Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለኢንቨስትመንት የተመቹ የለውጥ አሠራሮች ላይ መንግሥትና ተገልጋዮች ለየቅል ሆነዋል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም ከሚገኙ አገሮች ውስጥ 190 ያህሉን በማካተት በየዓመቱ ይፋ የሚደረገው የዓለም ባንክ ሪፖርት፣ በአገሮቹ መካከል ያለውን ምቹነትና ተስማሚነትን የሚለኩ አሥር ጠቋሚዎችን በመለየት ደረጃዎችን የሚያወጣው የዓለም ባንክ ‹‹ኤዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ›› የተሰኘው ታዋቂ ሪፖርት ለዓመታት ይፋ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ሪፖርቱ በአብዛኛው አገሮች ለንግድ አሠራርና ለኢንቨስትመንት መቀላጠፍ የሚከተሏቸውንና የሚያራምዷቸውን ሕጎች፣  የሚተገብሯቸውን አሠራሮች ወዘተ በመቃኘት ምቹ ስለመሆን አለመሆናቸው  በየዓመቱ ይፋ ያወጣል፡፡ በዚህ ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ከአብዛኞቹ አገሮች ግርጌ ስትቀመጥ ቆይታለች፡፡ አገሪቱ ከምትወቅስባቸው መካከል በምትከተላቸው ገዳቢ ሕጎች ሳቢያ ወደ ንግድ ሥራም ሆነ ኢንቨስትመንት ለመግባት በርካቶች እንደሚቸገሩ፣ በአገሪቱ የተንዛዛ ቢሮክራሲ፣ በውሳኔና በደካማ የአገልግሎት አሰጣጥ ሳቢያ በርካታ ኢንቨስተሮችም ሆኑ ነጋዴዎች እንደሚጉላሉ ሪፖርቱ ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡

የዓለም ባንክ በዋና ዋና መመዘኛ መስፈርትነት የሚጠቅሳቸው የሚከተሉት አሥር መለኪያዎች ናቸው፡፡ የንግድ ሥራ ለመጀመር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች፣ የግንባታ ፈቃድ በቀላሉ ለማግኘት መቻል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት፣ ንብረት ማስመዝገብ፣ ብድር ማግኘት መቻል፣ ለአነስተኛ ኢንቨስተሮች ከለላ መስጠት፣ የታክስ መክፈል መቻል፣ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ማካሄድ፣ የውል ስምምነቶችን መተግበር እንዲሁም የኪሳራ ዕወጃን ያለ ውጣውረድ መፍታት የሚሉ አሥር ዋና ዋና መለኪያዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ 190 ያህል አገሮች ደረጃ ይወጣላቸዋል፡፡

ሪፖርቱ ዓለም አቀፍ ተደራሽነትና ተቀባይነትን ያተረፈ፣ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችም ለእንቅስቃሴያቸው መመዘኛ ከሚያደርጓቸው ነጥቦች መካከል አንዱ በማድረግ የሚጠቅሱት ይህንኑ የዓለም ባንክ ሪፖርት ነው፡፡ የዚህ ዓመቱን የአገሮችን ደረጃ ይፋ ያደረገው የባንኩ ሪፖርት ኢትዮጵያ በ159ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮችም 31ኛዋ ሆናለች ያለው የዓለም ባንክ፣ አገሪቱ ከወትሮው ይልቅ 12 ነጥቦችን ወደ ታች በማሽቆልቆል ይብሱን ወደታች እንደወረደች አስፍሯል፡፡

በመሆኑም አገሪቱ በኢንቨስትመንት መስህብነት ከሌሎች አገሮች ጋር ለመወዳደር ካሻት ከታች እስከ ላይ መሠረታዊ የለውጥ ሪፎርሞችን መተግበር እንደሚጠበቅባት አሳስቧል፡፡ በዚህ ምክንያት ይመስላል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የአገሪቱን የአሠራር ማዕቀፎች ለማሻሻልና በባንኩ መለኪያ መሥፈርቶች መሠረት አገሪቱ የምታስመዘግባቸውን ዝቅተኛ ውጤቶች ለማሻሻል መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡

ከሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ይልቅ ለየት ባለ አደረጃጀትና የአመራር ኃይል መንቀሳቀስ የጀመረው ኮሚሽኑ፣ የተመቻቸ የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ ለመፍጠር የሚረዱትን የዓለም ባንክ መመዘኛዎችን በጥሩ ውጤት መተግበር የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ማድረግ ከጀመረ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡

በዚህ ዓመትም ሁለተኛውን ምዕራፍ የማሻሻያና የለውጥ እንቅስቃሴን የተመለከተ የምክክር መድረክ ሰሞኑን ጠርቶ ነበር፡፡ የካቲት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠራው መድረክም ከግንባታ ዘርፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አካላት ታድመው ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ከሥሩ መመዘኛዎች በስድስቱ ማለትም ንግድን ከታች ለመጀመር በሚያስችሉ አሠራሮች፣ በኮንስትራክሽን ፈቃድ አሰጣጥ፣ በንብረት ማስመዝገብ፣ በብድር አሰጣጥ፣ በድንበር ዘለል ንግድ እንዲሁም በታክስ አከፋፈል መስክ ያሉት መመዘኛዎች ላይ ቅድሚያ በመስጠት ለመንቀሳቀስ መነሳቱን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚሁ መሠረትም ውይይቱ ተካሂዷል፡፡

እነዚህ መመዘኛዎች ላይ ጥሩ የሚባለውን ውጤት በማስመዝገብ በየደረጃውም ለውጥ በማምጣት በአራት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከዓለም 50 አገሮች ምርጧ አገር እንድትሆን የሚያስችል ‹‹ራዕይ 2020›› የተባለ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ይህ እንዲሳካም በያመቱ የ40 ከመቶ ለውጥ ማስመዝገብን መሠረት ያደረገ ውጤት እንዲመዘገብና የአገሪቱ አጠቃላይ ውጤትም አሁን ካለበት 159ኛ ወደ 34ኛ እንዲመጣ ማቀዱን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈጸም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩትና በየጊዜው ስለ አፈጻጸሙ ሪፖርት የሚያቀርብላቸው አካል በኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኩል እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አበበ አባየሁ ለሪፖርተር ጠቅሰዋል፡፡

በዓለም ባንክ መለኪያ መሠረት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጦችን መተግበር ትፈልጋለች ለዚህም ሥር ነቀል ለውጦችን ማድረግ ያስፈልጋታል ያሉት አቶ አበበ፣ በመለኪያዎቹ ዝርዝር ነጥቦች ላይ የንግድ ማኅበረሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ መጨበጥ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

አገሪቱ ማስመዝገብ ስለምትፈልጋቸው ውጤቶችና በአሁኑ ወቅት ስለምትገኝበት ሁኔታ ከኮንስትራክሽን መስክ የተውጣጡና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ከግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ፣ ከቤቶች ልማት፣ ከውኃና ፍሳሽ አወጋገድ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላትና ሌሎችም ታድመው ነበር፡፡ የግል ተቋራጮች፣ መሐንዲሶች፣ አርክቴክቶችና የእነዚህ ባለሙያዎች ማኅበራትም ተገኝተው ነበር፡፡

ኮሚሽኑ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል ያላቸው መለኪያዎች በአብዛኞቹ ተሳታፊዎች ዘንድ ተችትን አስተናግደዋል፡፡ ለአብነት የግንባታ ፈቃድ ማግኘትን በተመለከተው መለኪያ መሠረት እስካሁን ባለው አሠራር መሠረት 12 የተለያዩ ዝርዝር ሒደቶችን ማለፍ፣ ፈቃድ ለማግኘት 130 ቀናትን መጠበቅና ለዚህ ሒደት የሚያስፈልገው ወጪም በእያንዳንዱ ሒደት 18.7 በመቶ እንዲገመት በምሳሌ ተደግፎ ቀርቧል፡፡

በግንባታ ፈቃድ መስክ ይጠየቃሉ ከተባሉት 12 ሒደቶች መካከል የግንባታው ዕቅድ ከከተማው ማስተር ፕላን ጋር መስማማቱን ማረጋገጥ፣ ከተጎራባቾች በግንባታው ሥራ ስምምነት መገኘቱን ማረጋገጥና ይንንኑ ስምምነትም ለማዘጋጃ ቤት ማሳወቅ፣ የግንባታ ዕቅዱና የግንባታ ፈቃዱ የፀደቀባቸውን ማረጋገጫዎች ማግኘት የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በጠቅላላው የግንባታ ፈቃድ ለመግኘት የሚጠይቀውን 130 ቀናት ወደ 24 ቀናት ዝቅ የማድረግ ዕቅድ ይዞ ብቅ ማለቱን ኮሚሽኑን አስተችቶታል፡፡

አብዛኞቹ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ቀላል እንደማይሆን በአሁኑ ወቅት ከሚታየው የከተማው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ተችተዋል፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በመወከል የተገኙት አቶ ዮሐንስ ወልደገብርኤል፣ ከዚህም በማሻገር ኮሚሽኑ የወጠነው ለውጥ የዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብትን የሚያረጋግጡ ሕግጋትን በመጋፋት ሊተገበር የታሰበ አካሄድ እንደሆነ በማብራራት ኮንነዋል፡፡

ይሁንና ኮሚሽኑ እነዚህን ለውጦች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስመዝገብ የኢንቨስትመንትና የንግድ አሠራር ሒደቶች ላይ የሚታዩ ቢሮክራሲዎችን የማስተካከልና የማቀላጠፍ ዓላማ እንዳለው አስታውቋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ አበበ እንደሚገልጹት፣ መሠረተ ልማቶችን ከመስፋፋት አኳያ ሲመዘን የአሠራር ሥርዓት ላይ የሚደረገው ማሻሻያ አነስተኛ ጫና ያለው ነው፡፡ ይኸውም አገሪቱ እንደ ኢነርጂ ያሉ ትልልቅ ግብዓቶችን አሟልታ መገኘቷ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ለማመልከት ነው፡፡ ይሁንና የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ካቢኔ በዓለም ባንክ ማሻሻያዎች ላይ ጥብቅ ክትልል እንደሚያደርግና እንቅፋት በሚሆኑ ጉዳዮች ላይም አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥበት በማድረግ ለውጦች እንዲደረጉ ግፊት እያደረገ መሆኑን አቶ አበበ ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች