Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ አስተዳደር በመልሶ ማደራጀትና በጥፋተኞች ላይ ዕርምጃ ሲወስድ መቆየቱን ገለጸ

የአዲስ አበባ አስተዳደር በመልሶ ማደራጀትና በጥፋተኞች ላይ ዕርምጃ ሲወስድ መቆየቱን ገለጸ

ቀን:

-የመልሶ ማልማት ፕሮግራም ለጊዜው ቆሟል      

– የተጠናቀቁ 40/60 ቤቶች በመጋቢት ወር ይመረቃሉ ተብሏል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የካቲት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የከተማው አስተዳደር ያለፉትን ስድስት ወራት በጥልቅ ተሃድሶ ስብሰባዎች፣ በመልሶ ማደራጀትና በጥፋተኞች ላይ ዕርምጃ በመውሰድ ማሳለፉን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ገለጹ፡፡

ከንቲባ ድሪባ የከተማውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ከማቅረባቸው በተጨማሪ፣ ለተነሱ ጥያቄዎች ከካቢኔ አባላት ጋር በመሆን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከንቲባው በሪፖርታቸው እንደገለጹት፣ ባለፉት ስድስት ወራት የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ከወረዳ እስከ ማዕከል ያሉ አመራሮችና የከተማ አስተዳደሩ 75 ሺሕ የሚሆኑ ሠራተኞች በጥልቅ ተሃድስ ግምገማ እንዲያልፉ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአመራር ለውጥና የመልሶ ማደራጀት ሥራም ተሠርቷል ብለዋል ከንቲባ ድሪባ ኩማ፡፡

‹‹በከተማ በተዘጋጀው የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ከ160 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የምክር ቤት አባላት፣ አደረጃጀቶችና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተገኙባቸው ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል፤›› ሲሉ ከንቲባ ድሪባ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ ሥራዎች ተጠምዶ ያሳለፈው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙሉ ኃይሉ ወደ መደበኛ ሥራው የገባው በጥር ወር አጋማሽ ነው፡፡ በግማሽ ዓመቱ የተሠሩ ሥራዎች አፈጻጸም ከዚህ አንፃር ደካማ ብቻ ሳይሆን፣ ክፍተቶችም እንዳሉባቸው ተገልጿል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አፈ ጉባዔ ዶ/ር ታቦር ገብረ መድኅን የምክር ቤቱን የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴዎቹ አማካይነት ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ክትትል አድርጓል፡፡

አንዳንድ ፕሮጀክቶች የአስተዳደር፣ የክትትልና የሀብት ብክነት ችግር እንዳለባቸው፣ ለወረራና ለሕገወጥ ተግባራት የተጋለጡ ክፍት ቦታዎች መኖራቸው፣ ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች መኖራቸውም በክትትል ወቅት እንደታዩ አፈ ጉባዔው ገልጸው፣ ከሥራ አስፈጻሚ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ የሁለት ወራት የማስተካከያ ጊዜ እንደተሰጠ አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር ታቦር ጨምረው እንደገለጹት፣ የቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሪፖርት እንዲያቀርብ ቢጠየቅም ሪፖርቱን አላቀረበም፡፡ ይህ እንደ ተሞክሮ እንዳይወሰድ በመጥቀስ ቢሮውን ወቅሰዋል፡፡

በአስተዳደሩ መደበኛ ስብሰባ ጎልተው ከወጡ ጉዳዮች መካከል የመልሶ ማልማት፣ የቤቶች ልማት፣ የመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ይገኙበታል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመሩ የመልሶ ማልማት ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ ጠቅላላ ስፋቱ 186 ሔክታር የሆነ የመልሶ ማልማት መሬት በተለያዩ ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት ሊገባ አልቻለም፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ያረፉ 1,228 ቤቶችን ለማፍረስ ታቅዶ፣ ማፍረስ የተቻለው 773 ቤቶች ብቻ ነው፡፡ በዚህም ነፃ ማድረግ የተቻለው 47 ሔክታር መሬት ብቻ ነው፡፡ የዚህ ችግር ማጠንጠኛዎች በርካታ ቢሆኑም በዋናነት ግን ለተነሺዎች በቂ ካሳና ተመጣጣኝ ምትክ ቦታ አለማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአስተዳደሩን አካሄድ ያልወደዱ ነዋሪዎች የፍርድ ቤት ዕግድ በማውጣት ወደ ሕግ የሚሄዱ በመሆናቸው፣ አሮጌ መንደሮችን ማልማት ሳይችል ለዓመታት ታጥረው እንዲቀመጡ አድርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመልሶ ማልማት ፕሮግራም የሚነሱ የከተማው ነዋሪዎች ቅሬታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ጉዳዩን በድጋሚ ለማጤን ተገዷል፡፡ በፌዴራል ደረጃም ይህ የተነሺ የነዋሪዎች ጉዳይ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ የኢትዮጵያ የፖሊሲና የምርምር ማዕከል ጥናት አካሂዷል፡፡ በዚህ ጥናትም ጉዳዩ ቆም ተብሎ እንዲታይና በልማት ምክንያት የሚነሱ ነዋሪዎች ተደስተው መነሳት እንጂ፣ ተከፍተው መነሳት የለባቸውም የሚል ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀደም ብሎ የጀመረውን የመልሶ ማልማት ፕሮግራም ቆም ብሎ በመመርመርና በዚህ ዓመት ያቀደውን ለጊዜው ለማቆም ወስኗል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ለዓለም ተሠራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ ዓመት 360 ሔክታር መሬትና 20 ሔክታር የወንዝ ዳር ልማት ለማካሄድ ታቅዶ ነበር፡፡ ‹‹የጀመርነውን መልሶ ማልማት በአግባቡ ለማጠናቀቅ ዕቅዳችንም ከዚህ አንፃር እንዲቃኝ ተወስኗል፤›› ሲሉ አቶ ለዓለም የ300+20 ሔክታር መሬት ጉዳይ ለጊዜው እንዲቆም መደረጉን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ የቤቶች ልማት ነው፡፡ የቤቶች ልማት ደካማ የሥራ አፈጻጸም፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር፣ ሙስናና ዝርክርክ አሠራር አለ ተብሎ በምክር ቤት አባላት ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ከንቲባ ድሪባ በሪፖርታቸው እንዳስቀመጡት፣ በአዲስ አበባ በተለያዩ ጊዜያት የተጀመሩ 133,321 የሚሆኑ ቤቶች በሦስት ማዕቀፍ ተለይተው በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሠረት በመጀመሪያ ደረጃ ነባር ግንባታዎች 39,249 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 23,016 የ10/90 ቤቶች ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በ20/80 ፕሮግራም 16,233 ቤቶች የግንባታ ሥራቸው ተጠናቆ መሠረት ልማት እየተሟላላቸው ነው ተብሏል፡፡

በማዕቀፍ ሁለት የተካተቱ ቤቶች ደግሞ፣ ግንባታቸው ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመሩ 52,651 ቤቶች ሲሆኑ፣ የሥራ አፈጻጸማቸው 54 በመቶ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ እንዲሁም በሦስተኛው ማዕቀፍ የሚካተቱት 41,421 ቤቶች የግንባታ አፈጻጸማቸው በአማካይ 30 በመቶ መድረሱ ተመልክቷል፡፡

በ40/60 ፕሮግራም በተለያዩ ጊዜያት 39,229 ቤቶች እየተገነቡ ሲሆኑ፣ በመጀመሪያው ማዕቀፍ 1,292 ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ እነዚህ ቤቶች በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው ተጠናቆ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰነዳቸው መሰጠቱ ተገልጿል፡፡ የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታ በ40/60 ፕሮግራም በተለይ 1,292 ቤቶች ግንባታ መጠናቀቁ እየተገለጸ፣ ነገር ግን ከዛሬ ነገ ይተላለፋሉ እየተባለ ሳይተላለፉ የቀሩ ቤቶች ላይ ስለሚናፈሰው ወሬ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አቶ አባተ እንዳሉት የቤቶቹ ግንባታ ተጠናቋል፡፡ ሰነዳቸው ከባንክ ጋር ርክክብ ተፈጽሟል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት በአካል ተገኝቶ በውሉ መሠረት ስለመሠራታቸው ቅኝት እያደረገ በመረከብ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ቤቶች በመጋቢት ወር መጀመሪያ እንዲመረቁና ከዚያም ለተጠቃሚዎች እንደሚተላለፉ ገልጸዋል፡፡ አቶ አባተ ጨምረው እንደገለጹት፣ 40/60 ቤቶች ሰው ገብቶባቸዋል፣ ለባለሥልጣናት ተላልፈው ተሰጥተዋል፣ ወይም ሊሰጡ ነው ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ መሠረት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሁለተኛው ማዕቀፍ 20,932 ቤቶች በግንባታ ላይ መሆኑና አፈጻጸጸማቸው በአማካይ 64 በመቶ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህን አፈጻጸም በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ 80 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን የከንቲባ ድሪባ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በሦስተኛው ማዕቀፍ ደግሞ 17,005 ቤቶች እየተገነቡ ሲሆን፣ አፈጻጸማቸው 32 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት በቤት ልማት ሒደቱ ላይ ክትትል ማድረግ እንዳይችሉ ሪፖርት ያልተላከ መሆኑ ቢገለጽም፣ የምክር ቤት አባላቱ ግን የግንባታ ጥራት፣ ዝርክርክ አሠራርና ሙስና መንሰራፋቱን ይገልጻሉ፡፡

በዕለቱ በመልካም ጎኑ ከታዩ ጉዳዮች መካከል የአዲስ አበባ አስተዳደር ለመምህራን ቤት በኪራይ ለማቅረብ መዘጋጀቱ ነው፡፡ አስተዳደሩ ከራሱ ግምጃ ቤት 1.2 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ አምስት ሺሕ ቤቶችን ገዝቷል፡፡ እነዚህን ቤቶች ለ12 ሺሕ መምህራን እሑድ የካቲት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ዕጣ በማውጣት ለአምስት ሺሕ መምህራን ያስረክባል ተብሏል፡፡

መምህራኑ የሚከራዩአቸው ቤቶች ከአንድ ሺሕ ብር በታች በሆነ ገንዘብ መሆናቸውን፣ እነዚህን ቤቶች ለማፅዳት አስተዳደሩ 125 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ማውጣቱ ተጠቁሟል፡፡ አስተዳደሩ ይህን አሠራር ቅርፁን በማሳደግ በዚህ ዓመት ሁለት ሺሕ ቤቶችን ገንብቶ ለመንግሥት ሠራተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማቅረብ መወሰኑን፣ ከንቲባው ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ በቤት ልማት ዘርፍ ያሉ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ ሥር የሰደደውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከመንግሥትና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ንግግር ተደርጎ ችግሩ መፈታቱን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

ሌላው የከተማው አስተዳደር ችግር የመሬት ዘርፍ ነው፡፡ በመሬት ዘርፍ የተንሰራፋው ችግር ቀስ በቀስ መሻሻል ቢያሳይም፣ አሁንም በርካታ ቦታዎች ለወረራ የተጋለጡ መሆናቸውን፣ ከ13 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ባለሀብቶች የሊዝ ውዝፍ ክፍያ እንዳለባቸው፣ ከ156 በላይ የሚሆኑ ባለሀብቶችና የመንግሥት ተቋማት ለዓመታት ቦታውን አጥረው ማስቀመጣቸው በምክንያትነት ቀርቧል፡፡ አስተዳደሩ እንደተለመደው እነዚህን ለዘመናት አጥረው የያዙ ባለሀብቶች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል፡፡ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ እንዳሉት፣ ሱፐርቪዥን በተሠራበት ወቅት በአስተዳደሩ ችግር ያላለሙና በራሳቸው ችግር ያላለሙ ተለይተዋል፡፡ እነዚህ አልሚዎች ጊዜ የተሰጣቸው መሆኑንና በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ልማታቸውን ካልጀመሩ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል፡፡

ዛቻው ለዓመታት የቀጠለ በመሆኑ አስተዳደሩ ባካሄዳቸው የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ስብሰባዎች፣ ይህ አድሏዊ አሠራር ሊቀረፍ እንደሚገባ ተነስቷል፡፡ በከንቲባው ሪፖርትም ምንም ዓይነት ግንባታ ባላከናወኑ 14 አልሚዎች ላይ ውል እንዲቋረጥ መደረጉ ቢገለጽም፣ ለዓመታት በግልጽ ታጥረው በሚታዩት ላይ ምንም ዓይነት ዕርምጃ አለመወሰዱ አስገራሚ ክስተት መሆኑን የምክር ቤት አባላት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...