Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቱርክ ትምህርት ቤቶች ለጀርመን ባለሀብቶች በሽያጭ እንደተላለፉ መሥራቾቹ አስታወቁ ለቱርክ መንግሥት እንደሚተላለፉ መንግሥት አስታውቆ ነበር

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቱርክ ባለሀብቶች የተመሠረቱትና ነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ኢንተርናሽናል በሚባል ስያሜ የሚታወቁት ትምህርት ቤቶች ይዞታ፣ ወደ ጀርመን ባለሀብቶች በሽያጭ መዛወሩን የትምህርት ቤቶቹ መሥራቾች  አስታወቁ፡፡ ይህ የሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት ለቱርክ መንግሥት ትምህርት ቤቶቹን አሳልፎ እንደሚሰጥ ካስታወቀ ከቀናት በኋላ ነው፡፡

ትምህርት ቤቶቹ የሚተዳደሩት በቱርክ መንግሥት በአሸባሪነት ከተፈረጀው የፈቱላህ ጉለን ንቅናቄ ጋር ግንኙነት ባላቸው ቱርካውያን እንደሆነ በመጥቀስ፣ የቱርክ መንግሥት ትምህርት ቤቶቹ እንዲዘጉለት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ሲወተውት ቆይቷል፡፡ ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ ለዘለቀው የቱርክ መንግሥት ጥያቄ በቅርቡ ምላሽ የሰጡት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ለሳምንት በዘለቀው የቱርክ ጉብኝታቸው ወቅት ይህንኑ ማረጋገጣቸው ታውቋል፡፡

ከቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲይፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር በአንካራ በሰጡት መግለጫ ፕሬዚዳንት ሙላቱ እንዳስታወቁት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ትምህርት ቤቶቹን ለቱርክ መንግሥት ከማስተላለፍ በተጨማሪ በፀረ ሽብር ተግባራትም አብሮ ይሠራል፣ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ የቱርክ መንግሥት ማሪፍ ፋውንዴሽን የተባለ መንግሥታዊ የትምህርት ተቋም በመመሥረት የፈቱላህ ጉለን ንቅናቄ አባላት ያስተዳድሯቸዋል ያላቸውን ትምህርት ቤቶች ለመንጠቅ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በተለይ የአፍሪካ መንግሥታት ለዚህ እንዲተባበሩት ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡

በዚህ ደረጃ የሚገኘው የትምህርት ቤቶቹና የቱርክ መንግሥት ጉዳይ ላይ ዝምታን መርጦ የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት ትምህርት ቤቶቹን ለቱርክ እንደሚያስተላልፍ ባስታወቀ ማግሥት፣ የትምህርት ቤቶቹ መሥራቾች ለጀርመን ባለሀብቶች ማስተላለፋቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

ካይናክ የትምህርትና የሕክምና አገልግሎት የተባለውን ኩባንያ በምክትል ሥራ አስኪያጅነት የሚመሩትና የነጃሺ ኢትዮ ቱርኪሽ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጉዳይ አስተባባሪው ከሊል አይዲን ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ሽያጩ የተከናወነው ቀድሞውንም ትምህርት ቤቱ በነበረው ዕቅድ መሠረት ነው ብለዋል፡፡

‹‹ምንም ዓይነት የመንግሥት ተፅዕኖ ወይም ጥያቄ ሳይቀርብልን በራሳችን አጀንዳ መሠረት ጠንካራ የፋይናንስና የአውሮፓ የትምህርት ጥራትን ወደ አገሪቱ ለማምጣት በማሰብ የተደረገ ነው፤›› በማለት የገለጹት አይዲን፣ ‹‹የጀርመንን የቢዝነስና የትምህርት ሥርዓት በኢትዮጵያ ለማስፋፋት የወሰድነው ዕርምጃ ነው፤›› ብለዋል፡፡  ይሁንና በምን ያህል መጠን ትምህርት ቤቶቹ ለጀርመን ባለሀብቶች እንደተላለፉ፣ የጀርመን ባለሀብቶች የተባሉት እነማን እንደሆኑ ለተጠየቁትም በቅርቡ ዝርዝር መግለጫ እንደሚሰጥበት ገልጸዋል፡፡

በጀርመኖች ይዞታ ሥር የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ከዚህ ቀደም የሚሰጧቸው ትምህርታዊ ይዘቶች ላይ ለውጥ እንደሚደረጉ የገለጹት አይዲን፣ ከእነዚህ መካከል የቱርክ ቋንቋ በጀርመንኛ እንደሚተካ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የስያሜ ለውጥን ጀምሮ የአስተዳደርና ሌሎች ለውጦች እንደሚደረጉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከበርካታ አገሮች የተውጣጡ ከ1,700 ያላነሱ ታዳጊዎችን በአዲስ አበባና በመቐለ ከተሞች የሚያስተምሩት ነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ትምህርት ቤቶች ወደ ቱርክ መንግሥት ይተላለፋሉ ከተባለ በኋላም ቢሆን፣ ትምህርት እየሰጡ እንደሚገኙና ከመንግሥትም እስካሁን የደረሳቸው ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያም ሆነ ጥያቄ እንደሌለ አይዲን ገልጸዋል፡፡ ይልቁንም በአገሪቱ ሕግ መሠረት የሚንቀሳቀሱ መደበኛና ለትርፍ የተቋቋሙ ትምህርት ቤቶችን እየመሩ እንደሚገኙ በመግለጽ፣ ከቀናት በፊት ፕሬዚዳንት ሙላቱ በቱርክ ቆይታቸው ወቅት ስለሰጡት መግለጫ አስተያየት ከመስጠት መቆጠባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች