Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየሠራተኞች ፍልሰትን ለመቆጣጠር ለተመሳሳይ ሙያ ተመሳሳይ ደመወዝ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተጀመረ

  የሠራተኞች ፍልሰትን ለመቆጣጠር ለተመሳሳይ ሙያ ተመሳሳይ ደመወዝ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተጀመረ

  ቀን:

  መንግሥት ከአንድ መሥሪያ ቤት ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት የሚደረግ ከፍተኛ የሠራተኞች ፍልሰት በሥራ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ በመሆኑ፣ ይህን ለመግታት አዲስ አሠራር ለመዘርጋት ተዘጋጀ፡፡ በዚህም መሠረት ለተመሳሳይ ሙያ ተመሳሳይ ክፍያ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተጀመረ፡፡

  ‹‹የሥራ ምዘናና የደረጃ አወሳሰን ሥርዓት›› በሚል  እየተዘጋጀ ያለው አዲሱ አሠራር በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ለአንድ ባለሙያ ሠራተኛ የሚከፈለው ደመወዝ የተለያየ በመሆኑ፣ ይህን ማስተካከል ያስፈልጋል የሚል ሐሳብ ይዟል፡፡

  በዚህ መሠረት የፌዴራል መንግሥት የቀድሞ አሠራር መለወጥ እንዳለበት በመወሰኑ፣ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ይህን አሠራር ለመለወጥ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ ባጠናው ጥናት የሥራ መደቦችን ውስብስብነትና ክብደት በመለካት፣ ከ70 በላይ የነበረውን የደመወዝ ስኬል ወደ 22 ዝቅ ማድረጉ ታውቋል፡፡

  ከፌዴራል እስከ ታችኛው መዋቅር ቀበሌ ድረስ የነበረው ከ15 ሺሕ በላይ ደረጃ ወደ ሰባት ሺሕ ዝቅ እንዲል አድርጓል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የሠራተኛ መፍለስ ያጋጠመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከፌዴራል መንግሥት ውሳኔ በመነሳት ይህን አሠራር እስከ መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ እንደሚዘረጋ አስታውቋል፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይስሃቅ ግርማይ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ ሙያ የተዘበራረቁ የደመወዝ ክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡ የሥራ ምዘናና የደረጃ አወሳሰን ሥርዓትን በማስተካከል ለተመሳሳይ ሙያ አንድ ዓይነት ክፍያ ሥርዓት ሊኖር ይገባል ሲሉ አቶ ይስሀቅ ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ማዕከል መሆን ያለበት ሥራ ነው፡፡ ሰው ማዕከል ሊሆን አይገባም፤›› ያሉት አቶ ይስሃቅ፣ ‹‹የሥራ ምዘናና አወሳሰን መነሻ ወይም መመዘን ያለበት ሥራ መሆን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሥራ ከተመዘነ በኋላ በሥራው ውስብስብነት የሚያስፈልገው ክህሎት መነሻ ተደርጎ ደረጃዎች ይወጣሉ፡፡ ይህ ደረጃ ከተቀመጠ በኋላ የደመወዝ አመዳደብ ሥርዓት ይቀመጣል በማለት አክለዋል፡፡

  በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየሆነ ያለው የሥራ ምዘናና አወሳሰን ሥርዓት ከ44 ዓመታት በፊት በተዘረጋ አሠራር ነው፡፡ ይህ ያለፈበት በመሆኑና መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸውን ለማቆየት የተለያ የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ በማድረጋቸው፣ ወጥ የሆነ የደመወዝ አከፋፈል እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ ይህ የተዘበራረቀ አሠራር መሥሪያ ቤቶች ሠራተኛ እንዳይበረክትላቸው ወይም እንዳያገኙ እያደረገ በመሆኑ፣ በሥራ ሒደት ላይ ችግር እያጋጠመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ሠራተኞች ጠቀም ያለ ክፍያ ወደሚያገኙባቸው ተቋማት የሚጎርፉ ስለሆነ፣ ዝቅተኛ የደመወዝ ስኬል ያላቸው መሥሪያ ቤቶች ደግሞ የሰው ኃይል ነጥፎባቸዋል፡፡

  የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሠራተኞች አሏቸው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ከአመራሮች ውጪ 75 ሺሕ ሠራተኞች አሏቸው፡፡ በተለይ እነዚህ ተቋማት አብዛኛዎቹ መዋቅሮቻቸው የሰው ኃይል ያልተሟላላቸው  እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሰው ኃይል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚፈልስበት፣ በአንፃሩ ደግሞ ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር ያለበት ከተማ ናት፡፡

  የዓለም ባንክ ከወር በፊት ባወጣው አምስተኛው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፖርት፣ አዲስ አበባ ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥርትና በአንፃሩ ከፍተኛ የሰው ኃይል ፍልሰት ያለባት ከተማ መሆኗን ገልጿል፡፡ በሌላው ዓለም የሥራ አጥ ቁጥር ከፍተኛ የሆነባቸው ከተሞች ውስጥ ያሉ ሠራተኞች፣ በሥራ ደኅንነታቸው ላይ እርግጠኛ መሆን ስለማይችሉ የያዙትን ሥራ አይለቁም፡፡ በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማ ሁለቱን ክስተቶች ታስተናግዳለች፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...