Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልፕሮፌሰር ሉሌ መልአኩ (1925 - 2009)

ፕሮፌሰር ሉሌ መልአኩ (1925 – 2009)

ቀን:

በከፍተኛ ትምህርት መስክ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በቅድስት ሥላሴና በቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጆች በመምህርነትና በጥናትና ምርምር ዘርፍ ለአምስት አሠርታት አገልግለዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሉሌ መልአኩ፡፡

በመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ዘመን (1923-1967) ታዳጊዎችና ወጣቶች በሥነምግባር የታነፁ፣ በግብረገብ የተቀረፁ ሆነው እንዲያድጉ፣ በአስተዋይ ኅሊና በትሁት ሰብዕና የተሟሉ እንዲሆኑ በተደረገው ሀገራዊ ንቅናቄ ውስጥ ከተሳተፉት አንዱ ፕሮፌሰር ሉሌ ነበሩ፡፡ ለተማሪዎችና በጎ ፈቃዱ ላላቸው ሁሉ ‹‹አጭር የግብረገብነት ትምህርት›› የተሰኘ የብዕር ትሩፋታቸውን አበርክተዋል፡፡

በማስተማርና በምርምር ሥራ የ50 ዓመታት አገልግሎታቸው ከታሪክ፣ ከሥነ ምግባርና ከባህል ጋር የተያያዙ ስምንት መጻሕፍት በአማርኛና በእንግሊዝኛ አዘጋጅተው በማሳተም ዕውቀትና ልምድን ለትውልዱ ለማስተላለፍ ችለዋል፡፡

በተለይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር በነበረው የቅድስት ሥላሴ ቲዎሎጂካል ፋኩልቲ ከ1957 እስከ 1969 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ሥነ ምግባርና የነገረ መለኮት አስተማሪነታቸው ይታወሳሉ፡፡ የቲዎሎጂካል ፋኩልቲው ከተዘጋ በኋላ በዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ዘርፍ በርካታ ጥናቶችን ማከናወናቸው ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቲዎሎጂካል ሴሚናሪ (ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት) በ1980 ዓ.ም. በመዛወር ለአምስት ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ በቀድሞ መንግሥት የተዘጋውና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር የነበረው ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዳግም በ1984 ዓ.ም. ሲከፈት በጡረታ እስከተገለሉበት 2006 ዓ.ም. ድረስ አስተምረዋል፡፡

የኅትመት ብርሃን ካገኙት መጽሐፎቻቸው መካከል የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የጥንት፣ የመካከለኛና የአሁን ዘመን ታሪክ፣ የቤተክህነትና የቤተመንግሥት ግንኙነትን ጨምሮ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ያዘጋጇቸው አራቱ መጻሕፍት ይጠቀሳሉ፡፡

ከአባታቸው ከሊቀ ጠበብት መልአኩ ትርፌና ከእናታቸው ከወ/ሮ ስመኝ ዓለሙ በቀድሞ አጠራር በጎጃም ጠቅላይ ግዛት፣ በደብረ ማርቆስ አውራጃ፣ በማቻከል ወረዳ፣ በዐማኑኤል ከተማ የተወለዱት ፕሮፌሰር ሉሌ መልአኩ፣ በአዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ቤት ትውፊታዊውን የአብነት ትምህርት ተከታትለዋል፡፡

ዘመናዊ ትምህርታቸውን በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ በግሪክ ሐልኪ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ በአሜሪካ ሚዙሪ ስቴት ኤድን ቴዎሎጂካል ሴሚናሪ በሥነ መለኮት የማስትሬት ዲግሪአቸውን ተቀብለዋል፡፡ በደረሰባቸው ድንገተኛ አደጋ ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው የካቲት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በ84 ዓመታቸው ያረፉት ፕሮፌሰር ሉሌ ሥርዓተ ቀብር የካቲት 17 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡

ዘመናቸውን ሙሉ በባሕታዊነት የኖሩት ፕሮፌሰር ሉሌ፣ በዋጋ የማይተመኑትን የጥንትና የቅርብ ዘመን መጽሐፎቻቸውን  ለትውልድ ዕውቀት በረከት እንደሚሰጡ ባላቸው እምነትና ባክነው እንዳይቀሩ በማሰብ ለተማሩበትና ለረዥም ዓመታት ላስተማሩበት ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ማበርከታቸው ታውቋል፡፡  

በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ የተገኙት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በሰጡት ምስክርነት፣ ‹‹ገበሬ የተለያየ እህል ዘርቶ ዓለምን እንደሚመግበው፣ ፕሮፌሰር ሉሌ መልአኩም፣ እንደ እውነተኛ የዕውቀት ገበሬ ሆነው በሰዎች ጭንቅላት የዘሩት ሁሉ፣ በመንፈሳዊውም በዓለማዊውም የአገልግሎትና የሥራ መስኮች በርካታ ሞያተኞችን፣ ምሁራንና የሥራ መሪዎችን አፍርተዋል፤›› ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...