Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልስለ ዓድዋ. . .

ስለ ዓድዋ. . .

ቀን:

የዓድዋ ድል 121ኛውን በዓል ለማክበር መንግሥታዊና የግል ተቋማትም መሰናዶ የጀመሩት ባለፉት ሳምንታት ነበር፡፡ በየዓመቱ ድሉን ለመዘከር ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች የሚያዘጋጁ ሰዎች በበዓሉ ቀንና ቀደም ብለውም መሰናዷቸውን ለሕዝብ እነሆ ይላሉ፡፡ ዓድዋን በማስታከክ የሚሰናዱ ዝግጅቶች ታሪክን በመመርኮዝ ወደ ጦርነቱ ከተገባበት ወቅት ጀምሮ በጦርነቱ ወቅትና ከድሉ በኋላም ያለውን ሁኔታ የሚያትቱ ናቸው፡፡ ድሉ ሲዘከር ዓድዋ ከተለያዩ ጉዳዮች አንፃር የሚተነተንባቸው ጥናቶችም ይቀርባሉ፡፡

ለዘንድሮው የዓድዋ ድል መታሰቢያ የተዘጋጁ መርሐ ግብሮች ድሉን በኪነ ጥበብ የሚዘክሩና ታሪኩን በስፋት የሚዳስሱም ነበሩ፡፡ ከዝግጅቶቹ መካከል ነባራዊውን የአገሪቱ ገጽታ ከግምት በማስግባት የዛሬው ትውልድ የሚገኝበትን ሁኔታ የሚያጠይቅ ይዘት ያላቸው ይገኙበታል፡፡ ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝብ ነው ከሚል አንድምታ በመነሳት፣ ድሉ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ ጭቁን ሕዝቦች ለነፃነታቸው እንዲታገሉ በማነሳሳት ስላበረከተው አስተዋጽኦም ተወስቷል፡፡

ሪፖርተር ከተከታተላቸው መርሐ ግብሮች መካከል በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ጥምረት የተዘጋጀው እንዲሁም በሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴመንት የተሰናዳው ይገኙበታል፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በዓሉን የተመለከተ ሙዚቃዊ ድራማ፣ ኮንሰርት፣ የሥዕል ዐውደ ርዕይና ሌሎችም ዝግጅቶች አሰናድቷል፡፡ ሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴመንት የደም ልገሳ፣ የሙዚየም ቴአትር፣ የጎዳና ትርኢት፣ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚስተናገዱበት መርሐ ግብርና ሌላም አዘጋጅቷል፡፡

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች የተውጣጡ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ግለሰቦች የታደሙት ዐውደ ጥናት የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደው በጣይቱ ሆቴል ነበር፡፡ የዓድዋ ድል በዓለም አቀፍ መድረክ ስለሚሰጠው ቦታና ከድሉ በስተጀርባ ስለነበረው የሕዝቦች ትብብር ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡ አቶ ግርማይ ኃለፎም በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ሲሆኑ፣ ‹‹ዓለም አቀፋዊ የዓድዋ ድልና ታሪካዊ እሴቶቹ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፣ የዓድዋ ድል ጥቁሮች ነጮችን ሊያሸንፉ አይችሉም የሚለውን የተሳሳተ ምልከታ በመሻር ታላቅ ቦታ እንደሚሰጠው ተመልክቷል፡፡

አውሮፓን ማዕከል ያደረገ (ዩሮሴንትሪክ) አመለካከትን በመስበር ረገድ ዓድዋ ግንባር ቀደም ድል መሆኑን ገልጸው፣ በዋነኛነት በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ አፍሪካውያንና በሌሎች አህጉሮችም በጭቆና ውስጥ ለነበሩ ሕዝቦች የተስፋ ጭላንጭል ያሳየ ድል መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ የዓድዋ ድልን ተምሳሌት በማድረግ በዓለም ላይ የነፃነት ትግሎች መፋፋማቸውን የሚናገሩት መምህሩ፣ ድሉ ለአገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ እውነታ ያበረከተውን አስተዋጽኦም ጠቅሰዋል፡፡ ድሉ የአገር ፍቅር ስሜትና አንድነትን በማጠናከር፣ የዘመናዊንት መስፋፋት መነሻ በመሆንና አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር እንዲኖራት አስችሏል፡፡

ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄና አሁንም በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን አህጉራዊ ትስስር በማጥበቅ ረገድ ድሉ መሠረት መጣሉን ያክላሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የዓድዋ ድል ነፃነትን ለመቀዳጀት የተደረጉ እንቅስቃሴዎችን በማነሳሳት ካሳደረው አዎንታዊ ተፅዕኖ አንፃር የሚገባውን በዓለም አቀፍ ደረጃ አግኝቷል ወይ? የሚል ጥያቄ የሚሰነዝሩ አሉ፡፡ በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሚሰጠው ቦታ ከመነሳቱ በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ የአሁኑ ትውልድ ምን ያህል ያከብረዋል? የሚለውም ተያይዞ ይነሳል፡፡ ውይይቱን የታደሙ ግለሰቦች ከሰነዘሯቸው ጥያቄዎች መካከልም የአሁኑ ትልውድ ስለ ዓድዋ ምን ያህል ግንዛቤ አለው? የሚለው ይገኝበታል፡፡

ለአገሪቱ ነፃነት የተዋደቁ አርበኞች ድሉን ቢያስገኙም፣ ትውልዱ በገዛ ፈቃዱ በህሊናው ቅኝ ተገዥ እየሆነ ነው የሚል አስተያየትም ተደምጧል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን የሚወራላቸው ጀግኖች የኢትዮጵያ ሳይሆኑ የሌሎች አገሮች ናቸው የሚል ትችትም ቀርቧል፡፡ ተመሳሳይ ሐሳቦች እንደ ዓድዋ ድል ባሉ አገር አቀፍ በዓሎች ላይ በብዛት ቢደመጡም፣ የብዙዎች የዘወትር ጥያቄ ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡ ከዐውደ ጥናቱ ተካፋዮች አንዳንዶቹ ዓድዋን የተመለከቱ ጥናትና ምርምሮች ከማዘጋጀት ባሻገር፣ ድሉን የሚዳስሱ የኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ለወጣቱ ትውልድ መቅረብ አለባቸው የሚል የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም ዓድዋ አካባቢ ድሉን የሚዘክር አንዳች ቋሚ ነገር መሠራት እንዳለበት ያሳሰቡም ነበሩ፡፡

በውይይት መድረኩ ‹‹የዓድዋ ዘመቻና የኢትዮጵያውያን አንድነትና ትብብር መገለጫዎች፤›› በሚል ጥናት ያቀረቡት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር አቶ ዳንኤል ወርቁ ያተኮሩት በጦርነቱ ወቅት በሕዝቡ መካከል ስለነበረው ትብብርና ሴቶችና ገበሬዎች በጦርነቱ ባይዋጉም ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊነት የነበራቸው ወንዶች ላይ ነው፡፡ በመምህሩ ገለጻ፣ ከዓድዋ በፊት በነበሩ ጦርነቶች ከነበረው የላቀ ትብብር በዓድዋ ታይቷል፡፡ እርስ በርስ የሚፎካከሩ ሹማምንት በዓድዋ ጦርነት በአንድነት መሠለፋቸውን የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ ጣልያን አገሪቱን ከፋፍሎ ለመግዛት የነበረው ውጥን የከሸፈው በአንድነቱ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ስለ ዓድዋ ሲነሳ ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸው ነገር ግን ድሉ ዕውን እንዲሆን ቀላል የማይባል ሚና የተጫወቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሚናቸው በጉልህ ካልተነገረላቸው መካከል ሴቶች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ በአጥኚው ገለጻ፣ ወደ 30,000 የሚደርሱ ሴቶች በጦርነቱ የተሳተፉ ሲሆን፣ ምግብና መጠጥ በማቅረብ፣ የቆሰሉ ዘማቾችን በማከምና በአዝማሪነት ሞራል በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በተመሳሳይ በጦርነቱ ወቅት መሣሪያ ይዘው ባይዋጉም በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ ወንዶች በርካታ ናቸው፡፡ በጦርነቱ ወቅት መጓጓዣ በቅሎ በማቅረብ፣ የጦር ሠራዊቱ የሚያርፍበትን ድንኳን በመትከልና መገልገያዎችን ከቦታ ቦታ በማጓጓዝ ተሳትፈዋል፡፡ አርሶ አደሮችም ቀለብ ከማቅረብ ጀምሮ በተለያየ መንገድ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

የዓድዋ ድልን ምክንያት በማድረግ ከተዘጋጁ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶች መካከል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የቀረበው ‹‹የጥቁር ሕዝቦች መልህቅ›› የተሰኘ ሙዚቃዊ ድራማ ይጠቀሳል፡፡ የካቲት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. የታየው ሙዚቃዊ ድራማ በተስፋዬ ሽመልስ ተጽፎ በራሔል ተሾመ የተዘጋጀ ነው፡፡ የድራማው መቼት አንድ ልቦለዳዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲሆን፣ የተለያዩ ክልሎችን የሚወክሉ ግለሰቦችን የወከሉ ተዋንያን ጥያቄ፣ መልስና የባህል ትርዒት ውድድር አካሂደዋል፡፡

በዕድሜ የገፉ አባቶችና እናቶች ተወዳዳሪዎቹን ለመዳኘት በቦታው ተገኝተው፣ ጥያቄዎቹን አስደምጠዋል፡፡ ድራማው የዓድዋ ልድን መነሻ በማድረግ የአሁኑ ትውልድ አገራዊ ግዴታዎቹን በመወጣት ረገድ ምን ያህል ተጉዟል? በሚለው ጉዳይ ያተኮረ ሲሆን፣ የየክልሉ ተወካዮች የቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን የሚፈትሹ ናቸው፡፡ የዓድዋ ድል አድራጊነት መንፈስ በትውልዱ ስለመስረፁ ለቀረበው ጥያቄ ተወካዮቹ አወንታዊ ምላሽ ነበራቸው፡፡ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ሁሉም በአንድነት እየሠራ መሆኑን በመግለጽ፣ አገሪቱ ብሩህ ተስፋ እንዳላት አመልክተዋል፡፡ ምላሻቸው የተለያዩ አካባቢዎችን ባህል በሚያንፀባርቅ ሙዚቃና ውዝዋዜ የታጀበም ነበር፡፡ የድማራው መደምደሚያ በሆነው የዳኝነት ውሳኔ መሠረት ሁሉም ተወዳዳሪዎች አጥጋቢ ምላሽ በማቅረባቸው አሸናፊዎች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

የዓድዋ ድል ሲዘከር ታሪኩን ከማውሳት ጎን ለጎን የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታም የመዳሰስ አዝማሚያ የታየባቸው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዝግጅቶች፣ በትናንትናና በዛሬ መካከል አንዳች ድልድይ ለመዘርጋት የታለመባቸው መሆናቸውን መረዳት ይቻላል፡፡ በጥናታዊ ጽሑፍ፣ በሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በፎቶግራፍ፣ በሥዕልና በሌሎችም መንገዶች ዓድዋን የሚዘክሩ መርሐ ግብሮች ተደራሽነት ምን ያህል ነው? የሚለውን መጠየቅ ግን ያሻል፡፡ የመርሐ ግብሮቹን ታዳሚ ከማስፋት አንፃር ብቻ ሳይሆን መልዕክቱን በአግባቡ ከማስተላለፍ ረገድም መታየት አለበት፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሒሩት ወልደማርያም እንደተናገሩት፣ የዓድዋ ድል አገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ እንድትገኝ መሠረት የጣለ በመሆኑ ወጣቱ ለአከባበሩ ትኩረት ሊቸረው ይገባል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በበለጠ ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ያስመዘገበችው በዓድዋ ምክንያት ባህል፣ ቅርስና ቋንቋ ስለተጠበቀ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለዜጎች ማንነት መከበር ምክንያት የሆነውን ድል በተገቢው ሁኔታ መዘከር ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...