በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በወርቅ ደረጃ ከሚመደቡ ታላላቅ የጎዳና ውድድሮች የቶኪዮ ማራቶን አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ውድድሩ ባለፈው እሑድ ሲከናወን በኬንያውያን የበላይነት ተጠናቋል፡፡ ለውድድሩ ትልቅ ግምት ከተሰጣቸው ኢትዮጵያውያን መካከል ፀጋዬ ከበደ ዘጠነኛ ሆኖ ያጠናቀቀበት ውጤት ተጠቃሽ ነው፡፡ በሴቶች መካከል በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር ኬንያዊቷ ሳራ ችፕችርችር አሸናፊ ስትሆን፣ ኢትዮጵያዊቷ ብርሃኔ ዲባባ ሁለተኛ መውጣቷ ታውቋል፡፡ በወንዶች ማንንም ጣልቃ ሳያስገቡ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ካጠናቀቁት ኬንያውያን መካከል ዊልሰን ኪፕሰንግ 2፡03.58 ሰዓት የርቀቱ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ጌዲዮን ኪፕኪተር 2፡05.51 ሁለተኛና ዲክሰን ቹምባ 2፡06.42 ሦስተኛ በመሆን ለውድድሩ የተዘጋጀውን የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ጠራርገው መውሰዳቸው የአይኤኤኤፍ ድረ ገጽ ዘገባ አመልክቷል፡፡