Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እኮ እንዴት እንራመድ?

እነሆ መንገድ። ከሳሪስ አቦ ወደ ቦሌ ድልድይ ልንጓዝ ተሳፍረናል። ሰው በሰው ላይ እንደጥልፍ ጥለት ተደራርቦ ይተፋፈጋል። ቅብጥብጡ ወያላ፣ ‹‹አንድ ሰው አንድ ሰው…›› እያለ ሲጮህ ዕቃ እንጂ ሰው የሚጭን አይመስለውም። ‹‹ምናለበት ብንሄድ?›› ይሉታል እንደ መከዳ የሚደገፋት ወንበር ላይ ስብር ብለው የተሰየሙ ወይዘሮ። ‹‹እንሄዳለን አንድ ሰው ብቻ፤›› ይላቸዋል። ‹‹እንዲያው በሁዳዴ እንኳ ብትታዘዙን ምን አለ?›› አጉተመተሙ። ሾፌሩ ሰምቶ ተጠምዞ አይቶአቸው፣ ‹‹ምነው እማማ ንክኪ ሲበዛ ማስገደፍ ጀመረ እንዴ?›› አላቸው። ‹‹ሥጋ፣ ሥጋ ነው። ያው በለው…›› አሉት። ‹‹በለው? ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ በዚህ መጣችሁበን። ኧረ ሠርተን እንብላበት›› ተገላመጠ። ‹‹አንተው አመጣኸው አንተው አሮጥከው። እንጂ እኔ ምን አልኩህ። ደግሞ ግልምጫህ? አንተ እንዲያው ሌላው ቢቀር ሁለቴ አልወልድህም? ደግሞ ሠርተን እንብላበት ይለኛል? ሥራችሁማ ይኼው። የዘመኑ ልጆች በሥራ እያመካኛችሁ ሽቅብ ማንጓጠጥ ነው። ለነገሩ እናንተ ምን ታደርጉ? ድፍረትና ንቀታችሁን በገንዘብ የሚተምንላችሁ ሰው ቢበዛም አይደል?›› ሲሉት፣ ‹‹ምን አጨቃጨቀኝ…›› እያለ አንደኛ ማርሽ አስገባ።

ወያላው ‹‹ቆይ እንጂ ይሙላ፤›› አለው ሥለት በአንጀቱ እንደተሰነቀረበት ሁሉ ገርጥቶ። ይኼኔ ከወይዘሮዋ ጎን የተሰየመ ወጣት አንድ ሁለት ብሎ ሁላችንንም ቆጥሮ ሲያበቃ፣ ‹‹አስራ ሰባት ሰው ጭነህ ነው ይሙላ የምትለው?›› አለው። ወያለው አንገቱን ደፍቶ ስድብ እያጉተመተመ ተንሸራታቹን በር ከረቸመው። ‹‹የዘንድሮ ወያላና መራጭ መቼ ወንበር ይቆጥራል ልጄ? ሥጋ ወዳጅ ሁሉ። ስግብግብነት እኮ እንኳን ሰው ተራራ ካይንህ አያስገባም። የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል እምነት የማጣታችን ጫፍ መስሎኝ ወስዶ ወስዶ እኛኑ ራሳችንን እንደ ግዑዝ ዕቃ ያለማስተዋል በጎታ መሥፈርት የሚሰፍረን፤›› ሲሉት ወይዘሮዋ ወጣቱ አማርኛቸው ቻይንኛ ሆኖበት ለይምሰል አንገቱን ይወዘውዛል። መንገዱ እኮ ባቢሎን ከሆነ ከራርሟል!

እየተጓዝን ነው። ይህ ዕረፍት የሚሳነው ጎዳና እፎይታ የከዳው መንገድ፣ እያንከለከለን ሳናስበው ከተገኘንበት አቅጣጫ አስበን የምንደርስበት ወደ መሰለን መስመር ይወስደናል። ለምሳሌ ሦስተኛው መቀመጫ ላይ የተሰየመ አንድ ለአገሩ እንግዳ የሆነ ባይተዋር ፈረንጅ ከወያላው ጋር ይጨቃጨቃል። ‹‹ቦሌ ስል እየሰማ ገብቶ ሚካኤል ይለኛል? አንደኛህን የአገርህን ታክሲ ይዘህ አትመጣም ከመጀመሪያው? ምን ዓይነት ነገር ነው እባካችሁ? ፈረንጅም ደንቁሮ ማደናቆር ያውቃል ለካ!›› ይላል ወያላው ተማሮ። ‹‹ከቻልክ በተለይ መጨረሻ ላይ ያልካትን ወደ እንግሊዝኛ ተርጉመህ ለራሱ መንገር ነው። አለዚያ ዝም ነው…›› ይላል ሾፌሩ እየሳቀ። ‹‹ሰላይ ሊሆን ይችላል አደራ እንዳታስበላን ከአፍህ ምንም አይውጣ…›› መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት ወጣቶች አንዲት ፍልቅልቅ ወያላውን አውቃ ታስቦካው ጀመር።

‹‹ከተበላንማ ቆየን…›› ጋቢና ያለው ነው ይኼን የሚለው። ‹‹ሰላይ?!›› አዛውንቷ ፈረንጁን አፍጥጠው እያዩ ቃሉን ደጋገሙ። ፈረንጁ አጠገቡ ወደ ተቀመጠችው ተሳፋሪ ዞሮ “what’s going on?” ይላል። ከእንግሊዝኛ ይሁን ከነገር ሽሽት ማንም የሚመልስለት ሰው ጠፋ። ያቺ ነገረኛ ፍልቅልቅ ሆነ ብላ ያስነሳቸው የጥርጣሬ ወሬ በአንዴ ታምኖ ዋና መነጋገሪያ ርዕስ ሆነ። ‹‹ምን ይታወቃል ትራምፕ አዲስ አበባ ሊመጡ ጥቂት ቀን ነው የቀራቸው። እስኪ የመንገዱንም የሰውንም አካሄድና አጠማዘዝ ቃኘው ብለው ልከውት ይሆናል፤›› ሲል አንዱ፣ ‹‹ታዲያ ሠልፍ በሠልፍ እንደሆንን ለምን አሁኑኑ አንድ ላይ ተባብረን አናስረዳውም? እ? ጎበዝ! በቢሮክራሲና በዴሞክራሲ ሠልፍ፣ በትራንስፖርት ዕጦት ሠልፍ፣ በመኖሪያ ቤት ዕጦት ሠልፍ… እንዲያው በሁሉ ነገር ሠልፍ ላይ መሆናችንን ነግረነው ይናገርልን?›› ይላል ሌላው። ፈረንጁ አንዴ ወደ ተናጋሪው አንዴ ወደ አድማጩ እያማተረ ተደናግጦ ተቀምጧል። መቼም በገዛ አገራችን ተሳቀን የሰው አገር ሰው ስናሳቅቅ የሚደርስብን ያለ አንመስልም። ወይ እንግዳ ተቀባይነት!

ጉዟችን ቀጥሏል።  ጋቢና ከተሰየሙት አንዱ በስልክ ይነታረካል። ‹‹ስማ ስልኩ እኮ የሚሠራው በካርድ ነው ፍሬ ፍሬውን አውራ፤›› ይላል። እንኳን ስልኩ ሰውም በካርድ መሥራት ጀምሯል ኧረ…›› ይላል ከመጨረሻዎቹ በዚያ ጥግ የተቀመጠው። ‹‹ታዲያ ካርድ መሙላት ያቃተው አለቀለት በለኛ?›› ስትል ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ዘመናይ ከሩቅ ቅርብ ሆና ማይኩን ተቀበለችው። ‹‹ለስንቱ ይሆን ከሆዳችን ቀንሰን ካርድ እየሞላን የምንዘልቀው? ያም አምጡ ይኼም አምጡ ባይ ሆኗል፤›› ይላል ከጎኗ የተቀመጠ ቀጠን ያለ ወጣት። ‹‹ሁሉም አጉርሱኝ ባይ ሆነ ብሎ ዝም ምንድነው ልጄ? ሁሉም ካልክ ዘንዳ አንተንም ጨምርና ንስሐ ግባ፤›› አሉት ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየሙት ቄስ። ‹‹አይ አባት ጣት መቀሳሰሩን ትተን ሸክማችንን በጋራ መሸከም ብናውቅ እስከ ዛሬ እርስ በርስ በዓይነ ቁራኛ ስንተያይ እንኖር ነበር?›› ቢላቸው ከሰውነቱ ወይ  ከኑሮ ማንኛው እንደ ከበደው ያላወቅንለት ወጣት መልሰው፣ ‹‹እሱስ ልክ ነህ ልጄ። ምን ይደረግ የአንዱን ሥጋ አንዱ መሸከም እያቃተው እኮ ነው፤›› አሉት።

ነገር በፌስቡክ ብቻ የሚገባው ዝም ሲል ሌላው ሳቀ። ሼኩ በፈገግታ ጣልቃ ገብተው፣ ‹‹ይኼን ካወቅክ ዘንድ ሆድ አየሁ ማለትን እንደማያውቅ ከተረዳህ፣ ይኼ ሁሉ ስብ ምንድነው? ለሰማዩም ለምዱሩም እኮ አይበጅም። ኧረ ለጤናም ጥሩ አይደለም፤›› ሲሉት ወጣቱ ወዲያው የጨዋታውን መንፈስ ቀየረው። የሰውነቱ ውፍረት አገር እንደነቀዝ እየሰረሰ ከሚያፈርሰው ‘ብቻዬን ጠብድዬ ልሙት’ ብሂል ጋር መነካካቱ አናደደው መሰል ቁጣው በድምፁ ስርቅርቅታ መሀል አታሞ እየደለቀ፣ ‹‹መሆንን ትተን መምሰል፣ መምሰል ካልን አይቀር ምናለበት እኛስ ስብ ጠናባቸው ብንባል? ቀለን ተቀብረን ማን አከበረን?›› ብሎ አዋዝቶ የልቡን ተናገረ። ስንቱ ነው ግን የልቤን ልናገር እያለ ልቡን የሚያጣው እናንተ?!

ወያላችን ሒሳብ እየተቀበለ ነው። በሾፌሩ ትይዩ መስመር መጨረሻ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ጎልማሳ ስልክ ይዟል። ‹‹ይሰማሃል? እኔ ይሰማኛል። አንተ ይሰማሃል? ይሰማኛል… ይሰማኛል…›› ይላል እየደጋገመ። ‹‹ታዲያ ከተሰማው ወደ ገደለው አይገባም? ምን ጆሯችንን ያሰማዋል?›› ስትል ከሾፌሩ ጎን የተሰየመች ተሳፋሪ ደግሞ እኛ ድረስ ይሰማል። ሾፌሩ፣ ‹‹ምን ታደርጊዋለሽ። ባለመደማመጥ ያሳለፍነው ጊዜ ቀላል ስላልሆነ እኮ ነው። ድንገት ስትደማመጪና ኔትወርኩ ጥርት ሲል እንዴት ግራ አይገባሽ?›› አላት። ‹‹ግን  እንኳን ሰው የሚናገረውን ራሳችን የምናወራውን ሳይቀር እናዳምጣለን ብለህ ነው?›› ተግባብተዋል። ‹‹እሱ ላይ መጣሽ አየሽ። የአራዳ ልጅ የሚመቸኝ ለዚህ ነው። ለምሳሌ ሩቅ ሳትሄጂ የአስተዳዳሪውንና የአመራሩን ‘ፑትለካ’ ረስተሽ ከእኔ ብትጀምሪ፣ የምናገረውን የማዳምጠው ቀን የሠራሁትን ገንዘብ ማታ ስቆጥር ብቻ ነው። አስገባው እስኪ…›› ብሎ ታክሲዋን አቆማት።

ወያላው ከፍቶ ያስገባል። ጉዟችን ይቀጥላል። አጠገቤ የተቀመጡት አዛውንት ተሳፋሪው በሙሉ እየሰማቸው፣ ‹‹እኔ ምለው ግን የካቲት በጤናው ነው?›› ብለው ጠየቁ። ያ ፌዘኛ ወጣት ይህቺን ያዘና ‹‹አድሟል ይላሉ፤›› አላቸው። ‹‹ምን አደረግነው ልጄ?›› ሲሉት አዛውንቱ፣ ‹‹ሰው በአገሩ እንደ ሰው በማይቆጠርበት፣ ማንም ጉልበተኛ ቀማኛ እየተነሳ ያሻውን በሚያግበሰብስበት፣ ለደካማ ተቆርቋሪ በታጣበት አገር አልዘንብም ነው አሉ የሚለው፤›› አለ ቧልተኛው የምሩን ለማስመሰል ተኮሰታትሮ። ‹‹ታዲያ እንዲያ ሲል ዝም አልከው? ወትሮም ከሰማይ እንጂ ከምድር ተረጥበን እንደማናውቅ አትነግረውም?›› ብለው አዛውንቱ ሳቁ። ‘አፄ ኃይለ ሥላሴ ካልመጡ እንዳመሌ አልጨልምም አለ’ አለማለቱም አንድ ነገር ነው ኧረ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ካርጎን እንዳለፍን መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት አንዱ፣ ‹‹ኧረ ፊኛዬ ሊፈነዳ ነው። ሾፌር አንዴ አቁመው እስኪ?›› አለ ያለምንተፍረት። አጠገቡ የተሰየመች ዓይነ አፋር፣ ‹‹እንዴ? ሼም የለም እንዴ ዘንድሮ?›› አለች አምልጧት። ‹‹በተፈጥሮ ሕግ የምን ሼም ነው? ሼም ካልሽ ራሳቸው ያወጡትን ሕግ መልሰው ራሳቸው የሚጥሱትን የሰው ልጆች ሼም አታስይዢም?›› ብሎ ተቆጣና ‹‹አቁመዋ?›› አለ ከመቀመጫው እየተነሳ። ወያላው ብሽቅ ብሎ ከኪሱ መጻፊያ አወጣና በነጭ መደብ የተፃፈ ሃይማኖታዊ ጥቅስ ሥር በችኮላ ‘ታክሲያችን ተንቀሳቃሽ መፀዳጃ አይደለም’ ብሎ ጻፈ። አዛውንቱ ቀበል አድርገው፣ ‹‹እንዴት ያለ ጉድ ነው? ቢቆምስ? መንገድ ላይ ልትለቀው ነው? ነውር አይደለም?›› ሲሉት፣ ‹‹መንገድ እንደ ፍራሽ፣ ድንጋይ እንደ ትራስ ተደግፎ መተኛት ነው የሚያሳፍረው? ወይስ መንገድ ላይ መተንፈስ?›› አላቸው።

‹‹ኧረ እንደማመጥ?›› ይላል ጎልማሳው። ‹‹በየት በኩል እንደማመጣለን? ሐሳባችንና ቋንቋችን እንደየፊናችን ተበታትኖ መግባባት አቅቶን አታይም? አንዱ ሲያለማ አንዱ ሲያፈርስ ሰበብ አያጣም። አንዱ ሲቆፍር ሌላው ሲምስ ይሉኝታ የለም፤›› ባይዋ ወይዘሮዋ ናቸው። በዚህ ሁሉ መሀል ሾፈራችን ታክሲያችን ክንፍ አስወጥቶ ያከንፋታል። ልክ ቦሌ ጫፍ ስንደርስ ጥግ አስያዛትና ‹‹ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም ይሉሃል ይኼ ነው። አሁን ከፈለጋችሁ ወርዳችሁ መደባደብ ትችላላችሁ፤›› አለን። ደግሞ ሾፈሩ ላይ ሌላ ሂስና ግለ ሂስ ተነሳ። በዚህ መሀል መጨረሻ ወንበር ተሰይሞ የነበረው በጥባጭ ሾልኮ ወርዶ በላሜራ የታጠረ ታዳጊ ችግኝ ላይ ከመብሉና ከውኃው የተጣራውን ቢጫ ፈሳሽ ያርከፈክፋል። ተናጋሪው ብዙ አድማጩ ጥቂት። እኮ እንዴት እንራመድ? መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት