Sunday, January 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በአንፀባራቂው የዓደዋ ድል የምትኮራ አገር በዴሞክራሲ ዕጦት ማፈር የለባትም!

ታላቁ የዓደዋ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር ሕዝብ በአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይል ላይ የተቀዳጀው ድል ብቻ ሳይሆን፣ በዘመኑ የዓለምን አስተሳሰብ የገለባበጠ አንፀባራቂ ገድል ነበር፡፡ የአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶች በኢንዱስትሪ አብዮት አማካይነት ጡንቻቸውን አፈርጥመው ከፍተኛ ሀብት ያካበቱበትና ጥሬ ዕቃና የሰው ጉልበት በነፃ ለማግኘት የሚፈልጉበት ጊዜ ስለነበር፣ በዘመኑ ምርጥ የሚባሉ የጦር መሣሪያዎች የታጠቀ ዘመናዊ ጦር በማሠለፍ ደሃ አገሮችን በወረራ ይዘዋል፡፡ በፓሪስ ተሰባስበው አፍሪካን ቅርጫ ያደረጉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከእነዚህ ኮሎኒያሊስት ወራሪዎች መካከል ደግሞ አንዱ ጣሊያን ነበር፡፡ በተጭበረበረ ስምምነት (የውጫሌ ስምምነት አንቀጽ 17 ያስታውሷል) አማካይነት ኢትዮጵያን በቁጥጥር ሥር የማዋል ዓላማው ባለመሳካቱ፣ ወረራ ፈጽሞ አንድ ቀን ባልሞላ ተጋድሎ በዚህ ጀግና ሕዝብ ተደምስሷል፡፡ በመላው ዓለም ከዳር እስከ ዳር የተስተጋባው የዓደዋ ድል ለዓለም ጥቁሮች መመኪያና ለነፃነት ትግል መነሻ ሊሆን የቻለው፣ በጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደር የሌለው መስዋዕትነት ነው፡፡ ይህ ድል ከተገኘ እነሆ አሁን 121 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ታላቁን የዓደዋ ፀረ ኮሎኒያሊስት ድል ስንዘክር የመስዋዕትነቱን መጠን በጨረፍታ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ የታሪክን ማርሽ የቀየረ አንፀባራቂ ድል በቀላል መስዋዕትነት የተገኘ አይደለም፡፡ ደም እንደ ውኃ ፈሶበታል፡፡ አጥንት ደቆበታል፡፡ የብዙ ሺሕ ጀግኖች ሕይወት ተሰውቶበታል፡፡ ወራሪው የጣሊያን ጦር እጅግ ዘመናዊ የሆኑ መድፎች፣ መትረየሶች፣ ጠመንጃዎችና ሌሎች አጋዥ መሣሪያዎች እስከ አፍንጫው ከመታጠቁም በላይ በአራት ታዋቂ ጄኔራሎች ይመራ ነበር፡፡ ይኼንን ዘመናዊ የጦር ኃይል ለመመከት ከአራቱም የአገሪቱ ማዕዘናት የተሠለፈው ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእናት አገሩ ከነበረው የጋለ ፍቅርና ወኔ በስተቀር እጅግ ኋላቀር መሣሪያዎችን ነበር የታጠቀው፡፡ ነገር ግን በጀግንነቱና በአርበኝነቱ ወደር የማይገኝለት ሕዝባችን የአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶችን አንገት ያስደፋ ጀብዱ ፈጽሞ ለተጨቆኑ ሕዝቦች መድኅን ሆኗል፡፡ ይህ ገድል ከዘመን ወደ ዘመን እየተሸጋገረ በአንፀባራቂነቱ ቀጥሏል፡፡

ይህ አንፃባራቂና ታሪካዊ ድል የኢትዮጵያን ዝና ከከፍታው ጫፍ ከማድረሱም በላይ፣ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መመሥረት ፅኑ መሠረት ፈጥሯል፡፡ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካና በእስያ ከፍተኛ የሆነ ፀረ ኮሎኒያሊስት መነሳሳት ፈጥሯል፡፡ የአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶች የፈጠሩትን የነጭ የበላይነት አስተሳሰብ አምክኖታል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ድል ባገኘችው ታላቅ ዝና መሠረት የአፍሪካውያን የጋራ መሰባሰቢያ ቤታቸው እንደትሆን የበኩሉን ታላቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ጀምሮ እስካሁን የአፍሪካ ኅብረት ድረስ በመቀመጫነት የምታገለግለው በዚህ ታላቅ ገድል ምክንያት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓለም ዙሪያ ለተጨቆኑ ሰዎች የነፃነት ተምሳሌት የሆነውን አንፀባራቂ ድል ከማስመዝገቡም በላይ፣ በምርኮ የተያዙ የጠላት ወታደሮችንና ቁስለኞችን በአግባቡ በመያዝ ወደ መጡበት እንዲመለሱ በማድረጉ የኮሎኒያሊስቶችን የበላይነት ስሜት ሰብሮታል፡፡ ከጀግንነት በላይ ሰብዓዊና ሥልጡን መሆኑን በዓለም አደባባይ አሳይቷል፡፡ ይኼ ድል በዚህ መንፈስ ሲዘከር ወደዚህ ዘመን መለስ ብሎ አንዳንድ ጉዳዮችን ማውሳት ተገቢ ነው፡፡

ጀግኖቹ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን በዘመናቸው የማይቻል ይመስል የነበረውን ጠንካራውንና ፈርጣማውን የኮሎኒያሊስት ኃይል ድባቅ መተው አንፀባራቂ ታሪክ ትተውልን አልፈዋል፡፡ ይህ አንፀባራቂ ድል ደግሞ ከአራቱም ማዕዘናት የተሰባሰቡት የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ነው፡፡ ይህንን ዓለም በሚገባ መስክሮታል፡፡ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊያን አገራቸው ምን ያህል ያፈቅራሉ? ለመስዋዕትነትስ ምን ያህል ዝግጁ ናቸው? የግል ጥቅምን ከማሳደድና ለሥልጣን ከመሟሟት በላይ የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ምን ያህል ናቸው? ከግል ወይም ከቡድን ጠባብ አመለካከት ወጣ በማለት ለአገርና ለወገን ያለው ትኩረትስ ምን ይመስላል? የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በማንሳት መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የድሮውን በመረገምና በዚህ ዘመን መነጽር ብቻ በማየት አገራዊ አንድነትን የሚያላሉ በርካታ ጥፋቶች ይፈጸማሉ፡፡ የአገሪቱ ሕዝብ አንድነት የተገነባው በታላቅ የአገር ፍቅር ወኔ መሆኑ የተሳናቸው ወገኖች፣ ታላቁን የዓደዋ ድል ጭምር ሲያጣጥሉት ታይተዋል፡፡ ቁም ነገሩ ግን ይህ ድል አገራቸውን የሚወዱ የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን መሆኑ ነው፡፡ በዓለም አደባባይም ተመስክሯል፡፡ ከአገር በላይ ምንም እንደሌለ ህያው መታሰቢያ ነው፡፡

ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ክብርና ሞገስ ያሰጣት ታላቁ የዓደዋ ድል ነው፡፡ ይህ ድል የተገኘው ደግሞ ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ ለአገራቸው ከፍተኛ ፍቅር በነበራቸው ጀግኖች ነው፡፡ ከጦር መሪው እስከ ተዋጊው ድረስ ቅሌን ጨርቄን ሳይሉ ከዘመኑ አስፈሪ ወራሪ ጋር የተፋለሙት ከምንም ነገር በላይ አገርን በማስቀደማቸው ነው፡፡ በአንድ ግዙፍ ኮሎኒያሊስት ኃይል ላይ ከዚያ በፊት ተገኝቶ የማይታወቅ ድል ያስመዘገቡት በዚህ ታላቅ የተቀደሰ ዓላማ ሥር ነው፡፡ ስለዚህ አገራችንን እንወዳለን የሚሉ ዜጎች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ባለሥልጣናት፣ ወዘተ በዚህ ደረጃ ላይ ይገኛሉ? ይህንን ድል የሚዘክሩ ወገኖች ሁሉ ሊመልሱት የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ትንሳዔ የሆነች አገር ከድህነት ለመውጣት ልማቷን ስትዘረጋ የዴሞክራሲው ጉዳይ ለምን ይረሳል? በአንድ እጅ እንደማይጨበጨብ ሁሉ በተለይ በፖለቲካው ዓውድ ውስጥ ያሉ ኃይሎች ራሳቸውን ሊጠይቁ ይገባል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ኢሕአዴግ የዓደዋ ድልን ሲዘክር፣ አገርን ከኮሎኒያሊስት ወራሪ ከመከላከል በላይ ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች ነፃነት ጭምር መሆኑን መገንዘብ አለበት፡፡ ይህቺ የነፃነት ጮራ አገር በዴሞክራሲ ለምን ጭራ ትሆናለች? በዚህ ዘመን ስሟ በክፉ ለምን ይነሳል? መባል አለበት፡፡ ከኮሎኒያሊስቶች ኃይል ጋር ተፋልማ ነፃነት ያወጀች አገር ዴሞክራሲ በምልዓት ሊኖራት ይገባል፡፡ በምዕራባዊያን ሚዲያ በልማት እየገሠገሠች ያለች አገር መሆኗ ቢወሳም፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ረገጣ ስሟ ጥላሸት ተቀብቷል፡፡ ይኼ በጣም ሊያሳፍር ይገባል፡፡

ታላቁና አንፀባራቂው የዓደዋ ድል የታሪክን አቅጣጫ ያስቀየረ አስገራሚ ገድል መሆኑ በበርካታ ጸሐፍት ብዙ ተብሎበታል፡፡ በመጻሕፍት፣ በሥዕሎች፣ በግጥሞች፣ በሙዚቃ፣ በድራማ፣ በቴአትር፣ በፊልም፣ ወዘተ ሙገሳዎች አግኝቷል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ ዝናን የተጎናፀፈ ነው፡፡ ለኮሎኒያሊዝም አከርካሪ መሰበር የመጀመሪያው ጠንካራ ምት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለምትባል የጀግኖች አገር ለቅኝ አገዛዝ አለመንበርከክና በነፃነት መኖር ትልቁ ምክንያት ነው፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን በቀረርቶና በሽለላ ነፃነታቸውን በሚገባ ያጣጣሙበት አኩሪ ድል ነው፡፡ የዓደዋ ድል በነፃነት የመኖርን የጋለ ፍቅር በተግባር ያረጋገጠ የመስዋዕትነት ውጤት ነው፡፡ ነፃነት፣ ክብርና ብሔራዊ ማንነት የሚገለጽበት ታላቅ ገድል ነው፡፡ በዚህ ዘመን ይህንን 121ኛ የዓደዋ ፀረ ኮሎኒያሊስት ድል የሚዘክር ትውልድ ለነፃነት የተከፈለውን ዋጋ በሚገባ መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ አገሩን የሚወድ ማንኛውም ዜጋ ይኼ ነፃነት የተገኘው በከፍተኛ መስዋዕትነት፣ መስዋዕትነቱም የተከፈለው ለአገር ሊኖር በሚገባው ከፍተኛ ፍቅር መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ አንፀባራቂው የዓደዋ ድል የዜጎች ኩራት የሚሆነውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ይህን አንፀባራቂ ድል እየኮሩበት መኖር የሚቻለው ዴሞክራሲን በማስፈን ነው፡፡ ከጥላቻ፣ ከግጭትና ከጥፋት በመራቅ በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ ዴሞክራሲን ማስፈን ይገባል፡፡ ዴሞክራሲ የሕዝብ ፈቃድ በነፃነት የሚገለጽበት ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ የዓደዋን ድል መዘከር ያለበት በነፃነት መንፈስ መሆን አለበት፡፡ በዚህ እሳቤ ውስጥ ተሁኖ ነው በአንፀባራቂው የዓደዋ ድል የምትኮራ አገር በዴሞክራሲ ዕጦት ማፈር የለባትም የሚባለው!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...