Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሚድሮክ ሔሊኮፕተር ተከሰከሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር ከሚተዳደሩት በርካታ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ (ቲኤንኤ) ኩባንያ ንብረት የሆነ ቤል 222U ሔሊኮፕተር፣ ቅዳሜ የካቲት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ አምስት መንገደኞች አሳፍሮ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ወደ ሐዋሳ ለመብረር በመነሳት ላይ ሳለ ተመልሶ ወደ መሬት ወድቋል፡፡

በሔሊኮፕተሩ ውስጥ ዋና አብራሪና ረዳት አብራሪ፣ እንዲሁም አምስት የተለያዩ አገር ዜግነት ያላቸው ተሳፋሪዎች ነበሩ፡፡ በአብራሪዎቹ ላይም ሆነ በመንገደኞቹ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስ ከአደጋው መትረፋቸው ታውቋል፡፡ መንገደኞቹ ወደ ሐዋሳ ለስብሰባ በመጓዝ ላይ የነበሩ ሚሲዮናዊያን እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በቅርቡ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ተገንጥሎ በትራንስፖርት ሚኒስቴር ሥር ከተቋቋመው የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የምዝገባ ቁጥር ኢቲ-ኤ ኤም አር ንብረትነቱ የቲኤንኤ የሆነ ሔሊኮፕተር በሁለት አብራሪዎች አማካይነት ወደ ሐዋሳ ለመብረር ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የጄኔራል አቪዬሽን ራምፕ (አውሮፕላን ማቆሚያ) በመነሳት ላይ ሳለ ከመሬት ብዙም ሳይርቅ ተመልሶ ወደ መሬት ወድቋል፡፡ በአብራሪዎቹ ላይም ሆነ በመንገደኞች ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ የገለጸው ቢሮው፣ በሔሊኮፕተሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ አደጋው በተከሰተበት ወቅት እሳት አለመነሳቱን ቢሮው አረጋግጧል፡፡

ሁለት ሞተር ያለው ቤል222 ሔሊኮፕተር የወደቀው በኃይል መቋረጥ (ሞተር በመጥፋቱ) እንደሆነ የሪፖርተር ምንጮች የተናገሩ ቢሆንም፣ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ ምርመራ በማካሄድ ላይ ስለሆነ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ የቢሮው ባለሙያዎች አደጋው እንደደረሰ ሥፍራው በመድረስ ከሔሊኮፕተሩና ከአብራሪዎቹ አስፈላጊውን መረጃ የሰበሰቡ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የተሰበሰቡትን መረጃዎች በመመርመር ላይ ናቸው፡፡ ቢሮው የአደጋውን ሪፖርት በቅርቡ አጠናክሮ ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡ ‹‹የአደጋ ምርመራ ሳይጠናቀቅ ምንም ማለት አይቻልም፤›› ብሏል ቢሮው፡፡

ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአውሮፕላን ምዝገባና የበረራ ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የቲኤንኤ ቤል222 ሔሊኮፕተር ተመዝግቦ የገባው እ.ኤ.አ. በነሐሴ 2008 ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1986 በአሜሪካ ቤል ሔሊኮፕተር ኩባንያ የተመረተው ሔሊኮፕተሩ እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 2016 ድረስ 3,891 ሰዓት መብረሩ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የአውሮፕላን ምዝገባና የበረራ ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት በየዓመቱ በኢትዮጵያ የተመዘገቡ ሲቪል አውሮፕላኖችና ሔሊኮፕተሮች ላይ ምርመራ በማድረግ የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ይሰጣል፡፡ ዳይሬክቶሬቱ በጥቅምት 2009 ዓ.ም. በቲኤንኤ ሔሊኮፕተር ላይ ምርመራ አድርጎ የብቃት ማረጋገጫ መስጠቱን፣ ሠርተፊኬቱም ለአንድ ዓመት የሚያገለግል መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሔሊኮፕተሩ ለበረራ ብቁ ነበረ፡፡ ሠርተፊኬቱ ሔሊኮፕተሩ እስከ ጥቅምት 2010 ለበረራ ብቁ መሆኑን ያረጋግጣል፤›› ብለዋል፡፡

የቲኤንኤ ዋና ሥራ አስኪያጅ ካፒቴን ተረፈ ኃይሌ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሔሊኮፕተሩ የቴክኒክ ብቃቱ የተጠበቀና በጥሩ ሁኔታ በማገልገል ላይ ነበረ፡፡ ‹‹አደጋ እንግዲህ በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት ይችላል፡፡ ያለ ነገር ነው፡፡ ዋናው ነገር አብራሪዎቻችንና ደንበኞቻችን ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በሰላም መውጣታቸው ነው፤›› ያሉት ካፒቴን ተረፈ፣ የአደጋ ምርመራው ሲጠናቀቅ የተሟላ መረጃ ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር የሚተዳደረው ቲኤንኤ እ.ኤ.አ. 2004 የተመሠረተ ሲሆን፣ በዋነኛነት የቻርተር በረራ አገልግሎት በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ይሰጣል፡፡ ኩባንያው ሁለት እያንዳንዳቸው 37 መቀመጫ ያላቸው ቦምባርዲየር ዳሽ8-200 አውሮፕላኖች ሲኖሩት፣ አውሮፕላኖቹ በአብዛኛው በሱዳንና በሌሎች አገሮች የቻርተር በረራ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ አውሮፕላኖቹ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና አስጎብኚ ድርጅቶች ይከራያሉ፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ቲኤንኤ ወደ ጎንደርና ሁመራ መደበኛ የመንገደኞች በረራ አገልግሎት መስጠት ጀምሮ የነበር ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ አገልግሎቱን አቋርጧል፡፡  ቲኤንኤ በተጨማሪ ሁለት አይረስ የተባሉ ቀላል አውሮፕላኖች በመጠቀም የፀረ አረምና አንበጣ መከላከያ መድኃኒት ርጭት አገልግሎት ይሰጣል፡፡

ቲኤንኤ ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የሚጠይቀውን የበረራ ደኅንነት መመርያ ሰነድ አሟልቶ ባለማቅረቡ ባለሥልጣኑ የኩባንያውን ፈቃድ ለአጭር ጊዜ አግዶት ቆይቷል፡፡ ባለሥልጣኑና የኩባንያው ማኔጅመንት መስተካከል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ተነጋግረው ኩባንያው የተጠየቁትን ሰነዶች በማሟላቱ ዕግዱ እንደተነሳለት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ቲኤንኤ ቤል222 ሔሊኮፕተርን የገዛው እ.ኤ.አ. በ2008 አሜሪካን ጄኔራል ሰፕላይስ ከተባለ ኩባንያ መሆኑን የሚናገሩት የሪፖርተር ምንጮች፣ ሔሊኮፕተሩ ረዥም ጊዜ ያገለገለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ባለሙያዎች በበኩላቸው ሔሊኮፕተሩ በየጊዜው መደበኛ ጥገና የሚደረግለት ለበረራ ብቁ የሚባል እንደበረ አስረድተዋል፡፡ ዋናው ነገር ለሔሊኮፕተርና ለአውሮፕላን የሚደረገው መደበኛ ጥገናና ክትትል ነው እንጂ ዕድሜው አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ ዕድሜ ያላቸው ሔሊኮፕተሮች አገራችን ውስጥ ይበራሉ ብለዋል፡፡

ባለሙያዎቹ ይህን ቢሉም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እ.ኤ.አ. ሰኔ 2013 ያወጣው የአቪዬሽን ሬጉሌሽን ዕድሜያቸው ከ22 ዓመት በላይ የሆኑ የመንገደኛ አውሮፕላኖች ወደ አገር እንዳይገቡ ይከለክላል፡፡ የጭነት ማጓጓዣ አውሮፕላኖች ዕድሜ ደግሞ ከ25 ዓመት እንዳይበልጥ መመርያው ያዛል፡፡

የቲኤንኤ ሔሊኮፕተር ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በባለሥልጣኑ እ.ኤ.አ. በ2008 ዓ.ም. ሲመዘገብ 22 ዓመት ዕድሜ ነበረው፡፡ ‹‹ሬጉሌሽኑ የወጣው እ.ኤ.አ. በ2013 በመሆኑ በሔሊኮፕተሩ ላይ ተፈጻሚነት የለውም፡፡ 22 ዓመት የሚለው ወደ አገር ተመዝግበው ሲገቡ ያላቸው ዕድሜ እንጂ፣ ከተመዘገቡ በኋላ 50 ዓመትም ቢሞላቸው ከገበያ እንዲወጡ የሚያስገድድ ሕግ የለም፤›› ብለዋል ኃላፊው፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተመዘገቡ 15 የግል አየር መንገዶች ቢኖሩም፣ በሥራ ላይ የሚገኙት ሰባት ያህል ብቻ ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች