Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

በአሸባሪው አይኤስ በግፍ የተሰዉት ወጣት ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ሐዘን ላይ ለመድረስ ያመሩት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 21 ፖሊስ አባላትና ለቀስተኞች

ትኩስ ፅሁፎች

እኛው ነን

(በጌትነት እንየው)
እኛ ነን፤ እኛው ነን፤ እኛ የዛሬዎች
በአጭር የተቀጩ ሩቅ መንገደኞች
ሠላሳ ህልመኞች፣ ሠላሳ ተስፈኞች፣ ሠላሳ ወጣቶች
አገር እንደሌለው በሰው አገር ምድር ሲቀላ አንገታቸው
ወገን እንደ ሌለው ከሰው አገር ባህር ሲቀየጥ ደማቸው
በአገር ቁጭ ብለን ከዓለም ጋራ እያየን
ከሬት የመረረ ከቋጥኝ የሚከብድ
ከቶን የሚያቃጥል ከብራቅ የሚያርድ
አገር ያህል መርዶ በሰንበት አመሻሽ በአገር የተሸከምን
በገዛ ሞታችን እዝን የተቀመጥን፡፡
ካሳለፍነው ሕይወት ካለፈው መከራ
መማር የተሳነን ደመና ወራሾች፣
የሞትነውም እኛ ያለነውም እኛ
ከፋይም ተቀባይ እኛው ነን ባለዕዶች፡፡
እኛው ነን….
ከቅጣትም ቅጣት ከመርገምትም መርገምት፣
የገዛ አንገታችን በስለት ሲቀላ
የገዛ ደማችን ባህሩን ሲያቀላ
የራሳችንን ሞት ቆሞ መመልከቱ፣
ምን ያህል ነው ፍሙ? ምን ያህል ይከብዳል ሰቆቃው እሳቱ?
ምን ያህል ነው ሸክሙ? ምን ያህል ይዘፍቃል? መከራው ክብደቱ
ምን ያህል ይጠልቃል? ምን ያህል ይሰማል? መጠቃት ስለቱ
ሐዘን ነው? ቁጣ ነው? ፀፀት ነው? ምንድነው መጠሪያው? ምንድነው ስሜቱ?
እውን ይህን መአት ይኼን የእኛን መቅሰፍት
ቋንቋዎች በቃላት ችለው ይገልጹታል?
እውን ይህ ስቃይ፣ ይህንን ሰቆቃ፣ እናትና አገር ሸክሙን ይችሉታል?
እኛው ነን እኛው ነን…
ለዚህ ክፉ እጣችን ለዚህ መርገምታችን
ለዓለም ለፈጣሪ አልፈታ ላለው እንቆቅልሻችን
መነሻም መድረሻም ጥያቄዎች እኛ መልሶችም እኛው ነን፡፡
እኛው ነን የገፋን፣ እኛው ነን የከፋን
እኛው ነን ያጠፋን፣ እኛው ነን ያጠፋን፡፡
ከዘመን ጋር አብሮ መዘመን ተስኖን
ሰፊ አገር ይዘን በሐሳብ እየጠበብን
በፍቅር ተሳስቦ አብሮ መራመዱ አቀበት የሆነን
ቂም እየቆነጠርን፣ ቂም እየመነዘርን
በዛሬ መንጋጋ የትናንቱን ድርቆሽ የምናመነዥክ
በዛሬ ምድጃ የትናንቱን አመድ ታቅፈን የምንሞቅ
ባንድ ላይ ከመጓዝ በየፊና ሩጫ አረፋ ምንደፍቅ
እኛው ነን እኛው ነን….
ከእምነት የተፋታን ከፈጣሪ የራቅን፡፡
እኛው ተጋፊዎች፣ እኛው ተገፊዎች
እኛው አሳዳጆች፣ እኛው ተሳዳጆች
ካሳለፍነው ሕይወት ካለፍነው መከራ
መማር የተሳነን ደመና ወራሾች
እኛው ነን እኛው ነን እኛ የዛሬዎች
የነገ፣ የታሪክ ያገር ባለዕዳዎች፡፡
እኛው ነን….
በንፍገት በስስት በስግብግብ መዳፍ
ከድሆች ጉሮሮ ካፋቸው መንጭቀን
ሌሎችን ረግጠን ሌሎችን ጨፍልቀን
በሌሎች ጀርባ በሌሎች ጫንቃ ላይ ወደ ላይ መሳቡ ቅንጣት የማይጨንቀን
በማስመሰል ጥበብ በአድርባይ አንደበት በሸፍጥ የሠለጠን
ከብዙዎች ድርሻ ተሻምተን ተናጥቀን
ላንድ ለራሳችን በወርቅ ላይ አልማዝ በሕንፃ ላይ ሕንፃ
ስንቆልል ስንከምር የማይሰቀጥጠን፣
የመንፈስ ድውዮች የንዋይ ምርከኞች
የወንበር ሱሰኞች የሆድ አምላኪዎች
ከሰውነት ወርደን በነፍስ የኮሰመን የሥጋ ብኩኖች
የራሳችን ኃጢያት የራሳችን ሲኦል እኛው ነን መርገምቶች
እኛው ነን!
በዚህ ሁሉ ግና …..
መቼም ቢሆን መቼ ሰው ይሞታል እንጂ ተስፋ አይሞትምና
በመንገድ የቀሩት ወጣቶቻችን
በአጭር የተቀጨው ሐሳብ ምኞታቸው
ተስፋ አለን ተስፋቸው፡፡
በአገራቸው አፈር በታናሾቻቸው
ነገ ውብ ይሆናል ለምልሞ ይጸድቃል በዛሬው ደማቸው
ዛሬ የመከነው ውጥን ርዕያቸው
በጊዜና በአገር ነገ እውን ይሆናል ይፈታል ሕልማቸው
ይህ ነው መፅናኛችን ይህ ነው መፅናኛቸው፡፡

********

የደም ማኅተም

(በብርሃኑ ፈቃደ)

ደማችን ውኃችን የሚገበርለት

ውቅያኖስ ባሕሩ ምንድን ነው ያለበት?

በባሕሩ ዳርቻ የሰው ሁለት አየን

አንደኛው ሰማዕት ሌላኛው ሌጌዎን

ያንድ ፍጥረት ሁለት የሆነብሽ ምድር

ጨለማሽ አይንጋ መሬትሽ አይክበር

የሾህ ያሜኬላ የቁንጥር ያድርግሽ

የዘራሽ ያጨድሽው ዕብቅ ይሁንብሽ

እያልን ብንጮህ  ብዙ ብንራገም

የሔደን አይመልስ ላለነው አይረባም

ይልቅስ ተወቃሽ አለ ከበላይ

የዓለም ፈጣሪው የምድር የሰማይ

ከዘመናት በላይ በዕድሜ ’ሚጠቀስ

ለስማችን ጥሩ ጉምቱ ’ሚነቀስ

በጦር በቸነፈር በብዙ ሰቆቃ

’ራሳችን ተቀብሮ ስንኖር በሲቃ

ደ’ሞ ጊዜ አመጣ የምንታይበት፣

በ’ምነታችን ፍዳ የምንከፍልበት፤

ባ’ለም አደባባይ የምንሞትበት፣

ከባሕር ዳርቻ የምንቀላበት፡፡

እርግጥ ነው!

ባ’ዘናችን መሐል ባየነው መከራ

አማኝነታችን ባለም የተጠራ፤

እርግጥ ዘመን መጥቷል የምንከብርበት፣

የ’ምነት አክሊል ደፍተን የምንኮራበት

ሐበሻ እውስጡ የፍቅር ልብ አለው፣

መስቀሉም ጨረቃም ለዚህ ምስክር ነው፡፡

እምነት ከልብ እንጂ ከታይታ መራቁን

ያለም ሕዝብ አዳሜ ካ’በሻ ማወቁን

ቋሚ ምስክሩ የባሕሩ ዳርቻ

ባበሽ የቀለመ የፍቅር መክተቻ

የሆነው ፍጥረትህ ለከፈለው ዋጋ

ምንድን ነው ሚዛንህ የምትሰጠው ፀጋ?

አምላኬ ኤሎሔ ብሎ ለለመነህ

በጅረታም ደሙ ማተቡን ላሳየህ

የዓለሙ ፈጣሪ ምንድን ነው ውለታህ?

ደ’ሞ ላራጆቹ!

እናንተ በላቾች በላዔሰብ ሙላችሁ

ባረዳችሁት በግ እጅግ መቅለላችሁ

ጎልያድ ስትሆኑ ደካማው ረታችሁ

በምነት ማዕተቡ ቁልቁል ከተታችሁ

ከስለቱ ሰላ ካ’ረር ጠነከረ

ያ’በሻነት ልቡ ባ’ምላኩ ደደረ

ከሸላቾቹ እጅ በደሙ ከበረ::

*********

የዓባይ ልጅ

ዓባይ ዓባይ ስትሉ ታቆሙት ቸግሯችሁ

በደሙ ሊከትረው ከመድረሻው ገባላችሁ፡፡

********

የነፍስ ዕዳ

ባሕር ገብቶ ሲጠመቅ፣

ፍቅር ሲነሳ እያያችሁ፣

ሐበሾች ልብ አርጉ!

አንድ ይሁን ቤታችሁ

ማገር ምሰሷችሁ

የተከፈለበት!

የነፍስ ዕዳ ልጃችሁ

እንዳይታዘባችሁ፡፡

**********

የደም ቀንዲል

ሳይገልጡ መጽሐፉን፣

ሳያነቡ ገጹን፤

ቢጥሉት ከውኃ አርቀው ከባሕር፣

ብርሃኑን ጨረር ፀዳሉን የፍቅር፡፡

ያበሽ ደሙ ቢፈስ ቀንዲል ሆናት ላገር፣

በውኃ መቃብር የወንድሜነቱን ያብሮነት የፍቅር፣

አሳየው ላ’ለሙ በሚሞት ማንነት የኢ-መዋቲን ገቢር፡፡

ምንጫሮ፡- ብርሃኑ ፈቃደ፣ ለውዶቹ የዳርቻው ብፁዓን

የቢራቢሮ ክንፍ

የቢራቢሮ ክንፍ በቀላሉ ሊጎዳ የሚችል ከመሆኑ የተነሳ የአቧራ ብናኝ ቢያርፍበት ወይም ትንሽ እርጥበት ቢነካው እንኳ ቢራቢሮው መብረር አስቸጋሪ ይሆንበታል። የሚገርመው ግን ክንፎቹ ሁልጊዜ ንጹሕና ከእርጥበት የጸዱ ናቸው። የዚህ ሚስጥሩ ምንድን ነው?

ጃይንት ብሉ ሞርፎ በተባለው ቢራቢሮ (ሞርፎ ዲድየስ) ላይ ጥናት የሚያካሂዱ የኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንደገለጹት የዚህ ቢራቢሮ ክንፎች እንዲሁ ሲታዩ ልሙጥ ይምሰሉ እንጂ በጣም ጥቃቅን በሆኑ ልክ እንደ ጣሪያ ሸክላ በተነባበሩ ቅርፊቶች የተሸፈኑ ናቸው። በእነዚህ ቅርፊቶች ላይ ያሉ በጣም ጥቃቅን የሆኑ ሸንተረሮች የውኃ ጠብታዎችና የአቧራ ቅንጣቶች ተንሸራትተው እንዲወርዱ ያደርጋሉ። መሐንዲሶች ውኃና አቧራ የሚከላከሉ የተራቀቁ የኢንዱስትሪና የሕክምና መሣሪያዎችን ለመሥራት የዚህን ቢራቢሮ ክንፎች ለመኮረጅ ጥረት እያደረጉ ነው።

ተመራማሪዎች የቢራቢሮን ክንፍ አስመስለው ለመሥራት መሞከራቸው ሳይንስ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ የሚታየውን ንድፍ ለመኮረጅ ጥረት እያደረገ እንዳለ የሚያሳይ አንድ ተጨማሪ ምሳሌ ነው። ብሃራት ቡሻን የተባለ አንድ ተመራማሪ “በተፈጥሮ ውስጥ ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ ድረስ ለቁጥር የሚያታክቱ አስደናቂ የምሕንድስና ውጤቶችን ማግኘት ይቻላል” ብሏል።

ንቁ!

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች