ታዋቂነት ስላገኙ በኢትዮጵያ ውስጥም ከአማርኛ ቃላት ይበልጥ ይታወቃሉ፡፡ ስለዚህም ሕዝብ ይበልጥ የሚያውቃቸውን የእንግሊዝኛ ቃላትን መጠቀም ሐሳብን በተሻለ ሁኔታ መግለጽ ያስችላል፡፡

ሊበራሊዝም በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ መስኮች የሚያጋጥም ሲሆን በተለያዩ መስኮች ያሉትን ትርጉሞች ማቀላቀል ውዥንብር ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካና በእንግሊዝ በፖለቲካው ወግ አጥባቂ የሆኑት ሪፐብሊካንና ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲዎች በኢኮኖሚው ወግ አጥባቂ ከሆነት ከዴሞክራትና ከሌበር ፓርቲዎች የበለጠ ሊበራል አቋም አላቸው፡፡ ኒኦ ሊበራሊዝምን በመጀመሪያ እንደ የኢኮኖሚ ሥርዓት የተቀበሉት የፖለቲካ መሪዎችም የወግ አጥባቂው የአሜሪካ ሪፐብሊካን መሪ ሮናልድ ሬጋንና የእንግሊዝ ኮንሰርቫቲቭ መሪ ማርጋሬት ታቸር ናቸው፡፡

በእኛ ሁኔታ ለምርጫ ውድድር የቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ጠያቂ ጋዜጠኞች ፖለቲካዊ ሊበራሊዝምንና ኢኮኖሚያዊ ሊበራሊዝምን ደበላልቀው ሲወያዩና ሲያወያዩ ይስተዋላሉ፡፡ ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን በሊበራሊዝም ፍልስፍና የሚያመሳስላቸው፣ ሁለቱም ግለሰብን ማዕከል ስለሚያደርጉ ነው፡፡ ከላይ እንዳየነው ምሳሌ በፖለቲካው ሊበራል የሆኑ በኢኮኖሚው ወግ አጥባቂ ወይም በፖለቲካው ወግ አጥባቂ የሆኑ በኢኮኖሚው ሊበራል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የፖለቲካ ሰዎች በኢኮኖሚው ላይ ውሳኔ ሰጪዎች ቢሆኑም፣ የኢኮኖሚ ጉዳይ ክርክሩ በኢኮኖሚስቶች መካከል ቢደረግ የበሰለ ውይይት እንሰማ ነበር፡፡ ያስተዋልኩትን ጉድለት ለመግለጽ የማተኩረው በኢኮኖሚያዊ ሊበራሊዝም ላይ ነው፡፡

ኒኦ ሊበራሊዝም ማለት አዲስ ዓይነት ሊበራሊዝም ወይም ዳግም የመጣ ሊበራሊዝም ማለት ስለሆነ፣ ስለአዲሱ ከማወቅ በፊት ስለቀድሞው ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ስለ ኒኦ ሊበራሊዝም ሊናገሩ የሚችሉትም የቀደመውን የተገበሩና በአዲስ የገበያ ሁኔታ እንዴት እንደሚተገብሩ የሚያስጨንቃቸው፣ በሊበራሊዝም ውስጥ ያረጁ ያፈጁ አገሮች ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች ከኒኦ ሊበራሊዝም በፊት ስለ ሊበራሊዝም ማወቅ ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡

ዛሬ ኒኦ ሊበራሊዝምን የሚተገብሩ አገሮች ሊበራሊዝምን በ18ኛው ክፍለ ዘመን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ጀምሮ ለረዥም ዓመታት ሲተገብሩ ቆይተው፣ እ.ኤ.አ. ከ1930ዎቹ እስከ 1970ዎቹ በኢኮኖሚስት ኬንስ በተነደፈው በመንግሥት ኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ መግባት የፍላጎት ጎን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከተቋረጠ በኋላ፣ እንደገና እ.ኤ.አ. ከ1980ዎቹ ጀምሮ ወደቀድሞው ሊበራሊዝም የአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚ ፖሊሲ አስተሳሰብ ስለተመለሱ ነው ሥርዓቱ ስሙን በድጋሚ ያገኘው፡፡ እነርሱ በሊበራሊዝም ውስጥ አርጅተዋል፡፡ እኛ ግን ለሥርዓቱ ገና ሕፃን ነን፡፡

በሽምግልና ዘመን አረጋዊ ሰው ብዙ ዓይነት ሕመሞች ይገጥሙታል፡፡ ስኳር፣ የደም ግፊት፣ ኩላሊት፣ ጉበት ወዘተ ይፈራረቁበታል፡፡ ሕፃን ልጅ የዕድሜ ባለፀጎችን ሕመም አይቶ በፍርኃት አላድግም ቢል ራሱን ነው የሚጎዳው፡፡ ታዳጊ አገሮች የበለፀጉ አገሮች የገጠሟቸውን የገንዘብ ቀውሶች አይተው ከነፃ ገበያ ቢሸሹ ወይም በነፃ ገበያ ውስጥ አናድግም ቢሉ፣ የኋላ ኋላ ዕጣ ፈንታቸው ከኒኦ ሊበራሊዘም እግር ሥር መውደቅ ነው፡፡ የኒኦ ሊበራሊስቶቹን መዋዕለ ንዋይ መለመን ነው፡፡

ኒኦ ሊበራሊዝምን ለማውገዝ የአሜሪካው እ.ኤ.አ. የ2008 የገንዘብ ቀውስ ይነሳል፡፡ ጆሴፍ ስቲግሊዝ በአሜሪካ ተንደላቅቀው የሚኖሩት አንድ በመቶ የሚሆኑት ሀብታሞች ብቻ ናቸው አሉ ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ገና የገንዘብ ገበያ ሳይኖራት የአሜሪካ የገንዘብ ቀውስ ዓይነት ውስጥ ትገባለች ተብሎ ይሠጋል እንዴ? ከታዳጊ አገሮች በርካታ ሕዝብ ወደ አሜሪካ የሚፈልሰው የዘጠና ዘጠኝ በመቶ አሜሪካውያን ድሆችን ኑሮ ለመጋራት አይደለምን? ከዘጠና ዘጠኝ በመቶዎቹ አሜሪካኖች ኑሮ ባነሰ ሁኔታ በውጭ አገር እየሠሩ የሚኖሩ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን የሚልኩልን ድጋፍ ከኤክስፖርት ሸቀጦቻችን ከምናገኘው ገቢ ይበልጥ የለምን?

ታዲያ የአሜሪካና የአውሮፓውያኑን ኒኦ ሊበራሊዝም ከእኛው የሊበራሊዝም ተስፋና ህልም ጋር በማነፃፀር ክፉ ጎኑን ብቻ ማሰብ ለምን ያስፈልጋል? ለማንኛውም የእነርሱንና የእኛውን ጎን ለጎን ለማየት የቀድሞው ሊበራሊዝም ወይም ነፃ ገበያ ምን እንደሆነ ማወቁ ይጠቅማል፡፡

ኢኮኖሚክስ የሀብት ድልድል ጥበብ ነው፡፡ ይህ ድልድል በነፃ ገበያ ሥርዓት የሚከናወነው የገበያ ኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት በሆነው ቀጣይ ድርጅት (Marginal Firm) አማካይነት ነው፡፡

ወደ የአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤት የተመላለሰ ሰው በቀን ስንት ድርጅቶች ንግድ ፈቃድ እንደሚመልሱና ስንት ድርጅቶች ንግድ ፈቃድ እንደሚያወጡ ይመለከታል፡፡ ይህ ዘርፉ ሲከስር ለመውጣት የመጨረሻውና ዘርፉ ሲያተርፍ ለመግባት የመጀመርያው የሚሆነው ቀጣይ ድርጅት ነው የነፃ ገበያ የሀብት ድልድል ፍልስፍና ጽንሰ ሐሳብ የሆነው፡፡ ግለሰቦች በቅርብ ከገበያው በሚያገኙት መረጃ አማካይነት ከአክሳሪ የንግድ ዘርፍ ወጥተው ወደ አትራፊ የንግድ ዘርፍ ለመግባት የሚወስዱት ውሳኔ፣ የአገርን ሀብት በክፍላተ ኢኮኖሚዎችና በዘርፎች አቀላጥፎ ይደለድላል፡፡

ስለዚህም ከነፃ ኢኮኖሚ ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች አንዱ ለግለሰብ ከራሱ በላይ ማንም ሊያውቅለት አይችልም ሲሆን፣ ሁለተኛው ገበያውን በወረቀት በሚያነቡ ባለሙያዎች ተቀነባብሮ ሩቅ ላለ መንግሥት በሚደርሰው መረጃ ከሚሰጥ ውሳኔ ይበልጥ፣ ግለሰቡ አጠገቡ ካለው የገበያ መረጃ ተነስቶ የሚወስነው ውሳኔ ውጤት ያመጣል ነው፡፡

ከዚህ በተቃራኒ መንገድ በመንግሥት አስተዳደር የአገር ሀብት ወደ ማምረቻ ዘርፎችና ክፍላተ ኢኮኖሚዎች የሚደለደለው፣ በመንግሥት ከተጠቃለለ መረጃ ተነስቶ በሚወሰን የማዕከላዊ ዕቅድ ውሳኔ ወይም የተቀደደን በመጣፍ ግብታዊ ዕርምጃ ነው፡፡

በመንግሥት አስተዳደር ሀብትን የመደልደል ችግር በኢትዮጵያ የምናየው ሁኔታ ነው፡፡ በመንግሥት አምራች ድርጅቶች ስኳሩ ሲመረት ዘይቱ ይጎድላል፡፡ ዘይቱ ሲሟላ ሳሙናው ይጠፋል፡፡ ሳሙናው ሲመረት ዱቄቱ ያልቃል፡፡ አንዱ ሲሟላ ሌላው ይጎድላል፡፡ የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር ቀዳዳው ውስብስብ ይሆናል፡፡

የመንግሥትን በኢኮኖሚው ውስጥ እጁን ማስገባት የሚደግፉ ወገኖች ክርክር ገበያው አይጠራም፣ ጠርቶም አያውቅም፡፡ ስለዚህ በዋጋ አወሳሰን አድሏዊነት አንዱ ሲጠቀም ሌላው ይጎዳል ነው፡፡ መንግሥት የገበያውን አድሎ ካላስተካከለው ማንም አያስተካክለውም ነው፡፡ ይህን የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የነፃ ገበያ ተሟጋቾች የሚኮንኑት በንግድ ሥራ (Business) የመንግሥት እጅ ሲገባ፣ ከሸቀጥ ግብይቱ በቅድሚያ የሚገዙትና የሚሸጡት የመንግሥት ባለሥልጣናት ናቸው በሚል ሙስናን የሚገልጹበት ቃላት ናቸው፡፡

አንባቢያንን በአጽንኦት የማስገነዝበው ይህ የነፃ ገበያና የመንግሥት አስተዳደር ኢኮኖሚያዊ የሀብት ድልድል ልዩነት ኢኮኖሚስቶችን የሚያከራክረው ለግለሰብ በሽያጭ በሚቀርቡ ሸቀጦች ላይ ብቻ እንጂ፣ ለሕዝብ በጋራ በሚሰጡ የመሠረተ ልማት፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ወይም የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ አይደለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...