አቶ ደስታ ደንቦባ ይባላሉ፡፡ በሲዳማ ዞን የዳዬ ከተማ ሽግግር አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡ ዳዬ ከተማ የተቆረቆረችው በ1940ዎቹ አካባቢ ነው፡፡ በከተማው 6 ቀበሌዎች አሉ፡፡ ከ45 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የተመዘገቡ ነዋሪዎች አሏት፡፡ በዳዬ የተለያዩ ፓርኮች፣ ደኖች፣ እንዲሁም ፏፏቴዎች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል በቱሪስት መስህብነት የተመዘገበው የቦቦራ ፏፏቴ አንዱ ነው፡፡ የከተማውን የልማት ሁኔታ በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን አቶ ደስታ ደንቦባን አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ዳዬ የሽግግር ከተማ ሆና ማገልገል የጀመረችው መቼና እንዴት ነው?
አቶ ደስታ፡- ከዚህ ቀደም የወረዳ ጽሕፈት ቤት ሆኖ ያገለግል የነበረው ኛማ የሚባል ከተማ ነበር፡፡ ይሁንና ቦታው ወጣ ያለና ገጠራማ በመሆኑ ለአሠራር አይመችም ነበር፡፡ በመሆኑም በ1954ዓ.ም. ለብዙዎቹ ወረዳዎች ማእከል ሆና ዳዬ የወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቱ መገኛ በመሆን እንድትሠራ ተወሰነ፡፡ 2007 ዓ.ም. ሐምሌ ወር ላይ ደግሞ የሽግግር ከተማ አስተዳደር እንድትሆን ተደረገ፡፡ ከሽግግሩ ወዲህ በነበሩት 3 ቀበሌዎች ላይ ተጨማሪ 3 ቀበሌዎች ተጨመሩ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ሥራውን የጀመረው 2008 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ላይ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- የከተማው ኢኮኖሚ በምን ላይ የተመሠረተ ነው?
አቶ ደስታ፡- የከተማዋ ኢኮኖሚ ምንጭ ቡና ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴም ያለበት ቦታ ነው፡፡ እድገቷም በዚሁ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በአካባቢው ከቡና ውጪ የተለያዩ ሰብሎችም በጥሩ ሁኔታ ይመረቱበታል፡፡ አገሩ ለም ነው፡፡ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ገብስና የመሳሰሉት ሰብሎች ይመረታሉ፡፡ በሌሎች ገጠራማ በሆኑ አካባቢዎች ማለትም በ3 ቀበሌዎች ውስጥ እንሰትና ቡና በብዛት ይመረታሉ፡፡ በእነዚህ ቀበሌዎች የሚሠሩ አርሶ አደሮች በሰብል ወቅት በሚያገኙት ገንዘብ ኑሯቸውን ያሻሽላሉ፡፡ ወደዚህ እየመጡም ቤት ይሠራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ከተማዋ የተቆረቆረችው በ1940ዎቹ ነው፡፡ ይህ ረጅም ዓመት የሚባል ቢሆንም ግን ዕድገት አላሳየችም፡፡ ይህ ከምን አንጻር ነው?
አቶ ደስታ፡- እኛ ከተማዋ ወደኋላ ቀርታለች የሚል እምነት የለንም፡፡ ምክንያቱም ከ100 ዓመት በላይ የቆዩ ከተሞች ነገር ግን ይህች ከተማ የደረሰችበት ገና ያልደረሱ ብዙ አሉ፡፡ ለምሳሌ ወደ ዳዬ ስትመጡ መንገዱ ላይ በንሳ ቀባዱ የሚባል ከተማ አለ፡፡ ከተማው ከዚህ ከተማ በፊት የተቆረቆረ ነው፡፡ ነገር ግን ከተማ ሳይሆን ቀበሌ ነው የሚመስለው፡፡ በዞናችን አሉ ከሚባሉ ከተሞች ውስጥ ፈጣን ዕድገት ያሳየው የኛ ከተማ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ለከተማው ዕድገት መሠረት የሚሆኑ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ ኅብረተሰቡም ደግሞ ታታሪና በደንብ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ጠንካራ የገቢ ምንጭ እንዲኖር አስችሎናል፡፡ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩ የከተማው ተወላጅ የሆኑ ኢንቨስተሮች ሁሉ አሉ፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በመሰማራት ለከተማው እድገት የበኩላቸውን እያደረጉ ነው፡፡ በከተማው ከ20 በላይ ሕንፃዎች አሉ፡፡ ብዙዎችም ሕንፃ ለመገንባት ፈቃድ አውጥተው ወደ ሥራ እየገቡ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከወረዳ ተለይቶ ከወጣ ወዲህ ትልቅ ለውጥ ታይቷል፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ ከተማዋ የራሷን በጀት ይዛ የራሷን አስተዳደር ይዛ ስትንቀሳቀስ ብዙ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በከተማው ዩኒቨርሲቲ እየተገነባ መሆኑን ሰምተናል፡፡ እስቲ አጠቃላይ ስለግንባታ ሒደቱና መቼ ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር ይንገሩን?
አቶ ደስታ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በ2007 ዓ.ም. ዳዬን ጎብኝተው ነበር፡፡ በወቅቱ የአካባቢው ኅብረተሰብ ዩኒቨርሲቲ እንዲከፈት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ በተጠየቀው መሠረትም ፈቃዳቸውን ሰጥተው ግንባታው በዚህ ዓመት ተጀምሯል፡፡ ይህ ለከተማው ፈጣን ለውጥ እንደሚፈጥር ተስፋ አለን፡፡ ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛል፡፡ በ2010 ዓ.ም. ተጠናቆም አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡
ሪፖርተር፡- በከተማዋ ትልቅ የመንገድ ችግር ይስተዋላል፡፡ ችግሩን ለመቀነስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች አሉ?
አቶ ደስታ፡- በከተማው ያለው የአስፓልት መንገድ አንድ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የተለያዩ የመንገድ ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በዚህ ዓመት የሚጀመር የ3 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ አለ፡፡ ጨረታ ወጥቶ ሥራው በቀጣይ ሚያዝያ ወር ይጀመራል ተብሎ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ የዚህ መንገድ ግንባታ በጀት በፌደራል መንግሥት የሚደገፍ ነው፡፡ ሌላው ከዳዬ እስከ ጅሪ የሚሠራ የ7 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ግንባታ ነው፡፡ ይህም በፌዴራል መንግሥት የሚሠራ ነው፡፡ እነዚህ መንገዶች ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀይሩ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በከተማው የተጀመሩ ሌሎች የልማት ሥራዎችስ አሉ?
አቶ ደስታ፡- ለወደፊት ኢንዱስትሪ ፓርክ በአካባቢው ለመገንባት መንግሥት ዕቅድ ይዟል፡፡ ዋናው የኢንዱስትሪ ፓርክ የሚቋቋመው ይርጋለም ሲሆን እዚህ ለማቋቋም የታሰበው መጋቢውን ነው፡፡ ለዚህ ግንባታ የሚሆን ቦታም ተዘጋጅቷል፡፡
ሪፖርተር፡- በከተማው ምን ያህል የጤና ተቋማት አሉ?
አቶ ደስታ፡- በጤናው ረገድ እየታየ ያለው ለውጥም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ከተማችን ውስጥ ለወረዳው አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ አንድ ትልቅ ጤና ጣቢያ አለ፡፡ በየቀበሌው የሚገኙ የተለያዩ ጤና ኬላዎችም አሉ፡፡ በ2008 ዓ.ም. ሥራ የጀመረ አዲስ ሆስፒታልም አለ፡፡ ሆስፒታሉ በአካባቢው ያሉ ወረዳዎችን ጭምር የሚመግብ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ለመገንባትስ የታሰበ ነገር አለ?
አቶ ደስታ፡- የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ በተወሰነ ደረጃ ተጀምሯል፡፡ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ ተጀምሯል፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች ግንባታ ተጠናቋል፡፡ የድንጋይ ንጣፍም በዚህ ወር ይጀመራል፡፡ ይህ እንደተጠናቀቀ ነው የሚታሰበው፡፡ ሌላው ጨረታ ወጥቶለት ወደ ሥራ ሊገባ ያለ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አለ፡፡ ግንባታው ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት እስከ ጤና ጣቢያ የሚዘረጋ ነው፡፡ ሥራውም በዚህ ወር ይጀመራል፡፡
ሪፖርተር፡- በከተማው የውኃ ችግር መኖሩን ተመልክተናል፡፡ አጠቃላይ የንጹህ ውኃ ተደራሽነት ምን ይመስላል? ተደራሽነቱን ከማስፋት አኳያስ የከተማው መስተዳድር ምን እያደረገ ይገኛል?
አቶ ደስታ፡- ውኃ የምናገኘው ከሁለት አቅጣጫ ነው፡፡ ከሰሜናዊና ከደቡባዊ ክፍል ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ግን ከደቡባዊ ክፍል የነበረው አንድ ፓምፕ በአጋጣሚ ተቃጥሎ በጥገና ላይ ነው፡፡ ይህ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚፈታ ችግር ነው፡፡ አካባቢያችን ደግሞ የውኃ ችግር የለበትም፡፡ ከዚህ በፊት ተከስቶ አያውቅም ወደ ፊትም አይከሰትም፡፡ በዙሪያችን የተለያዩ ምንጮች አሉ፡፡ ከሰሜናዊው ክፍል የሚመጣው ውኃ ደግሞ እንደ ድሮው በደምብ አላጠገበም እንጂ አልተቋረጠም፡፡ ከሱ የሚገኘው በፈረቃ ለተለያዩ ቀበሌዎች እየተሰጠ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በተያያዘ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? የመንገድ መብራቶች አለመኖራቸውን ታዝበናል፡፡
አቶ ደስታ፡- የመብራት ችግር የአገሪቱ ችግር ነው፡፡ የኃይል ማነስ ቢኖርም አገልግሎት እየሰጠ ነው የሚገኘው፡፡ ሰሞኑን ደግሞ አንድ ትራንስፎርመር ተቃጥሏል፡፡ ነገር ግን ከሞላ ጐደል ደህና ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የመቆራረጥ ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን እየተሻሻለ ነው፡፡ የተቃጠለውም ቢሆን በቅርቡ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡ መንግሥት ነገሮችን በቅርበት ስለሚከታተል፣ ኅብረተሰቡም እኛ ለምንጠይቀው ጥያቄ ወዲያው ምላሽ ስለሚሰጥ ችግር የለም ማለት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- በከተማው ያለው የትምህርት ተደራሽነት ምን ያህል ነው? ምን ያህል ትምህርት ቤቶችስ አሉ?
አቶ ደስታ፡- ከከተማችን አንጻር ያለው የትምህርት ተደራሽነት ጥሩ የሚባል ነው፡፡ አንድ የመሰናዶ ትምህርት ቤት አለ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም እንደዚሁ፡፡ ሁለት መለስተኛና አንደኛ ደረጃ፣ እንዲሁም የግል ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ አንድ ኢንደስትሪያል ኮንስትራክሽን ኮሌጅም አለ፡፡ ብዙ ወጣቶች በኮሌጁ በሙያ እየሠለጠኑ በግል በመደራጀት የተለያዩ ሥራዎች እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ እየተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ ሕንጻዎች አሉ፡፡ ይኼ በመልሶ ማልማት የሚታይ ነው ወይስ ከተማዋ አዲስ ፕላን አላት?
አቶ ደስታ፡- የቆዩ አሮጌ የመንግሥት ቤቶች አሉ፡፡ እነሱ እየተነሱ ባለሀብቶች እንዲገነቡበት ይሰጣቸዋል፡፡ አዲስ የሚከፈቱ መንገዶችም አሉ፡፡ የተሠሩት እየተነሱ በአዲስ ፕላን እየተሠሩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በተገቢው መጠን እድገት ለማስመዝገብ ምን አይነት ድጋፍ ትፈልጋላችሁ?
አቶ ደስታ፡- ከተማዋ ጅምር ላይ ነች፡፡ ወደፊት ጥሩ ለውጥ ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡ መንግሥት ከጎናችን ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግልን እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ አካባቢው ካሽ ክሮፕ የሚመረትበት፣ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች ያሉበት ሲሆን በእነዚህ ላይ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሀብቶች በራችን ክፍት ነው፡፡