Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል ለማመንጨት መቃረቡን መንግሥት ይፋ አደረገ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል ለማመንጨት መቃረቡን መንግሥት ይፋ አደረገ

ቀን:

  –  ዋናው የውኃ ሙሌት ከታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ጋር በመመካከር ይከናወናል ተብሏል

  –  መንግሥት ለሜቴክ ተሳትፎ ያሳለፈው ፖለቲካዊ ውሳኔ ሴራዎችን ማምከኑ ተገለጸ

የመሠረት ድንጋዩ ከተጣለ ስድስተኛ ዓመቱን ለመያዝ የተቃረበው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ፣ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ውኃ ለመያዝ መቃረቡን መንግሥት ይፋ አደረገ፡፡  

የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ ምክር ቤት ቦርድ አባልና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ግድቡ በይፋ የተጀመረበት ስድስተኛ ዓመት መቃረቡን አስመልክቶ የካቲት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ግንባታው የደረሰበት የአፈጻጸም ደረጃ ሕዝባዊ ተሳትፎ አጥጋቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ላይ በተጠናከረው የፕሮጀክቱ አፈጻጸም መረጃ መሠረት 56 በመቶ መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡

‹‹56 በመቶ ማለት በምን ደረጃ ላይ ነው ከተባለ በቴክኒክ ሥራው የመጀመሪያ ዙር ኃይል ለመጀመር ተቃርቧል፤›› ብለዋል፡፡ የግድቡን ግንባታን በተመለከተም ፈጣንና በየጊዜው ለውጥ የሚታይበት መሆኑንና በመጀመሪያ ዙር ኃይል ለማመንጨት የሚያስፈልገውን የውኃ ሙሌት ለመጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ ኃይል የሚያመነጩት ሁለት ተርባይኖች  መሆናቸውን፣ እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት በድምሩ 750 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ዝግጅት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገልጸዋል፡፡

ከግድቡ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተቀብሎ ወደ ብሔራዊ የኃይል ማስተላለፊያ መረብ የሚያደርስ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ኃይል ማስተላለፊያ፣ ግድቡ ከሚገኝበት እስከ ሱሉልታ ማሠራጫ ድረስ ተዘርግቶ መጠናቀቁንም ጠቁመዋል፡፡

በግድቡ የውኃ ሙሌት ለመጀመር የሚደረገውን ዝግጅት የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ግብፅና ሱዳን ተስማምተውበት እንደሆነ የተጠየቁት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ ለመጀመሪያው ምዕራፍ ኃይል ማመንጫ የሚያስፈልገውን ውኃ ለመያዝ ከሁለቱ አገሮች ጋር መመካከር እንደማይጠይቅ አስታውቀዋል፡፡

የመጀመሪያውን ምዕራፍ ኃይል ለማመንጨት የሚያስፈልገው የውኃ መጠን በጣም አነስተኛ መሆኑን፣ ምንም ዓይነት ተፅዕኖም በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ እንደማያደርስ አክለዋል፡፡

የአጠቃላይ ግድቡ የውኃ ሙሌት የሚከናወነው ግን ከሁለቱ አገሮች ጋር በመመካከር እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ አጠቃላይ የውኃ ሙሌቱ ከግብፅ አስዋን ግድብ የበለጠ ሰው ሠራሽ ኃይቅን የሚፈጥር በመሆኑ፣ በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች የውኃ ድርሻ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል ሥጋት መኖሩን አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የውኃ ሙሌቱ የጎላ ተፅዕኖ እንደማያደርስ እርግጠኛ ቢሆንም፣ በአገሪቱ መካከል መተማመንን ለመፍጠር ከፖለቲካዊ ይሁንታ ባሻገር የውጭ ገለልተኛ አማካሪ ኩባንያዎች የሙሌት ሒደቱን፣ አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖዎችን እንዲያጠኑ በኢትዮጵያ ሐሳብ አቅራቢነት ጥናት ለመጀመር ዝግጅት ላይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

አማካሪ ኩባንያዎቹ የሚያጠኑት ግድቡ የሚይዘው 74 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ቢጠራቀም፣ በሁለቱ የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት አይደርስም የሚል በጥናት ላይ የተመሠረተ ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ መሆኑን ዶ/ር ደብረ ጽዮን ጠቁመዋል፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሥራ ላይ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) እንዲሳተፍ መንግሥት ያሳለፈው ፖለቲካዊ ውሳኔ፣ ትክክልና ወሳኝ መርህ እንደነበር ዛሬ የተገኙት ውጤቶች ምስክር መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ሜቴክ በግንባታው እንዲሳተፍ የወሰነው ዋና ኮንትራክተር ከሆነው የጣሊያኑ ሳቢኒ ኩባንያ ጋር የተፈረመውን ውል በመከለስ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ውሳኔው ፖለቲካዊ ግብ ላይ ያተኮረ ነበር ብለዋል፡፡

ከጣሊያኑ ኩባንያ ሳሊኒ ጋር የተገባውን ውል በመከለስ ሜቴክ ኤሌክትሮኒካል ሥራዎችን እንዲይዝ የተደረገው፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለምንም መስተጓጎል ተገንብቶ እንዲጠናቀቅና በዚህም የአገሪቱን አቅም ለማስተዋወቅ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የህዳሴው ግድብ የማንኛውም የውጭ አካል መጫወቻ ሊሆን አይችልም፤›› ያሉት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ በጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ላይ የውጭ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የፈጸሙትን እኩይ የተባለ ተግባር አስታውሰዋል፡፡

ግድቡ ፋይናንስ እንዳያገኝና ለግድቡ ግንባታ የገቡ ኩባንያዎችን በማስወጣት ጭምር፣ ግንባታው ሁለት ዓመታት እንዲዘገይ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን እያከናወነ የሚገኘው ሳሊኒ ኩባንያ ባይሆን ኖሮ ሊያስወጡት ይችሉ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ ሜቴክ በመኖሩ ግን ግንባታው ሊቋረጥ እንደማይችል መረዳት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ሳሊኒን ከግንባታው ለማስወጣትም ያልተሞከረ ነገር እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡

ሜቴክ በኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ላይ ባካሄዳቸው ማሻሻያዎች የግድቡ የማመንጨት አቅም ወደ 6,450 ሜጋ ዋት ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል፡፡ በግድቡ ዲዛይን ሳይቀር አንድ ተጨማሪ ተርባይን በማስገባት አጠቃላይ የተርባይኖቹ ቁጥርን ወደ 16 ማድረስ መቻሉንም አብራርተዋል፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...