ቶታል ኢትዮጵያ ለአሽከርካሪዎች ተጨማሪ ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል ሲሙሌተር (ምስለ መኪና) አስገባ፡፡ ድርጅቱ 500 አሽከርካሪዎች ያሉት ሲሆን፣ የሾፌሮችን የአነዳድ ብቃት ለማሻሻል እንዲቻል በሲሙሌተሩ ይሠለጥናሉ፡፡ ድርጅቱ ያስገባውን ሲሙሌተር ሚያዝያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲያስመርቅ የተገኙት የቶታል ኢትዮጵያ የትራንስፖርትና አቅርቦት ኃላፊው አቶ አልዓዛር አበበ እንደገለጹት፣ አሽከርካሪዎች ነዳጅ ጭነው በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በሲሙሌተሩ መሠልጠናቸው ክህሎታቸውን ያሳድግላቸዋል፡፡ የአሽከርካሪ ፈቃድ የሚሰጠው ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሲሆን፣ ቶታል ኢትዮጵያ ባለሥልጣኑን የማገዝ ሥራ እየሠራ መሆኑን አቶ አልዓዛር ተናግረዋል፡፡ ሲሙሌተሩ አራት ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡