Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ድርቅ የሚፈጃቸው ሀብቶች

የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን በድርቅ የመታው ክስተት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦችን ለምግብ ዕርዳታ ዳርጓል፡፡ አካባቢው በተደጋጋሚ ለድርቅ አደጋ መጋለጡ የተለመደ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳንና በኡጋንዳ የተከሰተው ድርቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው የሌሎችን እጅ ጠባቂ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል፡፡ በተለይ አዲሲቷ አገር ደቡብ ሱዳን ድርቁ የከፋ በመሆኑ ወደ ረሃብ መሸጋገሩ ታውጇል፡፡ በኢትዮጵያም ከቀደመው ዓመት ቀጥሩ በግማሽ የሚቀንስ ሕዝብ ለችግር የዳረገ ድርቅ ተከስቷል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በርካታ አርብቶ አደሮች የሚኖሩባቸው፣ ከቀንድና ከጋማ ከብቶች ጋር የተሳሰረ ሕይወት ያላቸው በርካታ ሕዝቦች የሚገኙባቸው ናቸው፡፡ ድርቁም በርካታ በቀንድ ከብት ሀብታቸው የሚታወቁትን አካባቢዎች አዳርሷል፡፡ ድርቁ በሰዎች ላይ ያንዣበበ ብቻም ሳይሆን እንደ ወትሮው አንጡራ ሀብቶቻቸውን የሆኑትን ከብቶች መንጠቅ ጀምሯል፡፡ ከሰሞኑ እንደሰማነውም ድርቁ ያገኛቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ከብቶች እየሞቱ ነው፡፡

ይህ መሆኑ የኢትዮጵያንም ሆነ የአጎራባቾች አገሮች ዜጎችን ጉዳት ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ መንግሥታቱም ሆኑ የውጭ ዕርዳታ ሰጪዎች ቀዳሚ ትኩረት የሰው ሕይወትን ማትረፍን ነው፡፡ ይህ ተገቢና ዋናው ተግባር ቢሆንም ለሚሊዮኖች የህልውና እና የሀብት ምንጭ የሆኑትን ከብቶች ለመታደግ የሚደረገው ርብርብ ቀዝቃዛ መሆን ግን ድርቁ ጥሎት የሚያልፈው ጉዳት ነገም እንደሚያገረሽ የሚያመላክት ነው፡፡

ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በአካል ተዘዋውሮ መመልከት እንደቻለው፣ በርካታ ከብቶች በመኖና በውኃ ዕጦት አልቀዋል፡፡ ቅድመ ትንበያዎችን ተጠቅሞ መኖና ውኃ ወዳለበት አካባቢ ማሻገር ባለመቻሉ በርካታ አርብቶ አድሮች ተጎድተዋል፡፡ ከድርቁ የተረፉ ከብቶቻቸውን ሸጠው ለመጠቀም ያልቻሉ ተጎጂዎችም ቁጥር ቢሆን ቀላል አይደለም፡፡ ወደ ገበያ ለመውሰድና የተጎዱ ከብቶችን ለማጓጓዝ ሲሞክሩ፣ ከመንገድ የቀሩባቸውን በርካቶች ነበሩ፡፡ በዘንድሮው ድርቅ ግን ይህ መደገም አይኖርበትም፡፡ በድርቁ ሳቢያ ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ከብቶቹ እያለቁ እንደሚገኙ እየሰማን ነው፡፡

በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቁ አካባቢዎችና ከብቶች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ወይም ከብቶቹን መኖና ውኃ ወደሚያገኙበት አካባቢ በመውሰድ ሕይወታቸውን ማቆየት ቢቻልም፣ ይህ አሠራር በቂ ወይም ዘላቂ መፍትሔ ግን አይደለም፡፡ ከብቶችን አርደው ለምግብነት እንዲውሉ ማድረግም ቢሆን ውጤቱ አነስተኛ ነው፡፡ ከብቶቹ ከሚሞቱ በማለት ገበያ ለማውጣት የሚከሩትም የሚቀርብላቸው ዋጋ እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም፡፡ ብዙ ሺሕ ብር ያወጣሉ የተባሉ ከብቶች ጥቂት መቶ ብሮች ይቆረጥላቸዋል፡፡ ድርቅ ሲከሰት ቀድሞ ዝግጅት ተደርጎ፣ ከብቶቹን በቶሎ ለገበያ አቅርቦ፣ በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር በቋሚነት ሊተገበር ባለመቻሉ የከብቶች እልቂት ሊያባብስ ይችላል፡፡ የአየር ንብረትና የአየር ፀባይ ለውጥ ቅድመ ትንቢያዎችን በተገቢው መንገድ በማሰራጨት፣ ዜጎች ከብቶቻቸው ለጉዳት ከመዳረጋቸውና ከማለቃቸው በፊት ቀድመው ለገበያ እንዲያወጡ ማድረግ አንዱ የመከላከል ዘዴ ሊሆን ይገባል፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመው አርብቶአደሮች ለሽያጭ የሚያወጧቸው ከብቶች የወደቀ ዋጋ በሚሰጧቸው ደላሎች እጅ እንደወድቁ፣ ከብቶቹን በጥሩ የገበያ ዋጋ ተረክቦ ወደ ሸማቾች የሚያደርስ አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ በተለይ ዘመናዊ የሥጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን መገንባት ግድ ይላል፡፡

ይህ አርብቶ አደሩን ጉዳት እንዲቀንስ ለማድረግ ከማስቻልም በላይ የምግብ ማቀነባበሪያዎችን ለማስፋፋት እንዲሁም የተቀነባበሩ የእንስሳት ተዋጽዖና የሥጋ ምርቶችን ለሸማቹ በሚስማማ ጥሩ ዋጋ የሚያቀርቡበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ ድርቅ በከፋበት ወቅት እንዲህ ያሉ አሠራሮች መኖራቸው በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ራሳቸውንም ከብቶቻቸውም ከጉዳት ለማዳን ያስችላሉ፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን በተሻለ ዋጋ የሚሸጡ ከብቶች በአንድ ሺሕ ብር የሚገዛቸው እንዲያጡ እየሆነ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ከብቶች ከመሞታቸው በፊት አለያም ያልተገባ ዋጋ በሚሰጡ ደላሎች ባለንብረቶቹ እንዳይጭበረበሩ ለመታደግ የተለየ የገበያ ትስስር መፈጠር ይኖርበታል፡፡

ሕይወት የማዳን ሥራው መካሄድ ያለበት ከብቶቹ በሞትና በሕይወት መካከል ከሆኑ በኋላ ሳይሆን ቅድመ ትንቢያዎችን መሠረት ባደረገና በዚያ በሚታገዝ ዕርምጃ መሠረት ነው ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ትልቅ ቦታ አለው፡፡

አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች በግብይቱ ውስጥ አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖዎች ይፈጥራሉ፡፡ እዚህ ላይ መጥቀስ የሚገባው በአገሪቱ የሚገኙት የሥጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ከሁለት እንደማይበልጡ ነው፡፡ አቅማቸውም አነስተኛ ነው፡፡ እንደ ባለሙያዎች ዕምነት የሥጋ ማቀነባበሪያዎች (በብዛት የታሸገ ምግብ የሚያመርቱ) ለምርታቸው የሚፈልጉት የሥጋ ዓይነት ያልሰባ ወይም የከሳ ከብት ሥጋ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በድርቅ የሚጎዱ ከብቶች ዋጋ እንዲኖራቸው ለማድረግ መልካም አጋጣሚ ስለሚሆን ተጨማሪ የሥጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን መገንባትና የገበያ ትስስር የሚፈጠርበትን መንገድ ማመቻቸት ድርቁ የሚፈጥረውን አደጋ መቀነስና አዳዲስ ቢዝነሶችንም የመፍጠሪያ ዕድል በመሆኑ ሊተኮርበት ይገባል፡፡ የገበያ ትስስሩ ጥቅም ላይ ብቻም ሳይሆን ከእነዚህ ከብቶች ታሳቢ የሚደረጉ የቆዳና ሌጦ አቅርቦትም እንዲዳብር፣ ዋጋ እንዲኖራቸው እንዲሻሻል ሊረዳ ስለሚችል ቢታሰብበትስ?

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት