Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኩሪፍቱ ትሩፋቶችና አዳማ ላይ ያሳረፈው አሻራ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ አንድ ብሎ የጀመረው በደብረ ዘይት ኩሪፍቱ ሐይቅ ዳርቻ ላይ በገነባው ሪዞርት ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ግን የኩሪፍቱ ስምንተኛ መዳረሻ  የሆነው ሪዞርት በአዳማ ተከፍቷል፡፡ ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፖ ኩሪፍቱ አዳማ በሚል ስያሜ የሚጠራውን ይህን ሪዞርት የከፈተው በአዳማ የሚገኘውን ማያ ሆቴል ለ15 ዓመታት በመከራየትና ኩሪፍቱ በሚታወቅበት ዲዛይን በመቀየር ነው፡፡

የአገር ውስጥና የውጭ እንግዶች በአማራጭ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ተብሎ በሚታመንበት ደረጃ የተለያዩ ሪዞርቶችን በማስፋፋትና በመገንባት ላይ ያለው ኩሪፍቱ ሪዞርት፣ በሆራ ሐይቅና በባህር ዳር ከተማ እንዲሁ ሌሎች ሪዞርቶች መገንባት ችሏል፡፡ በቅርቡ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ ከሚጠበቀውና በመቶ ሚሊዮን ብሮች ኢንቨስትመንት እየተደረገበት ካለው የደብረ ዘይቱ ሪዞርት ማስፋፊያ ጥሮጀክት በተጨማሪ፣ በቡራዩ የሚገነባው የኩሪፍቱ ቡራዩ ሪዞርት እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡

 በትግራይ ገርአልታ ውስጥ እየተገነባ ያለው የኩሪፍቱ ሪዞርት በቅርቡ ከአዳዲስ አገልግሎቶቹ ጋር ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ከካስቴል ወይን ጠጅ ጋር በመሆንም በዝዋይ የተከፈተው ካስቴል ኩሪፍቱ ወይን ሐውስም በኩሪፍቱ ሪዞርት ሥር የሚተዳደር ነው፡፡ በቅርቡም በሐዋሳ ኩሪፍቱ ሪዞርት ግንባታ እንደሚጀምር የቦስተን ፓርትነርስና የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

የኩሪፍቱ ጉዞ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የተገደበ ያለመሆኑን  አቶ ታዲዮስ ገልጸዋል፡፡ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች በመግባት ኩሪፍቱን አፍሪካዊ ብራንድ የማድረግ ራዕይ አላቸው፡፡ ወደዚህ ስኬት ለመጓዝም በቅርቡ በጂቡቲ ሞቻ ደሴት ላይ ለመገንባት ያቀዱት ሪዞርት ወደ ግንባታ እየተሸጋገረ ነው፡፡ እንደ ሩዋንዳና ኡጋንዳ ያሉ አገሮችም በኩሪፍቱ ደረጃ ሪዞርት በአገራቸው እንዲገነባላቸው ጠይቀዋል፡፡ ከጥያቄውም በላይ ለግንባታዎቹ የሚሆኑ ቦታዎችን እንዲያማርጡ ጭምር ዕድል እንደተሰጣቸው የገለጹት አቶ ታዲዮስ፣ ይህ ኩሪፍቱ በሌሎች አፍሪካ አገሮች ውስጥ እገነባዋለሁ ያለውን ሪዞርቶች እውን ለማድረግ ሰፊ ዕድል እንዳለው ይጠቁማል ብለዋል፡፡

 በአሁኑ ወቅት አዳማ ውስጥ የሚገኙ ሆቴሎች ዋናነት በኮንፈረንስ ቱሪዝም ላይ መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ የአዳማው ኩሪፍቱ ሪዞርት ግን ከዚህ በተለየ ለከተማው አዲስ አገልግሎት ይዞ እንደመጣ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አቶ ታዲዎስም ይህንኑ ሐሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት አዳማ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ታዋቂ ነች፤›› ያሉት አቶ ታዲዎስ፣ የኩሪፍቱ ዓላማ ደግሞ ከዚህ በተለየ መሥራት ነው ይላሉ፡፡ ኮንፈረንስ ቱሪዝምን በርካታ ሆቴሎች እየሠሩበት በመሆኑ የአዳማው ኩሪፍቱ የተለየ መንገድ ይዞ ለከተማዋ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ አንድ ዕርምጃ ወደፊት የሚያራምድ ይሆናልም ይላሉ፡፡ በተለይ ሰዎች ለእረፍት መጥተው ወይም ከሰኞ እስከ ዓርብ ድረስ ልጆቻቸውን ይዘው የሚመጡበት የመዝናኛ መዳረሻ (ቫኬሽን ዴስትኔሽን) እንዲሆን ጭምር ታስቦ የተገነባ ስለመሆኑም አቶ ታዲዮስ ጠቅሰዋል፡፡

ማያ ሆቴልን በኩሪፍቱ ደረጃ ለመቀየር በተያዘው ዕቅድ መሠረት እስካሁን የተሠራው ሥራ ግማሽ ያህል ደርሷል፡፡ እስካሁን ለመጀመርያው ምዕራፍ ሥራ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በማያ ሆቴል ውስጥ የሚሠራው ቀጣይና ሁለተኛው ምዕራፍ ሥራ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቃቸው የገለጹት አቶ ታዲዎስ፣ የማያ ሆቴልን ለ15 ዓመታት የተከራዩበትን ዋጋ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ግን በኩሪፍቱ የአገነባብ ሥልትና ደረጃ የተገነቡ 48 ልዩ መኝታ ክፍሎችን ሥራ ማስጀመር ተችሏል፡፡ ወደፊት ለውጥ የሚደረግባቸውና ተጨማሪ ክፍሎችን ጨምሮ በ96 መኝታ ክፍሎች ወደ ሥራ ገብቷል፡፡  

አቶ ታዲዮስ አዳማን ሌላዋ የኩሪፍቱ መዳረሻ ያደረጉበት ምክንያት በዘርፉ ያለውን አገልግሎት ከማስፋፋትና በደብረ ዘይት እየታየ እንዳለው ዕድገት እዚህም እንዲታይ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አዲሱ የፍጥነት መንገድና በለቡም በኩል እየተገነባ ያለው መንገድ በቅርቡ አገልግሎት ስለሚጀምር፣ ወደ አዳማ ለሚመጣ እንግዳም ሆነ ለአዳማና ለአካባቢው ነዋሪ በተለየ መንገድ አገልግሎት ለመስጠት ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከዚህም ሌላ የአዳማውን ሪዞርት ቱሪስቶች የመጀመርያ መዳረሻ ሊያርጉት ይችላሉ፤›› የሚሉት አቶ ታዲዎስ፣ ለዚህም ነው የአዳማውን ኩሪፍቱ ሪዞርት ዲዛይንና አገነባብ በከተማው ውስጥ በሌላና በአዲስ ዲዛይን እንዲገነባ የተደረገው ይላሉ፡፡

በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎች በመጠቀምና አገራዊ ገጽታን በተላበሰ አገነባብ የታነፁት የአዳማው ኩሪፍቱ ሪዞርት መኝታ ክፍሎች፣ እያንዳንዳቸው የራሳቸው በረንዳዎች ያሉዋቸውና ውስጣዊ ገጽታቸውም ያማረ ነው፡፡ የአዳማው ኩሪፍቱ ሪዞርት ከመኝታ ክፍሎቹ ባሻገር የቀድሞውን ማያ ሆቴል ገጽታ በእጅጉ ቀይሮታል፡፡ በዚህ ሥፍራ ኩሪፍቱ ደንበኞችን ያገናዘበውን አሻራ ያሳረፈበት ደግሞ የቀድሞውን የማያ  ሆቴል የመዋኛ ሥፍራ ለአገልግሎት ያበቃበት ዲዛይን ነው፡፡ ቀደም ብሎ የነበረው መዋኛ ገንዳ  ዙሪያውን ምንም ያልነበረበትን ሥፍራ ነበር፡፡ አሁን የእንግዶችን ቀልብ በሚሰብ ዲዛይን መገንባት ተችሏል፡፡ የመዋኛ ሥፍራው አንድ ጎን ወደ መዋኛ ገንዳ ገባ ያሉ የእንግዶች ማስተናገጃ እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡ በባህላዊ መንገድ ሳር ክዳን የተገነቡ ፒዛ፣ ኬክና ጁስ ቤቶች አሉት፡፡ በአንድ ጎን ደግሞ ኩሪፍቱ በሚታወቅባቸው ግብዓቶች የተገነቡ ክፍት ባር ይታያል፡፡ መዋኛ ገንዳውን ማዕከል ያደረገው አዲሱ ዲዛይን በአንድ ጎን የሙዚቃ ኮንሰርት ማሳያ አነስተኛ መድረክ ተበጅቶለታል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ የአዳማውን ኩሪፍቱ የመጀመርያውን ምዕራፍ ግንባታ መጠናቀቅ አስመልክቶ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የታደሙ እንግዶችም፣ የአዲሱ ኩሪፍቱ ዲዛይን ለአዳማ አማራጭ መዝናኛ ሥፍራ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ የዲዛይኑ አፍላቂ አቶ ታዲዮስ፣ ይህንን ቦታ በዚህ ደረጃ እንዲሠራ ማድረጋቸው ዋነኛ ምክንያት እንግዶች የተለየ ነገር እንዲያገኙ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ሁሉም የኩሪፍቱ ሪዞርቶችና የሚለዩባቸው ባህላዊ ግብዓቶች በአዳማው ሪዞርት ላይ ይታያል፡፡ በተለይ ኩሪፍቱ የሚጠቀምባቸው የአገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች በአብዛኛው ሊባል በሚችል ደረጃ በአገር ውስጥ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ከመኝታ ክፍሎች አንስቶ የመመገቢያ ጠረንጴዛዎቹና ወንበሮቹ ሳይቀሩ በአገር ውስጥ በሚገኙ ጥሬ ዕቃዎችና አገራዊ ይዘት ባላቸው ዲዛይኖች የተሠሩ ናቸው፡፡ ጠረንጴዛና ወንበሮቹ በእንጨት፣ በቆዳና በጠፈር የተሠሩ ናቸው፡፡ በእነዚህ ጠረንጴዛዎች ላይ ከማንኪያና ሹካዎቹ በስተቀር ጨው መነስነሻ፣ አፍ ማበሻ ወረቀት ማስቀመጫ፣ የሲጋራ መተርኮሻና ሌሎችም መገልገያዎች በቀላሉ ከቀርቀሀና ከእንጨት የተሠሩ ናቸው፡፡

መኝታ ቤቶቹ ውስጥም በተመሳሳይ መንገድ የሚሠሩ የተለያዩ መገልገያዎች ጎልተው ይታያሉ፡፡ ከቀርቀሃ የተሠራ ኮርኒስ፣ ከጣውላ የተሠራ ቁምሳጥንና በእንጨት ቅርፊት የተለበጠ ማቀዝቀዣ፣ በጥሬ ቆዳና እንጨት የተሠሩ ምቹ ሶፋዎች፣ በባህላዊ መንገድ የተሠሩ አልጋ ልብሶችና መጋረጃዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ኩሪፍቱ የሚጠቀምባቸው እነዚህ ዕቃዎች ደግሞ በሙሉ ለዚሁ አገልግሎት ተብሎ በተቋቋሙ ዲፓርትመንቶቹ የሚመረቱ መሆናቸው የኩሪፍቱን የተለየ አካሄድ አመላካች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ኩሪፍቱ በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለየ የሚታወቅበት ሌላው መገለጫው ደግሞ የራሱ የሆነ የሠራተኞች ማሠልጠኛ ማዋቀሩ ነው፡፡ የአዳማው ኩሪፍቱም ሥራ ሲጀምር ቀድሞ የማያ ሆቴል ሠራተኞችን በመረከብ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በኩሪፍቱ ደረጃ መሠረት አሠልጥኗል፡፡ ሥልጠናው በሠራተኞች ላይ ብዙ ለውጥ ማምጣቱን ሠራተኞች ይመሰክራሉ፡፡

ወ/ሮ ደብረ ወርቅ ኃይሉ የ32 ዓመት ወጣት ናት፡፡ ማያ ሆቴልን ኩሪፍቱ ሪዞርት ከመረከቡ በፊት ከስምንት ዓመታት በላይ አገልግላለች፡፡ ‹‹ኩሪፍቱ ማያ ሆቴልን እንደሚረከብ ሲሰማ ግን ብዙዎቻችን ሥጋት ውስጥ ወድቀን ነበር፤›› ትላለች፡፡ እንደፈራችው ሳይሆን ግን ሁሉም ሥራ መቀጠላቸውን ገለጸች፡፡ ‹‹ግን ቀድሞ በነበረው የአሠራር ሒደት አልቀጠልንም፡፡ እንደ አዲስ ወደ ሥልጠና ገባን፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ እንዴት እንግዳን ማስተናገድ እንደሚቻል የተሰጠው ትምርህት፣ ከዚህ ቀደም ከነበረን አሠራር ጋር ሳነጻጽረው በጭፍን እንሠራ እንደነበር እንድገነዘብ አድርጎኛል፤›› በማለት ትገልጻለች፡፡ መልካም ነገሮችን ስለመማሯና ጥሩ መሥራትም ጥቅም የሚገኝበት መሆኑን ያየሁበት ነው የምትለው ወ/ሮ ደብረ ወርቅ፣ የኩሪፍቱ ልምድ በአዳማ ላይ አዲስ ነበር ያመጣል ብላ ታስባለች፡፡ በአጭር ጊዜ የያነው ለውጥና ሠራተኛውን እያገኘ ያለው ጥቅም ከቀድሞው ጋር የማይገናኝ ስለመሆኑ ገልጻለች፡፡

የጥበቃ ሠራተኛው አቶ ፀጋዬ ገብሬ ደግሞ በቀድሞ አሠራር ደንበኞችን የምናስተናግደው በዘፈቀደ ነበር ይላሉ፡፡ ‹‹እንደውም አንድ ደንበኛ ወደ ግቢው መኪና ይዞ ሲገባ ማቆሚያ ከማሳየት ውጭ ምንም አናደርግም፡፡ አሁን ግን ይህ ተለወጠ፤ ሠለጠንን፤ ደንበኞችን ከበር ጀምረን እንንከባከባለን፤›› ብለዋል፡፡  የሠራተኞች ማሠልጠኛ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው የሚሉት አቶ ታዲዮስ፣ ‹‹እያንዳንዱን ሪዞርት ወይም ሎጅ አገልግሎት ከማስጀመራችን በፊት ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ ለዚያ የሚያስፈልጉ ሠራተኞችን የማሠልጠን ልምድ አለን፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ብዙዎቹ ሆቴሎች ብቁ የሆኑ ባለሙያ ማግኘት ችግር እንዳለባቸው ይታወቃል ያሉት አቶ ታዲዮስ፣ እኛ ግን ችግሩን ቀድመን በለመየታችን ሠራተኞች ለኩሪፍቱ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም እንዲተርፉ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ረዥም ራዕይ ከግብ ለማድረስ ኩሪፍቱ መወሰኑን ከአቶ ታዲዮስ ማብራሪያ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡  አንዱና ዋነኛው ተግባር በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጭ የተለያዩ ሪዞርቶችን መገንባት ሲሆን፣ ለሚገነቡትና በሥራ ላይ ላሉ ሪዞርቶች በሙሉ የኩሪፍቱን የአገልግሎት አሰጣጥ ሊመጥኑ የሚችሉ ሠራተኞችን የሚያፈራ ከፍተኛ ማሠልጠኛ መገንባትም ሌላው ውጥናቸው ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ቱሪስቶች እንዲጨምሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ከፍተኛ የሆነ ሥራ እየሠሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች