Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበባራክ ኦባማ ላይ ፊታቸውን ያዞሩት ዶናልድ ትራምፕ

በባራክ ኦባማ ላይ ፊታቸውን ያዞሩት ዶናልድ ትራምፕ

ቀን:

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን በያዙ በአምስተኛ ሳምንታቸው የመጀመሪያውን ንግግር ለኮንግረሱ ማክሰኞ አቅርበዋል፡፡ በአወዛጋቢ ንግግሮቻቸውና ዓለምን ባስደመሙ ውሳኔዎቻቸው የሚታወቁት ትራምፕ፣ በኮንግረሱ ፊት ከሥልጣን በኋላ የመጀመሪያ ንግግራቸውን ከማድረጋቸው አስቀድሞ፣ ከፎክስ ቴሌቪዥን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር፡፡

ሰዎችን ለመውቀስ፣ ለማጣጣልና ጥፋተኛ ለማለት ምንም የማይገዳደሩት ትራምፕ፣ ከፎክስ ጋር በነበራቸውም ቆይታ ተሰናባቹን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ‹‹በእኔ ላይ ከተነሱ አመፆች ጀርባ አሉ፤›› ብለዋቸዋል፡፡

ኦባማንና በደፈናው ‹‹የኦባማ ሰዎች›› ያሏቸውን በመጥቀስም ሥልጣን ከተረከቡባቸው፣ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በትራምፕ ላይ ለተነሱ ተቃውሞዎች አቀናባሪው ኦባማ ናቸው ብለዋል፡፡

ትራምፕ የአገሪቱን ደኅንነት ሥጋት ላይ ይጥላሉ ያሏቸውን የሰባት አገሮች ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የዕግድ ትዕዛዝ ባስተላለፉበት ቅፅበት በአሜሪካ ኤርፖርቶችን ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች ብዙዎች ለተቃውሞ ወጥተው ነበር፡፡ ትራምፕ ይህንን ቀጥታ ያዛመዱት ከኦባማ ጋር ነው፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ፣ ትራምፕ ያለምንም ማስረጃ፣ ‹‹ኦባማ በእኔ ላይ የተደረጉ ተቃውሞዎችን ከጀርባ ሆነው አቀነባብረዋል፤›› ብለዋል፡፡

ከአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ጀምሮ በአገሪቱ ሚዲያዎች ላይ ትችትን የሚሰነዝሩትና ተዓማኒ አይደሉም በማለት የሚኮንኑት ትራምፕ፣ ሥልጣን ከያዙ በኋላም ከሚዲያው ጋር ያላቸው ግንኙነት የሻከረ ነው፡፡ የዘር ጥላቻን በሚያነግሡ ንግግሮቻቸው በሚዲያው በተደጋጋሚ የሚተቹና በፖለቲካ ተንታኞች የሚወቀሱ ሲሆኑ፣ ለዚህም ኦባማና የኦባማ ወዳጆች ከኋላ ሆነው የአገሪቱ ሚዲያዎች ከዋይት ሐውስ ፕሬስ መረጃ እንዲያገኙ ስለሚያደርጉ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ከመጋረጃ ጀርባ በእርግጠኝነት ምን እየተካሄደ እንደሆነ ማወቅ አይቻልም፡፡ እንደማስበው ኦባማ ከጀርባ አሉ፡፡ ምክንያቱም የእሳቸው ሰዎች ከሁሉም ነገር ኋላ አሉ፤›› ያሉት ትራምፕ፣ በቅርቡ ሪፐብሊካኖች በነበራቸው ስብሰባ ላይ ብዙ ሰዎች ያሰሙት ከነበረው ሁከትና ማጉረምረም ጀርባ ኦባማ አሉ ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ኦባማ በትራምፕ ላይ በሚሰነዘሩ ወቀሳዎችና ትችቶች እንዲሁም ተቃውሞዎች ጀርባ እንዳሉ፣ ይህም ፖለቲካ እንደሆነና የፖለቲካም ባህሪ ከዚህ ያልተለየ መሆኑን ትራምፕ ሲናገሩ፣ ሪፐብሊካንና የሪፐብሊካን አቀንቃኝ ሚዲያዎች ደግሞ ኦባማ ‹‹ኦርጋናይዚንግ ፎር አክሽን›› (ኦኤፍኤ) የተባለውን ቡድን አቅጣጫ ይሰጣሉ ሲሉ አብጠልጥለዋቸዋል፡፡

ኦባማ እ.ኤ.አ. በ2012 ለዳግም ምርጫ ሲወዳደሩ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ መሪ፣ እንዲሁም በመጀመሪያው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የዋይት ሐውስ ምክትል ኃላፊ በነበሩት ጂም መሲና የሚመራው ኦኤፍኤ፣ ለትርፍ ያልቆመና ማንኛውንም የፖለቲካ ዕጩ እንደማይደግፍ ሚዲያዎች አስፍረዋል፡፡ ሆኖም ድርጅቱ ያደገው ኦባማ ለመጀመሪያው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ሲወዳደሩ እሳቸውን ይደግፉ በነበሩ ቡድኖች ነው፡፡ ብዙዎቹ የድርጅቱ አጀንዳዎችም ከዴሞክራቲክ ፓርቲና ከኦባማ ቁልፍ የፖሊሲ አቋሞች ጋር የተዛመዱ ናቸው፡፡ ኦባማ ግን ከዚህ ቡድን ጋር በግላቸው ግንኙነት ስለመፍጠራቸው የተገኘ ማስረጃ የለም፡፡ ትራምፕ ግን በኦባማ ላይ ጣታቸውን ከመቀሰር አልተቆጠቡም፡፡

በአሜሪካ ታሪክ ሥልጣን ያስረከቡ ፕሬዚዳንቶች በእግራቸው የተተካውን ፕሬዚዳንት የማይተቹ ቢሆንም፣ ኦባማ ትራምፕ ሥልጣን በያዙ በጥቂት ቀናት ውስጥ ትራምፕ ጥለውት የነበረውን የጉዝ ገደብ ተቃውመዋል፡፡ ‹‹ሰዎች በእምነታቸው ምክንያት መገለላቸውን ከመሠረቱ እቃወማለሁ፤›› ማለታቸውም በወቅቱ በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡

ትራምፕ ጉዳዩን ‹‹ፖለቲካዊ›› ነው ይሉታል፡፡ በተለይ ከዋይት ሐውስ አፈትልከው አሜሪካን አደጋ ላይ ይጥሏታል የተባሉ የደኅንነት መረጃዎች እንዲሾልኩ በማድረግ የኦባማ ቡድን የሚሉትን ወንጅለዋል፡፡

ለኮንግረሱ ንግግራቸውን ከማድረጋቸው አንድ ቀን አስቀድሞ ኦባማን ‹‹የተቃውሞዎች ህቡዕ አቀናባሪ›› ያሉት ትራምፕ፣ ለኅትመት እስከገባንበት ማክሰኞ ምሽት ድረስ ለኮንግረሱ ንግግራቸውን ባያሰሙም፣ ሲኤንኤን አስቀድሞ ይዞት በወጣው ዘገባ ትራምፕ አዲስ ነገር ይዘው ብቅ አይሉም ብሏል፡፡

ከምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ጀምሮ አሜሪካን ከንግድ ስምምነቶች ማስወጣት፣ ስደተኞች ለተወሰነ ጊዜ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ማድረግ፣ ኦባማ ኬር የተባለውን የሕክምና ኢንሹራንስ ሥርዓት መለወጥ፣ ለሌሎች አገሮች የሚሰጡ የገንዘብ ዕርዳታዎችን መቀነስ፣ አሜሪካን ከኔቶ አባልነት ማስወጣትና ሌሎችንም አጀንዳዎች ሲያነሱ የቆዩት ትራምፕ፣ ሥልጣን ከያዙ ማግሥት ጀምሮ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ከተናገሩት ዋና ዋና የሚባሉትን ፈጽመዋል፡፡

‹‹በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ትልልቅ ጉዳዮችን ለመፈጸም ቃል ገብተዋል፡፡ ከእነዚህም የተወሰኑትን ሥልጣን በተረከበ በአምስት ሳምንታት ውስጥ ፈጽመዋል፤›› ያለው ዘገባው፣ ለአብነትም አሜሪካ ከትራንስ ፓስፊክ ፓርትነርሽፕ የንግድ ስምምነት መነጠሏንና ለጊዜው የታገደ ቢሆንም የሰባት አገሮች ዜጎች አሜሪካ እንዳይገቡ ማገዳቸውን አውስቷል፡፡

ትራምፕ ከመንግሥት ተቋማት በጀት 54 ቢሊዮን ዶላር ለመቀነስ ማቀዳቸውና እ.ኤ.አ. ለ2018 የአሜሪካ መከላከያ ኃይል አሥር በመቶ የበጀት ጭማሪ በማድረግ 54 ቢሊዮን ዶላር ለማድረግ ማቀዳቸውም ይፋ ሆኗል፡፡ ከትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ባለቤቶችና ሥራ አስኪያጆች ጋርም መክረዋል፡፡

በእነዚህ ጊዜያት ባደረጓቸው ንግግሮችና ባሳለፏቸው ውሳኔዎች ሚዲያዎችን ጨምሮ በፖለቲካ ተንታኞችና በመብት ተሟጋቾች የተተቹትና ተቃውሞ የበረታባቸው ትራምፕ፣ በኮንግረሱ ፊት አዲስ ነገር ይዘው መቅረብ አይችሉም፣ ቀድሞውንም ከተናገሩት ዋናዎቹን አድርገዋል የሚል አስተያየትም እየተሰነዘረ ነው፡፡

በኮንግረሱ የሚያደርጉት ንግግር ቀጥታ አገሪቷን የሚመለከቱና የተደቀኑ ችግሮችን የሚፈቱ ሊሆኑ ይገባል የሚሉ አስተያየቶችም ተሰምተዋል፡፡ ትራምፕ በንግግራቸው ያጎደፉአቸውን፣ በድርጊታቸው ያጠፏቸውን በማስታወስም፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱ በኮንግረሱ በሚኖራቸው ንግግር የፖለቲካ ጊዜ ለመግዛት ሊጠቀሙበት ይገባል፤›› ያሉም አሉ፡፡

ትራምፕ ባሳለፉት አምስት ሳምንታት የፕሬዚዳንትነት ቆይታ፣ በአሜሪካ ዘመናዊ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሠሯቸው ሥራዎች ተቃውሞ በዝቶባቸዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ 100 የሥራ ቀናት ለአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ልዩ ቦታ የሚሰጠው፣ ሕዝቡና ሚዲያውም ፕሬዚዳንቱን የሚያይበት ነው፡፡ ትራምፕ የተመዘኑትና የተተቹት ደግሞ ገና ከምርጫ ዘመቻ ጀምሮ ነው፡፡ እንደ ኤንቢሲ/ዎል ስትሪት ጆርናል የሕዝብ አስተያየት ከሆነ፣ ትራምፕ በአምስት ሳምንቱ የሥራ ቆይታቸው አብዛኛውን ማስደሰት አልቻሉም፡፡ 48 በመቶ የሚሆኑ የሕዝብ አስተያየት ተሳታፊዎች የትራምፕን ሥራ ሲቃወሙ፣ 44 በመቶው ደግሞ የትራምፕን አካሄድ ደግፈዋል፡፡

ሲኤንኤን፣ አሉታዊ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ አድርገው ከማሸነፍ አንስቶ በአከራካሪ ንግግሮቻቸው ይታወቃሉ የሚላቸው ትራምፕ፣ ምን አዲስ ነገር ይዘው ብቅ ይሉ ይሆን? የሚለው የወቅቱ የመነጋገሪያ ርዕስ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...