በአዲስ አበባ ከተማ ለሚካሄዱ ግንባታዎች መስተጓጐል ምክንያት በሆኑት፣ ለይዞታ ባለቤቶች የሚሰጠው ተነፃፃሪ ካርታ (ፕሮፖርሽናል ካርታ) እና በልማት ምክንያት የሚነሱ ባለይዞታዎች የሚያቀርቡት የፍርድ ቤት ዕገዳ ላይ፣ የፌዴራል መንግሥት መመርያ እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥያቄ የቀረበለት የፌዴራል መንግሥት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት፣ ከአስተዳደሩና ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጋር ንግግር መጀመሩ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ለዓመታት የተከማቹ ሰነድ አልባ ባለይዞታዎች ካርታ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ካርታ የመስጠት ሥራ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ በቅርቡ ለምክር ቤት ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ ‹‹ይህንን ሥራ በዚህ ዓመት አጠቃሎ በሚቀጥለው ዓመት የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ወደ ሌሎች ሥራዎች መዛወር አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን እስካሁን ለሰነድ አልባ ባለይዞታዎች፣ ቀደም ሲልም ሰነድ አልባ ላልሆኑ ባለይዞታዎች ከተሰጡ ካርታዎች ውስጥ በቀላሉ የማይገመቱ ተነፃፃሪ ካርታዎች ተሰጥተዋል፡፡
ተነፃፃሪ ካርታ በአንድ ግቢ ውስጥ ራሱን የቻለ ካርታ ያልተሰጠው ይዞታ፣ ለአብነትም የቀበሌ ቤት በግል ይዞታ ግቢ ውስጥ ሲኖር፣ በፕላን መሠረት መለያየት ለማይቻሉ ይዞታዎችና ለተለያዩ ወራሾች የሚሰጥ የካርታ ዓይነት ነው፡፡
ተነፃፃሪ ካርታ የሚሰጠው ግለሰብ ይዞታውን መሸጥ መለወጥ ወይም ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ ማካሄድ የማይፈቀድለት በመሆኑ፣ የችግሩ ተጎጂዎች ቅሬታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ለዓለም ተሰራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህንን ችግር ለመፍታት የፌዴራል መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጥ ተጠይቆ ንግግር ተጀምሯል፡፡
ይህ ለፌዴራል መንግሥት የቀረበው ጥያቄ ኪራይ ቀመስ ይዞታዎችን አያካትትም ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው እንደገለጹት፣ የኪራይ ቀመስ ይዞታዎች ጉዳይ የተዘጋና ውሳኔ የተሰጠበት ነው፡፡
ኪራይ ቀመስ የሚባሉት ይዞታዎች በአዋጅ 47/1967 ተወርሰው የሆነ ጊዜ ኪራይ የተከፈለባቸው ናቸው፡፡ ባለይዞታዎች እነዚህን ቤቶች የግል ይዞታ መሆናቸውን መከራከሪያ ቢያቀርብም፣ አስተዳደሩ ፋይላቸውን በሚመለከትበት ወቅት ኪራይ የተከፈለባቸው በመሆኑ እንደ ቀበሌ ቤት የሚታሰቡ ናቸው፡፡ ነገር ግን ነዋሪዎች ይዞታዎቹ የግል መሆናቸውን በመግለጽ ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና ግንባታ ቢሮ በ1996 ዓ.ም. ባካሄደው ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ 328 ሺሕ ቤቶች ነበሩ፡፡ በዚያ ወቅት በተጠናው ጥናት ከእነዚህ ውስጥ 150 ሺሕ የሚሆኑት የቀበሌ ቤቶች ናቸው፡፡
ከቤቶቹ መካከል ብዛት ያላቸው በልማት ምክንያት የፈረሱ ናቸው፡፡ ባልፈረሱ አካባቢዎች በግል ይዞታ መካከል የሚገኙ የቀበሌ ቤቶች ያሉ በመሆኑና ግለሰቦች ሊያጠቃልሏቸው የሚችሉባቸው ሕግጋት ባለመኖራቸው፣ ወይም መንግሥት መፍትሔ ባለማስቀመጡ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች ይዞታቸውን ወደ ገንዘብ መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በዚህም ለዓመታት ቅሬታ ሲቀርብ የቆየ በመሆኑ አስተዳደሩ ለዚህ ችግር የመጨረሻ ዕልባት ለመስጠት የፌዴራል መንግሥትን መጠየቁ ታውቋል፡፡
በከተማው ለሚካሄዱ ግንባታዎች ሌላው እንቅፋት ነው የተባለው የፍርድ ቤቶች ዕግድ ነው፡፡ በተለይ የመንገድ ግንባታዎችና የመልሶ ማልማት ፕሮግራሞች፣ ባለይዞታዎች ከፍርድ ቤት በሚያመጧቸው ዕግዶች ምክንያት እየቆሙ ነው ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በቅርቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው ውይይት፣ የመንገድ ፕሮጀክት በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚዘገዩ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፣ መሥሪያ ቤታቸው በቅርብ ከባለድርሻዎች ጋር ባካሄደው ስብሰባ በፍርድ ቤቶች ዕግድ በልማት ላይ እየፈጠረ ያለው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም ብለዋል፡፡ በዕግድ ምክንያት ግንባታቸው ተጠናቆ የቆሙ የመንገድ ፕሮጀክቶች አሉ በማለት ኢንጂነሩ ገልጸዋል፡፡
በመልሶ ማልማት አካባቢዎች ለአብነት በመሀል አዲስ አበባ 186 ሔክታር መሬት በመልሶ ማልማት ውስጥ ታቅፏል፡፡ ከዚህ ውስጥ ባለፉት ወራት ከሰው ንክኪ ነፃ የተደረገው 47 ሔክታር መሬት ብቻ ነው፡፡
በአጠቃላይ ለተነሺዎች በተገቢው መንገድ መሠረተ ልማት አሟልቶ ቤት አለማስረከብ፣ ተመጣጣኝ ካሳና ምትክ ቦታ አለማቅረብ፣ እንዲሁም የፍርድ ቤት ዕግድ ችግሮች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
አቶ ለዓለም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፍርድ ቤት ዕግድ ለመልሶ ማልማት ሥራዎች እንቅፋት እየሆነ በመምጣቱ የፌዴራል መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጥ ተጠይቋል፡፡ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጋር ውይይት እያደረገ ነው፤›› ሲሉ አቶ ለዓለም ተናግረዋል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 መሬት የመንግሥትና የሕዝብ በመሆኑ ለኅብረተሰብ የልማት ተጠቃሚነት ከተፈለገ አስፈላጊውን ካሳ በመስጠት ማልማት እንደሚቻል ይገልጻል፡፡
የልማት ተነሺዎች ለማስለቀቅ 90 ቀናት መስጠት ተገቢ ሆኖ እያለ ግን በ24 ወይም በ48 ሰዓት ውስጥ ለማስለቀቅ ይሞክራል፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ተነሺዎች የፍርድ ቤት ዕግድ የሚያቀርቡ በመሆናቸው፣ የከተማ አስተዳደሩ ለማካሄድ ያቀደው የልማት ሥራ ሲስተጓጎል ይታያል ተብሏል፡፡
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው ይላል፡፡