Sunday, June 4, 2023

የደቡብ አፍሪካ ጎዳናዎች የፓን አፍሪካኒዝም መሞትን አመላካች ናቸውን?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ደቡብ አፍሪካ በመኖር ላይ ያሉ የአፍሪካ ልጆች ላይ የደረሰው አሰቃቂ አደጋና ጉዳት በመላው ዓለም ግርምት የፈጠረ ነው፡፡ በተለይ ለአፍሪካውያኑ ጉዳዩ የበለጠ አንገብጋቢና የአገሮቹ የተናጠል ውሳኔና የጋራ ዕርምጃ፣ በአኅጉሪቱ ሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖስ ምን ይሆናል ብለው እንዲጨነቁ ያስገደደ ድርጊት ሆኗል፡፡

ደቡብ አፍሪካውያን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛትና ከአፓርታይድ አገዛዝ ነፃ እንድትወጣ ለአመራሮች ሥልጠና በመስጠት፣ የነፃነትን ትርጉም በማካፈልና በተለያዩ መንገዶች ደቡብ አፍሪካን በቅርበት ለረዳችው የኢትዮጵያ ዜጎች ጉዳዩ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ኢስላሚክ ስቴት የተሰኘው አሸባሪ ቡድን በሊቢያ ኢትዮጵያዊያንን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ የወሰደ ቢሆንም፣ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰው ጉዳትና አሁን የሚገኙበት አስጊ ሁኔታ በውል አልታወቀም፡፡

ይህ የኢትዮጵያዊያንና የአፍሪካ አገሮች ዜጎች ጉዳትን በማየት አንዳንዶች የአፍሪካውያን የመረዳዳትና የወንድማማችነት ስሜት መሞቱን እስከማወጅ ደርሰዋል፡፡ የእነዚህን ተስፋ የቆረጡ አፍሪካውያንን ዝርዝር ከተቀላቀሉት መካከል አንዱ አሊ ሙፉሩኪ ናቸው፡፡ የታንዛኒያው ኢንፎቴክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሊሚትድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙፉሩኪ፣ ‹‹Reflections on Late President Kwame Nkruman’s Pan-Africanism Legacy›› በሚል ርዕስ በባህር ዳር ከተማ ከሚያዝያ 10 እስከ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በተካሄደው የጣና ፎረም አንዱ ክፍል ‘የመለስ ዜናዊ መታሰቢያ የሌክቸር ሲርየስ’ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ የፓን አፍሪካኒዝም አባት ተደርገው የሚወሰዱት ክዋሜ ንክሩማህ ፓን አፍሪካኒዝምን በተግባር ቀድመው የገደሉ መሆናቸውን ተከራክረዋል፡፡

ከአፍሪካ ታላላቅ ልጆች መካከል አንዱ ነበሩ የተባሉትን መለስ ዜናዊን ሥራና ሕይወት ለማስታወስ ሌክቸር ሲርየስ መዘጋጀቱን ያደነቁት ሙፉሩኪ፣ በአፍሪካውያን ልዩ ቦታ ስለሚሰጣቸው ክዋሜ ንኩሩማህ ደካማ ጎን ለመናገር የመረጡት በአፍሪካ ስለመልካም አመራር መለያ ባህርያት ያለውን አረዳድ ለማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹በዚህ ሳምንት የፓን አፍሪካኒዝም ህልም ጭላንጭል በመጨረሻ ሲጠፋ አይተናል፡፡ ይህ ቢያንስ ለእኔ እውነት ነው፡፡ ይህን ህልም ለማንሰራራት የሚቻል ከሆነ ትልቅ ጥረት ይጠይቃል፤›› ያሉት ሙፉሩኪ፣ ንኩሩማህ የችግሩ ምንጭ እንጅ መፍትሔ እንዳልሆኑ አስገንዝበዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች የተገደሉት፣ አካላቸው የተቆራረጡ፣ የተደፈሩትና በቁማቸው የተቃጠሉት በንክሩማህና ሌሎች መሰሎች የተሳሳተ የአመራር ዘይቤ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ አፍሪካውያን መደበቂያ አጥተው በሌሎች አፍሪካውያን እንደ እንስሳ እየታደኑ ያሉት፣ እነ ንክሩማህ ባስተዋወቁት የአመራር ሥልት የተነሳ እንደሆነም ሙፉሩኪ በድፍረት አስረድተዋል፡፡

ንክሩማህ እ.ኤ.አ. በ1957 የጋናን ነፃ መውጣት በፈጠረላቸው ዕድል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ፣ በፓርቲያቸው ሲፒፒ ፍፁም የበላይነት የተያዘው ፓርላማ ካወጣቸው ቀዳሚ ሕጎች አንዱ የውጭ ዜጎችን ከጋና ስለማስወጣት የሚደነግግ ሕግ እንደነበር ሙፉሩኪ አስታውሰዋል፡፡ ሕጉ ምንም እንኳን ጋናዊ ያልሆኑና ለአገሪቱ ሥጋት የሆኑ ሰዎችን ለማስወጣት ያለመ ቢሆንም፣ በተግባር ግን በትውልድም ሆነ በሕግ የጋና ዜጋ የሆኑ ሰዎችን ከአገራቸው ለማፈናቀል ጥቅም ላይ መዋሉን አመልክተዋል፡፡

ሙፉሩኪ ይህ የንክሩማህ ድርጊት በፓን አፍሪካኒዝም እምነታቸው ላይ ጥርጣሬ ማሳደሩን ጠቅሰዋል፡፡ ከሁሉም የባሰው ናይጄሪያ፣ አይቮሪኮስትና ሌሎች በርካታ አገሮች ይህንኑ ልምድ በመቅሰም ተመሳሳይ ሕግ ማውጣታቸውና በበቀል ዕርምጃ ጋናውያንን ከአገራቸው ማባረራቸው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች የበርካታ ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት ማናጋታቸውንና በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ላይም በቀላሉ የማያገግም ጉዳት ማስከተላቸውንም አስታውሰዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1965 በአክራ በተካሄደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሪዎች ጉባዔ የመጨረሻ ንግግር ያደረጉት ንክሩማህ፣ በወቅቱ ነፃ የአፍሪካ አገሮች አንድ መንግሥት እንዲመሠርቱ ጥሪ ማድረጋቸውን ሙፉሩኪ አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ 33 አገሮች የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ግን 54 በውስጥ ጉዳያቸው ማንም ጣልቃ እንዳይገባባቸው አምርረው የሚቃወሙና ከቅኝ ገዥዎቻቸው የወረሱትን ድንበር መለስ እንቅስቃሴ የሚያከብሩ አገሮች መኖራቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ንክሩማህ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሪዎች ጉባዔ የመጨረሻ ንግግር ካደረጉ ከ50 ዓመት በኋላ፣ የድርጅቱ ተተኪ የአፍሪካ ኅብረት ወጪውን መሸፈን የማይችል በተለይም ለሰላም አስከባሪ፣ ለስደተኞችና እንደ ኢቦላ ያሉ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታዎችን እንኳን ማቅረብ የማይችል ተቋም መሆኑ አሳዛኝ እንደሆነም ሙፉሩኪ ገልጸዋል፡፡ የኅብረቱ ጽሕፈት ቤት በቻይና የተለገሰ መሆኑም የዚህ አንዱ ማሳያ አድርገው አቅርበዋል፡፡

አፍሪካ ለሉላዊነት (Globalization) የቀረበላትን ጥሪ ተቀብላ ለንግድ በሯን ለሁሉም ክፍት ያደረገች ቢሆንም፣ አፍሪካውያን የሌላ አፍሪካ አገርን ድንበር ተሻግረው ለመሥራት እጅግ እስቸጋሪ ፈተናዎችን እንደሚጋፈጡ ግን ጠቁመዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ በጥቁር አፍሪካውያን ስደተኞች ላይ ጥቃት እየተሰነዘረ ያለውም የተመቻቸ ሁኔታን መሪዎች ባለመፍጠራቸው እንደሆነ ሙፉሩኪ አስረድተዋል፡፡ የሩዋንዳ ስደተኞችን አገራቸው ባለፈው ዓመት በብዛት ማባረሯን ያስታወሱት ሙፉሩኪ፣ ኬንያም በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት የሶማሊያ ስደተኞችን ለማባረር ማቀዷን ጠቁመዋል፡፡

የአክራው የመሪዎች ጉባዔ ከተካሄደ ሃምሳ ዓመት የሞላው ቢሆንም፣ አፍሪካውያን ለአንድነት ፕሮጀክታቸው የሚያሳዩዋቸው የስኬት ታሪኮች እጅግ ጥቂት መሆናቸውን ያመለከቱት ሙፉሩኪ፣ ፓን አፍሪካኒዝም የሞተው በደቡብ አፍሪካ የተከሰቱት አስቀያሚ ድርጊቶችን ቀድሞ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ክዋሜ ንክሩማህ ይህን ህልም ለማጥፋት የመጀመሪያውን ቁልፍ ሚና መጫወታቸውንም አስረድተዋል፡፡

‹‹ንክሩማህ የአፍሪካ ጀግና አይደሉም››

አሊ ሙፉሩኪ የክዋሜ ንክሩማህን ጠንካራ ጎኖች እንደሚገነዘቡ በዚህም ትኩረት የሚስቡ፣ ግርማ ሞገስ ያላቸው፣ በንግግር ክህሎታቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው፣ ቆራጥ የነፃነት ታጋይ፣ ታላቅ የፖለቲካ አደራጅና አዲስ ሐሳብ አፍላቂ መሆናቸውን ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡ ለአንድ ነፃና የተባበረች አፍሪካ መሥራች አባት እንደሆኑም ያምናሉ፡፡

ይሁንና እነዚህ የንክሩማህ ጠንካራ ጎኖች ደካማ ጎኖቹን ሊሸፍኑ እንደማይችሉም ተከራክረዋል፡፡ እንደ ግለሰብም ሆነ መሪ ንክሩማህ አሁን አፍሪካ የምትፈልጋቸውን መሪዎች ባህርይ እንደማያሟሉም አመልክተዋል፡፡ ንክሩማህ አወዛጋቢ፣ ትዕግሥት የሌላቸው፣ ለሌሎች ክብር የማይሰጡና ሌሎችን የማይሰሙ፣ ነገሮችን በኃይል እንጂ በሰላማዊ መንገድ የማይፈቱ፣ ሙሰኛ የነበሩና አምባገነን መሆናቸው የከሸፉ መሪ እንደሚያደርጋቸውም ገልጸዋል፡፡

በተለይ የጋና መሪ በነበሩባቸው እ.ኤ.አ. ከ1957 እስከ 1966 በዘለቁት ጊዜያት ንክሩማህ የፈጸሟቸው ተግባራት የጥሩ መሪ መሥፈርትን የሚያሟሉ ሆነው እንዳላገኟቸው ዘርዝረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ፓርቲያቸውና ንክሩማህ በግላቸው ከሚያራምዷቸው ሐሳቦች ውጪ የሚያምኑ ግለሰቦችን ሕግን ተገን አድርገው ማጥቃት፣ ጓደኞቻቸውንና ወገኔ የሚሏቸውን መሾማቸው፣ ተቃዋሚዎቻቸውን እስከ አምስት ዓመታት ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማሰር የሚያስችል ሕግ ማፅደቃቸው፣ ዳኞችን ለማባረር የሚያስችል ሥልጣን ለማግኘት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻላቸው፣ ከሲፒፒ ውጪ ሌላ ፓርቲ እንዳይንቀሳቀስ መከልከላቸው፣ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አንድ ዕጩ ብቻ እንዲኖር ማድረጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህ የንክሩማህ ድክመቶች የአፍሪካ አቻዎቻቸውን ጭምር ማማረሩን የጠቆሙት ሙፉሩኪ፣ እ.ኤ.አ. በ1965 በአክራ በተካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ጥሪ ከተደረገላቸው ነፃ የአፍሪካ አገር መሪዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ያልተገኙት ንክሩማህ ለአፍሪካ ኅብረት እንቅፋት እየሆኑ ነው በማለት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

የጋና ፕሬዚዳንት ሆነው በድጋሚ ከተመረጡ ስድስት ወራት እንኳን ሳይሞላ የቬትናም የፖለቲካ ኃይሎችን ለማስታረቅ ከአገር ሲወጡ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሲደረግባቸው፣ ብዙዎች ያልተደነቁትም በዚሁ ባህሪያቸው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

‹‹ንክሩማህ ጀግና አልነበሩም፣ አገር ገንቢም አልነበሩም፣ ፓን አፍሪካኒስትም አልነበሩም፡፡ የታሪክ ጸሐፊዎች ባለፉት 50 ዓመታት ከሳሉት የተሳሳተ የንክሩማህ ምሥል መለከፍ መላቀቂያ ጊዜው አሁን ነው፤›› ያሉት ሙፉሩኪ፣ የንክሩማህ የኢኮኖሚ አስተዳደርም እንደ ፖለቲካ አመራራቸው ሁሉ በችግር የተሞላ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ነፃ ከወጡ የአፍሪካ አገሮች ሁሉ የበለፀገች የነበረችው ጋና ከንክሩማህ የስምንት ዓመታት አመራር በኋላ በሙስና የተነሳ እጅግ የተራቆተች እንደነበረችም ጠቅሰዋል፡፡

ንክሩማህ የአፍሪካ ጀግና ለመሰኘት ያላቸው የአመራር ሪከርድ በቂ እንደማያደርጋቸው የተከራከሩት ሙፉሩኪ የተሻለ የአገር ግንባታ ሥራ የሠሩ፣ ብዙኃነትን ያቻቻሉ፣ አገሮቻቸውን ለብልፅግናና ሰላም ያበቁ መሪዎችን ጀግና በማድረግ ‹‹መስፈርታችንን ከፍ እናድርግ፤›› በማለት ደምድመዋል፡፡

መስመር የሳተ ትችት?

አሊ ሙፉሩኪ ስለ ንክሩማህ የሰላ ትችት ባቀረቡበት መድረክ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች፣ የቀድሞ መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችና የታወቁ ምሁራን ከታዳሚዎች መካከል ይገኛሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ብዙ ታዳሚዎች ፊት ላይ የመከፋት ስሜት ይነበብ ነበር፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም በንግግሩ መሀል አቋርጠው ወጥተው ካለቀ በኋላ ወደ አዳራሹ ገብተዋል፡፡

ስለ ንክሩማህ እንዲናገሩ ዕድል የተሰጣቸው ሌሎች ሁለት ምሁራን የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪና በተመድ የሶሪያ ልዩ የሰላም መልዕክተኛ የነበሩትና የአልጀሪያ የነፃነት ታጋይ የነበሩት አምባሳደር ላክድሃር ብራሂሚ፣ ንክሩማህ የአፍሪካ ጀግና መሆናቸውን ተከራክረዋል፡፡

ለአንዳንዶች የሙፉሩኪ ንግግር ስለ ንክሩማህ ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ጠቃሚ ነበር፡፡ ሌሎች ግን ሙፉሩኪ የያዙት አቋም መስመር የለቀቀ መሆኑን ተከራክረዋል፡፡

የመድረኩ መሪ የአፍሪካ ኅብረት፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ እርከን አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱል ሞሐመድ ንክሩማህን ሲገልጹ፣ ‹‹ታላቅ ፓን አፍሪካዊ ተሟጋች፣ ሐሳብ አፍላቂና መሪ፤›› ብለዋል፡፡ የንክሩማህ ሐሳብ የአፍሪካ ዜጎችን፣ መሪዎችንና ሌሎች ሦስተኛ ወገን ተመልካቾችን የሚያነሳሳ እንደሆነም መስክረዋል፡፡

‹‹እኛ አፍሪካውያን ጀግኖቻችን ዝቅ ማድረግ እንወዳለን፤›› ያሉት ምቤኪ፣ የአፍሪካ መሥራች አባቶች ድክመት ቢኖርባቸውም ስኬታቸውና ጅምራቸው ለተሻለች አፍሪካ ጥርጊያ መንገድ በመሆኑ ሊሞገሱ እንደሚገባ ተከራክረዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1964 በካይሮ በተካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ንክሩማህ ስለአንድ የአፍሪካ መንግሥት ሲያወሱ በቦታው እንደነበሩ ያስታወሱት አምባሳደር ብራሂሚ፣ ሐሳቡን የጋና ልዑካን ጭምር ይቻላል ብለው እንዳልተቀበሉት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ብዙዎቻችን የምናደንቀው ሐሳቦቹን ነው፡፡ አሁንም ድረስ የአንድ የአፍሪካ መንግሥት ሐሳብ ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡ ከ50 ዓመታት በኋላ ነገሮች እንዴት መጥፎ እንደነበሩ መናገር ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ከነፃነት በኋላ በነበሩት ዓመታት ነገሮች እንዴት አስቸጋሪ እንደሆኑ ግን አውቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ንክሩማ ላይ ለመፍረድ መጠቀም ያለብን መሥፈርት በጊዜው የነበረውን እንጂ፣ አሁን ያሉትን የአመራር መሥፈርቶች መሆን እንደሌለበትም ተከራክረዋል፡፡ በ1950ዎቹና 60ዎቹ የነበረው የመንግሥት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥበብ ከዛሬው ፈጽሞ የተለየ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ ለአብነትም በወቅቱ ካፒታሊስት ያልሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓትና የአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት ተቀባይነት እንደነበራቸው ጠቅሰዋል፡፡

የአፍሪካ የኢኮኖሚ ልማትና ዕቅድ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ፕሮፌሰር አደባዮ ኦሊኮሺ ድክመት የሌለበት መሪ እንደሌለ አስታውሰው፣ የንክሩማህ ድክመት የዊንስተን ቸርችልና የኦቶማን ቢስማርክም ድክመት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በተጨባጩ ዓለም የሌሉ መሥፈርቶችን በማውጣት ጀግኖቻችንን መግደል የለብንም፤›› በማለትም የሙፉሩኪን ድምዳሜ ተቃውመዋል፡፡

የቀድሞው የቦትስዋና ፕሬዚዳንት ፌስተስ ሞሃይ በሙፉሩኪ የቀረበው ትንታኔ ትክክል ቢሆንም ድምዳሜው ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ንክሩማህ ታላቅ መሪ ቢሆንም ፍፁም ሰው ግን አልነበረም፡፡ ሁላችንም እንደዚያው ነን፤›› ያሉት ሞሃይ፣ በደቡብ አፍሪካና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የተከሰቱት አስቀያሚ ድርጊቶች አስቸጋሪ ጊዜያትን የሚጠቈሙ ቢሆንም፣ የፓን አፍሪካኒዝም መሞትን የሚያረጋግጡ እንዳልሆኑም አመልክተዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ መርሐጽድቅ መኮንን ሙፉሩኪ ያቀረቡት የንክሩማህ ታሪክ ብዙዎች የሚሸሹት እንደሆነ አስታውሰው፣ ይህ የተሟላ ዕይታ ለመያዝ ጠቃሚ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ንክሩማህ ለደቂቃ ቢነቁና በደቡብ አፍሪካ ደርባንና ጆሃንስበርግ እየተከናወነ ያለውን ነገር ቢያዩ ምን ይላሉ?›› ያሉት አቶ መርሐጽድቅ፣ እ.ኤ.አ. በ2001 በደቡብ አፍሪካ ደርባን የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ዘረኝነትን፣ የውጭ ዜጎችን መጥላትንና ሌሎች የአለመቻቻል ምንጮችን ስለማስወገድ የሚደነግግ ስምምነት ማፅደቁ ከአሁኑ ክስተት አንፃር ተቃርኖ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ከኮንጎ የመጡ አንድ አስተያየት ሰጪም ንክሩማህ አፍሪካውያን የአኅጉሪቱ ሀብት ላይ ቁጥጥርና ባለቤትነት እንዲኖራቸው፣ በንግድና በመሳሰለው ጉዳይ ላይ የፖለቲካ አንድነት እንዲኖራቸው፣ እንዲሁም የአፍሪካ ዜጎች በነፃነት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ከማንም በላይ የታገሉት ንክሩማህ ጀግና ካልተባሉ ማን ሊባል ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ከአምባሳደር ብራሂሚ ጋር በመስማማት፣ ‹‹የ1960ዎቹ አመለካከት ከአሁኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አስተሳሰብ የተለየ በመሆኑ፣ ስለሊቢራል ዴሞክራሲ፣ ልማት፣ የውጭ ግንኙነትና የመንግሥት መዋቅር ንክሩማህን ስንፈርጅ በጊዜው መሥፈርት መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ንክሩማህ በአንድ የተለየ መስክ ከፍ ያለ ቢሆኑና በሌሎች ሁኔታዎች ግን ድክመት ቢኖርባቸው ጀግንነቱን እንደማያጠፋው ገልጸዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የተከሰተው እጅግ አሳፋሪ ቢሆንም፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን ድርጊቱን መቃወማቸውንና ለተጠቂዎቹ ትብብር እያደረጉና ከለላ እየሰጡ በመሆናቸው፣ በጅምላ ሁሉንም መውቀሱ ጠቃሚ እንደማይመስላቸውም አመልክተዋል፡፡

የአፍሪካ አንባውንድ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ራሔል ካሳሁን፣ ከምንም ነገር በላይ በመድረኩ በነፃነት የሐሳብ ልውውጥ መደረጉ ትልቅ ስኬት መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፣ ‹‹መሪዎች ፍፁም አለመሆናቸውን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ለጥፋታቸውም ይቅርታ ማድረግ አለብን፡፡ ንክሩማህ በርካታ ችግሮች ነበሩባቸው፡፡ ምክንያቱም ከጊዜያቸው የቀደሙና ትልቅ ህልም የነበራቸው በመሆናቸው ነው፡፡ የንክሩማህ ህልም በአንድ ሰው የሚሳካ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የጣና ፎረምን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ሙፉሩኪ የሰላ ትችት ቢያቀርቡባቸውም፣ ‹‹ንክሩማህ የአፍሪካ ብርቅዬ ልጅ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ትችቱም መስመር የሳተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የጣና ፎረም የቦርድ ሰብሳቢ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የቀረበውን ሐሳብ ማንም ወደደውም ጠላውም በነፃነት በአፍሪካ ጉዳይ ግለሰቦች ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የመድረኩ ተሳታፊ መሰል ትንታኔና የተለያዩ አመለካከቶች በኢትዮጵያ መሪዎች ላይ ያለ ገደብ ሲቀርቡ ማየት እንደሚመኙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -