Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ለአርብቶ አደሮች የመድን ሽፋን ድጎማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ በኦሮሚያ በድርቅ ሳቢያ ከብቶቻቸውን ያጡ 1000 አርብቶ አደሮች ካሳ ተቀብለዋል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገሪቱ በየጊዜው በሚከሰተው ድርቅ ሳቢያ የከብት ሀብቶቻቸውን እያጡ የሚገኙት አርብቶ አደሮች፣ የሚደርስባቸውን ጉዳት መቋቋም እንዲችሉ ታስቦ የተጀመረው የመድን ሽፋን በመላ አገሪቱ ማዳረስ እንዲቻል መንግሥት ድጋፍ እንዲሰጥ ተጠይቋል፡፡ በአገሪቱ ከ10 ሚሊዮን ያላነሱ አርብቶ አደሮች ቢኖሩም ለከብቶቻቸው የመድን ሽፋን ማግኘት የቻሉት ግን ከሚታሰበው በታች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ናቸው፡፡

የካቲት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከብቶቻቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው የቦረናና የምዕራብ ጉጂ ዞን አካባቢ ለሚገኙ 1,474 አርብቶ አደሮች የ1.6 ሚሊዮን ብር የመድን ካሳ ክፍያ ከፍሏል፡፡ በያቤሎ ከተማ በተደረገው ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተገለጸው፣ በክልሉ የከብት ሀብት የመድን ዋስትና ሽፋን የሚሰጠው ለረዥም ጊዜ በተሰበሰበ የአየር ሁኔታ መረጃና በተጠና ቀመር ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡

በመሆኑም አርብቶ አደሮች አገልግሎቱን ለማግኘት በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለት የዝናብ አጠር የበጋ ወቅቶች ለከብት መኖ የሚያወጡትን ወጪ ከሰበታ እስከ 11 በመቶ የሚደርስ ግምት በዓረቦን መልክ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ለሪፖርተር ያብራሩት፣ በዓለማቀፉ የከብት ሀብት ምርምር ተቋም ረዳት ተመራማሪ አቶ ዋቆ ጎቡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ረዥም ደረቃማ ወቅት ተብሎ በሚጠቀሰውና ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት አራት ወራት ውስጥ ለሚቆየው ጊዜ እንዲሁም ከየካቲት እስከ ሚያዝያ መጨረሻ ባሉት ሦስት ዝናብ አጠር በሆኑ ወራት ውስጥ የአርቶ አደሩ አካባቢ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል እንዲረዳ የመድን ሽፋን እየቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ደረቃማ በሆኑ ወቅቶች ከዚህ ቀደም ለሞቱ ከብቶች ምትክ እንዲሆን ተብሎ በሚሰጠው የመድን ሽፋን ፈንታ በሕዝቡ ጥያቄ ከብቶቹ ከማለቃቸው በፊት ለመኖ፣ ለውኃና ለሌሎች ግብዓቶች ማሟያ የሚውል እንዲሁም ቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ የመድን ሽፋን እየተሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ በኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የከብት ሀብት ዋስትና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጌታነህ ኢሬና እንዳብራሩት ከሆነ፣ የዓረቦን ክፍያው ለምሳሌ አንድ ግመል በሁለቱ ደረቃማ ወቅቶች የ5,000 ብር መኖ የሚፈልግ ሲሆን፣ ፍየልና በግ ደግሞ የ500 ብር መኖ ያስፈልጋቸዋል። አንድ በሬ ወይም ላም በአማካይ እስከ 3,000 ብር የሚገመት መኖ ሊያፈልጋቸው እንደሚችል ታሳቢ ተደርጎ፣ ቢዚያ ሥሌት መሠረት ክፍያው እንደሚጠየቅ አቶ ጌታነህ አብራርተዋል። በዚህም ሥሌት መሠረት ለአምስት በሬዎች ዋስትና መግዛት የሚፈልግ አርብቶ አደር የ3,000 ብርን ሰባት በመቶ ሲባዛ በአስምት በማድረግ በድምሩ 1,050 ብር ፕሪሚየም መክፈል ይጠበቅበታል ማለት ነው።

      በየአካባቢው ባሉ አሥር የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ አርብቶ አደሮች የከብት ሀብት ዋስትና ሽፋን ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን አገልግሎት ለማግኘት የቅድሚያ ክፍያ (የፕሪሚየም) መፈጸም ቢጠበቅባቸውም የመክፈል አቅም ስለሌላቸው፣ ሲፋ ኢትዮጵያ የተባለ አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ትሮኬር ከተባለ የውጭ ተቋም በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ አማካይነት እስከ 35 በመቶ የሚደርሰውን የዓረቦን ክፍያ ከአሥሩ ወረዳዎች በሁለቱ ውስጥ ለሚገኙ አርብቶ አደሮች በድጎማ መልክ እየሸፈነላቸው እንደሚገኝ አቶ ጌታነህ  ጠቅሰዋል።  

አርብቶ አደሮቹ አንጡራ ሀብታቸው ለሆኑት ከብቶች ዋስትና ማግኘት መቻላቸው መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታነህ፣ ‹‹የክልልና የፈዴራል መንግሥታት እንደዚህ ዓይነት ድጎማ ማድረጉን ከግምት ውስጥ ቢያስገቡ የዋስትናው ተጠቃሚ አርብቶ አደሮችን ቁጥር በማሳደግና ከድርቅ አደጋ ተጋላጭነት ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፤›› በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ ዋቆም በዚህ ይስማማሉ፡፡ መንግሥት ለአርብቶ አደሮች የመድን ክፍያ ድጎማ ቢያቀርብ፣ ደጋግሞ እየተከሰተ የበርካታ እንስሳትን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን ድርቅ በተሻለ አቅም ለመለካከል የሚችሉበት አቅም እንዲጠናከር ሊያግዛቸው እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

የኬንያን ተሞክሮ የጠቀሱት አቶ ዋቆ፣ የኬንያ መንግሥት ባደረገው የመድን ሽፋን ድጎማ መሠረት 20 ሺሕ አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገና 40 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጎማ በመስጠቱ እስከ አራት ከብቶች ያሏቸው አርብቶ አደሮች የመድን ሽፋኑን በነፃ ማግኘት እንዲችሉ አግዟቸዋል፡፡ ይህም ማለት ከአራት በላይ ከብቶች ያሏቸው በራሳቸው የመድን ሽፋን እንዲፈጽሙ የሚጠይቅ አሠራር ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ይህ ቢተገበር በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡ በሰብል ላይ ለሚደርስ ጉዳት መንግሥት የመድን ሽፋን ድጎማ በመስጠቱ ይህ ዕድል ለአርብቶ አደሮችም እንዲደርሳቸው መደረጉ ድርቅን በመቋቋም ከብቶች ሳይሞቱ እንዲቆዩ ለማገዝ እንደሚረዳም አቶ ዋቆ አክለዋል፡፡

በከብቶች ላይ ለሚደርስ ጉዳት ካሳ ማግኘት የሚያስችል የመድን ሽፋን አገልግሎት ለኦሮሚያ አርብቶ አደሮች መስጠት የተጀመረው በ2004 ዓ.ም. በኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያና በዓለም ዓቀፍ የከብት ሀብት ምርምር ተቋም ትብብር አማካይነት ነበር። የከብት ሀብት መድን ፕሮጀክት ሐሳብን ያመነጨው የምርምር ተቋሙ፣ ከአሜሪካው የጠፈር ምርምር ድርጅት (ናሳ) የሚያገኘውን የከባቢ አየር ሁኔታና የአየር ንብረት ለውጦችን የሚመለከቱ ዝርዝር መረጃዎች አጠናቅሮ ለኢንሹራንስ ኩባንያው በማቅረብና ጥናት በማካሄድ እየተሳተፈ ይገኛል።

       በሁለቱ ድርጅቶችና ተባባሪዎቻቸው አጋርነት የሚካሄደው የአካባቢና የአየር ንብረት ሁኔታን በመከታተል፣ ለውጦች ሲከሰቱ በከብቶች መኖ ይዘት፣ በመኖ እጥረትና በሌሎች ተጓዳኝ ሁኔታዎች ላይ የሚታዩትን ባህርያት ገምግሞ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በመከላከል ላይ ተመሥርቶ የሚሰጠውን የመድን ዋስትና ከብቶቻቸው ከሞቱባቸው አርብቶ አደሮች ባሻገር ከብቶቻቸው ለከፍተኛ አደጋ የተጋልጡባቸውንም ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። የዋስትና ሽፋኑም ላም፣ በሬ፣ ግመል፣ በግና ፍየልን የሚያካትት መሆኑን አቶ ጌታነህ ጨምረው ገልጸዋል።  ይህንኑ የዋስትና ዓይነት የበለጠ በማዘመንና በማስፋፋት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለማሻሻል ባለው ዕቅድ መሠረት፣ የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ አገር በቀል ከሆነው ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ ኩባንያ ጋር በመተባበር የከብት ሀብት ዋስትናን ወደ ሌሎች አርብቶ አደር አካባቢዎች ለማስፋፋትና የበለጠ የተቀላጠፈ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሯል።   

      ካሳ የተከፈላቸውን 1,474 አርብቶ አደሮችን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል ቦረናና ምዕራብ ጉጂ ዞን የሚገኙ 4,588 አርብቶ አደሮች በዚህ የከብት ሀብት ዋስትና አገልግሎት ታቅፈዋል። የመድን ዋስትና አገልግሎቱ ከተጀመረ ጀምሮ ለአራተኛ ዙር ክፍያ ተፈጸመ ሲሆን፣ ዓላማውም ተጠቃሚ አርብቶ አደሮች ከደረሰባቸው ጉዳት በፍጥነት ማገገም እንዲችሉ ማገዝ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች