Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቱርክና የግብፅ ታዳሚዎች ሲጠበቁ የቀሩበት የንግድ ዓውደ ርዕይ 180 ኩባንዎችን አሳትፏል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በየዓመቱ በቋሚነት ከሚዘጋጁ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ውስጥ አንዱ ‹‹አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት›› እየተባለ የሚታወቀው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ንግድ ትርዒት በዚህ ስያሜው ላለፉት 20 ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ዘንድሮም ለ21ኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ሐሙስ፣ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፍቷል፡፡

180 የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የተሳተፉበት የዘንድሮው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትን የከፈቱት የንግድ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አሰድ ዘይድ ናቸው፡፡

ካለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት አንፃር ሲታይ በ21ኛው የንግድ ትርዒት ወቅት የተሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች ቁጥር ቢቀንስም፣ ከ27 አገሮች የተውጣጡ ኩባንያዎች እንደታደሙበት ተጠቅሷል፡፡ በዕለቱ እንደተገለጸው ዘንድሮ በንግድ ትርዒቱ ከሚጠበቁ የውጭ ኩባንያዎች መካከል ተሳትፏቸው ከቀነሱባቸው ምክንያት አንዱ በርካታ ኩባንያዎችን ሲያሳትፉ የቆዩት ቱርክና ግብፅን የመሰሉ አገሮች ዘንድሮ ኩባንያዎቻቸውን ባለመወከላቸው ነው፡፡ በንግድ ትርዒቱ መክፈቻ ሥርዓት ወቅት የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳም ይህንኑ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹በቀደሙት ዓመታት በአዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ወቅት ከጎናችን ባለመለየት ሲሳተፉ የነበሩት የቱርክ ባለሀብቶች በአገራቸው ባለው ሁኔታ ምክንያት መሳተፍ ስላልቻሉ የተሰማን ሐዘን ጥቅል ነው፤›› በማለት የቱርክ ኩባንያዎች ያልተገኙበትን ምክንያት ገልጸዋል፡፡   

የግብፅ ኩባንያዎችም በዘንድሮው የንግድ ትርዒት ወቅት ላለመሳተፋቸው ምክንያት እንዳላቸው በንግግራቸው የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ በቀጣዩ ዓመት በሚዘጋጀው 22ኛው ትርዒት ላይ በትላልቅና በርካታ ቁጥር ባላቸው ኩባንያዎች እንደሚወከሉ ከወዲሁ ማስታወቃቸውን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ኩባንያዎች አለመሳተፍ በአገሪቱ ትልቅ ከሆኑት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች አንዱ እንደሆነ በሚጠቀሰው ዝግጅት ላይ የተገኙ የውጭ ኩባንያዎችን ቁጥር 100 ብቻ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህም ከአምናው የውጭ ኩባንያዎች ተሳታፎ አንፃር ሲታይ በ31 መቀነሱን አቶ ጌታቸው አመላክተዋል፡፡

ይህም ሆኖ ዘንድሮ የመጡት ተሳታፊዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ከማስተዋወቅ ባሻገር የእርስ በርስ ግንኙነት የሚፈጥሩበት መድረክ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የንግድ ትርዒትም ሆነ በሌሎች ንግድ ምክር ቤቱ በሚያካሂዳቸው ተግባራት ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲበረታታ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲሳብ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

በተለይ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና የንግድ ለንግድ ግንኙነት እንዲጎለብት የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በማስተሳሰር የንግድ ትርዒቱ እንደ ድልድይ እያገለገለ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

21ኛውን የንግድ ትርዒት የከፈቱት የንግድ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አሰድ ዘይድ ባደረጉት ንግግር ወቅት አፅዕኖት የሰጡት፣ ዓለም አቀፋዊውን የንግድ ውድድርና ግሎባላይዜሽን የተመለከተ አካሄድ መከተልና እንደሚገባ ነው፡፡ በተለይ በዘመነ ግሎባላይዜሽን ፈጣን ለውጦች እየታዩ ከመሆኑ አንፃር፣ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ከዓለም እኩል ይራመዳሉ ወይ? የሚለው ጉዳዩ ሊታሰብበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የትኛውም ኩባንያ ከዓለም አቀፍ የገበያ ውድድር ውጭ ሊሆን እንደማይችል በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ ኩባንያዎችም ከዚህ ውጭ ስለማይሆኑ በዓለም የሚታዩትን ለውጦችን እንዲያጤኑ ጠይቀዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንደምትሆን የገለጹት አቶ አሳድ፣ በዓለም የንግድ ማዕቀፍ መሠረትም  የንግድ ድርጅቶች ሊገዙበት የሚገባ ሕግ እንደሚወጣ በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡  

ይህ ሕግም የዓለም የንግድ ድርጅት ሕግጋቶችን መሠረት በማድረግ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ ያሉ ቢዝነሶች የሚተዳደሩበት መሆኑን በመጥቀስ፣ ለዚህ ዝግጁ መሆን እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የመንግሥት ስትራቴጂያዊ አጋር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማበረታት እንዲሁም የአባላቶቹን አቅም ለማጎልበት ኃላፊነቱን እየተወጣና ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ከሚያስችለው አንዱ የንግድ ትርዒት ዝግጅቱ ስለመሆኑ ተናግሯል፡፡

ይሁን እንጂ ንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒቱን በሚፈለገው የጥራት ደረጃ ለማስጓዝ ያልቻለ ስለመሆኑ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ለዚህም አንዱ ምክንያት ደረጃውን የጠበቀ የኤግዚቢሽን ሥፍራ አለመኖር ነው፡፡

ለንግድ ትርዒቱን በተሻለ ጥራትና ደረጃ ለማዘጋጀት የንግድ ትርዒት ማሳያ ቦታ ክፍተትን ለመቅረፍ ደግሞ ንግድ ምክር ቤቱ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽና ኮንቬንሽን ማዕከል ለመገንባት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም አስታውሰዋል፡፡ ለዚህም ግንባታ መንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ጭምር አጋርነቱን እንዳሳየ ከሚኒስቴር ዴኤታው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዕለቱ ንግድ ምክር ቤቱን በመወከል ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኮንንም የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽንን ዘመናዊ ለማድረግና ለማስፋት ከአንድ የስፔን ኩባንያ ጋር የተጀመረውን ሥራ አንስተዋል፡፡

በሐሙሱ የንግድ ትርዒት መክፈቻ ላይ ከወትሮ የተለየ ሆኖ የታየው የንግድ ትርዒቱ መክፈቻ ላይ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አለመገኘት ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ በተከታታይ ባደረጋቸው የንግድ ትርዒቶች የመክፈቻ ሥርዓቱ ላይ በየወቅቱ በነበሩ የንግድ ሚኒስትሮችና በንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የሚከፈት ሲሆን፣ በዘንድሮው የንግድ ትርዒት ላይ ይህ አልተስተዋለም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች