Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየግዥ መመርያ በሚጥሱ ነጋዴዎች ላይ የጉዳት ካሳ ቅጣት የሚጥል መመርያ ተዘጋጀ

የግዥ መመርያ በሚጥሱ ነጋዴዎች ላይ የጉዳት ካሳ ቅጣት የሚጥል መመርያ ተዘጋጀ

ቀን:

– የግዥ መርህ የማያከብሩ የሥራ ኃላፊዎችም ይቀጣሉ ተብሏል

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚፈልጓቸውን ዕቃዎች በማዕከል ደረጃ ግዥ እንዲፈጽም የተቋቋመው የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ በገቡት ውል መሠረት ዕቃዎችን በወቅቱ በማያቀርቡ ኩባንያዎች ላይ 1.1 በመቶ የተጣራ የጉዳት ካሳ እንደሚያስከፍል ይፋ አደረገ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ የግዥ ዕቅድና የአፈጻጸም ሪፖርት በማያቀርቡ፣ ዕቃዎችን በወቅቱ ላቀረቡ ኩባንያዎች በአምስት ቀናት ውስጥ ክፍያ በማይፈጽሙ፣ በተለይም የግዥና የፋይናንስ ኃላፊዎችን ጨምሮ እስከ ሚኒስትር ደረጃ ያሉ ባለሥልጣናትን ተጠያቂ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

ከፍተኛ ሙስና በተንሰራፋበት በዚህ የግዥ ዘርፍ መሠረታዊ የሆነ የአሠራር ለውጥ ያመጣል የተባለው የግዥ መመርያ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አማካይነት እየተሻሻለ ሲሆን፣ በተለይ ከሚቀጥለው 2010 በጀት ዓመት ጀምሮ በይፋ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎትና የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በጋራ ባዘጋጁት ስብሰባ፣ ከመንግሥት የግዥና የፋይናንስ ኃላፊዎች ከግል አቅራቢዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ፣ ‹‹አቅራቢዎች በገቡት ውል መሠረት ሳያቀርቡ ሲቀሩም እያስታመምን ቆይተናል፡፡ ችግሩ ሲከፋም የአቅራቢዎች ለውጥ እያደረግን መጥተናል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በኋላ ይህን አሠራር አቁመናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

‹‹አንድ አቅራቢ ዕቃ በወቅቱ ካላቀረበ የሚቀጣበት አሠራር እየተዘጋጀ ነው፡፡ በውሉ መሠረት የማያቀርብ ኩባንያ 1.1 በመቶ የተጣራ ጉዳት ካሳ የሚከፈልበት አሠራር በሚሻሻለው መመርያ ውስጥ ተካቷል፤›› ሲሉ አቶ ይገዙ አስታውቀዋል፡፡

የመንግሥት ግዥዎችና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ሥራዎችን ተቆጣጣሪ ተቋም የሆነው የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጆንሴ ገደፉ የአቶ ይገዙን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡

አቶ ጆንሴ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት የፋይናንስ አዋጅ ፀድቋል፡፡ በአዋጅም አዋጁን ለማስፈጸም እየተዘጋጁ ባሉ መመርያዎች እስከ ዳይሬክተሩ፣ ከዚያም እስከ ሚኒስትሩ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናት የሚቀጡበት ሥርዓት ተቀምጧል፡፡

የግዥ ዕቅድና የአፈጻጸም ሪፖርት በወቅቱ ያላቀረበና ዕቅዱን በወቅቱ በተለያዩ አውታሮች ለአቅራቢዎች ይፋ ያላደረገ አካል ቅጣት እንደሚጣልበት አቶ ጆንሴ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ከአዲሶቹ የካቢኔ አባላት (አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች) ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ለግዥና ለፋይናንስ ኃላፊዎችም ሥልጠና ተሰጥቷል፤›› ሲሉ አቶ ጆንሴ ቀጣዩን የመንግሥት አቋም ይፋ አድርገዋል፡፡

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ከተቋቋመበት ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ ገበያ ለማረጋጋት፣ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ስንዴ፣ ለግንባታ የሚውሉ አርማታ ብረት፣ የሳኒተሪ ዕቃዎች፣ ለዩኒቨርሲቲዎች የሚውሉ የላብራቶሪ ዕቃዎችና ማጣቀሻ መጻሕፍት፣ የምግብ ዘይቶችና የመሳሰሉት ግዢዎችን በአምስት ዓመት ውስጥ ከ51.3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግዥ መፈጸሙን አስታውቋል፡፡ ይህም በየዓመቱ በአማካይ 8.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2009 ዓ.ም. ግማሽ ዓመትም በአጠቃላይ ለተለያዩ ዕቃዎች ግዥ ሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ ግዥ ለመፈጸም ውል ገብቷል፡፡

የሙስና መፈልፈያ ናቸው ከተባሉ ግንባር ቀደም ዘርፎች መካከል አንዱ የግዥ ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት መንግሥት ትኩረት ቢያደርግም፣ አሁንም የግዥ ዕቅድ በተገቢው አለመንደፍ፣ በተለይም በበጀት ዓመት ማጠቃለያ ላይ በርካታ ግዥዎች መፈጸም ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው ተብሏል፡፡ ይህም የግዥ ዘርፉ ከፍተኛ ሙስና፣ ብክነትና ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርት የሚቀርቡበት እያደረገው እንደሆነ ተመልክቷል፡፡  

አቶ ይገዙ እንዳሉት በተለይ አንዳንድ አቅራቢዎች በውሉ መሠረት ወቅቱንና ጥራቱን የጠበቀ ዕቃ አለማቅረብ፣ መሥሪያ ቤቶች በወቅቱ ትክክለኛ ፍላጎታቸውን አለማቅረብ፣ በአቅርቦት ላይ እጥረት ማጋጠም፣ ዕቃ ከገባ በኋላ ለአቅራቢዎች በወቅቱ ክፍያ አለመፈጸም፣ በጨረታ የተወገዱ ተሽከርካሪዎች አሸናፊ ለሆኑት የስም ዝውውር ለማስፈጸም የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ መኖር፣ የብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ለወሰዱዋቸው ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች በወቅቱ ክፍያ ያለመፈጸም ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የመንግሥት የግዥ ወይም የፋይናንስ ኃላፊዎች በርካታ ቅሬታዎች ያነሱ ሲሆን፣ አቅራቢ ኩባንያዎች በገቡት ውል መሠረት ዕቃዎችን በወቅቱ አለማቅረባቸው፣ በተሰጣቸው ዝርዝር መሥፈርት ዕቃዎችን ያለማቅረብ ችግሮችን አንስተዋል፡፡ አቅራቢዎች በበኩላቸው የመንግሥት ተቋማት ያዘዙትን ዕቃ በወቅቱ የማያነሱ መሆኑንና ክፍያም በወቅቱ አለመክፈላቸውን እንደ ችግር አቅርበዋል፡፡

ኃላፊዎቹ እነዚህ ችግሮች የሚፈቱበት ጠንካራ መመርያ እየተዘጋጀ መሆኑንና ይህን መመርያ በሚጥሱት ላይም ዕርምጃ እንደሚወሰድ አብራርተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...