Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክማቆሚያ አልባው የዳኝነት ሥርዓቱን ወደ አስፈጻሚው መዳፍ የማስገባት ጉዞ

ማቆሚያ አልባው የዳኝነት ሥርዓቱን ወደ አስፈጻሚው መዳፍ የማስገባት ጉዞ

ቀን:

ከ2008 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ፣ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት መንግሥት (አስፈጻሚው አካል) ችግሩን ለመቅረፍ በመፍትሔነት ከወሰዳቸው ዘዴዎች አንደኛው ‹‹በጥልቀት መታደስ›› ነው፡፡ ጥልቅ ተሐድሶው ችግሮቹ በተፈጠሩባቸው አካባቢዎችና ጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ላይ ብቻ አልቆመም ፡፡ 

ጥልቅ ተሐድሶው ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች በተጨማሪ የትግራይ፣ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎችና የአዲስ አበባ መስተዳደር እንዲሁም የፌዴራል መንግሥቱንም ጭምር አካልሏል፡፡ በሒደቱ ውስጥ ያለው ደግሞ አስፈጻሚው አካል ብቻ ሳይሆን የሕግ ተርጓሚውንም ያካተተባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ዳኞችን በመተው ሌሎች የፍርድ ቤት ሠራተኞችን ከፍትሕ ቢሮ (ዓቃቤ ሕጎች) ጋር በጥልቀት የመታደሱ ሒደት አካል የሆነባቸውም አሉ፡፡ በመሆኑም የአስፈጻሚው አካል የቀረጻቸው ፖለቲካዊ አጀንዳዎች የዳኝነት አካሉም እንዲተገብረው እየተደረገ ነው ማለት ነው፡፡

በእርግጥ ‹‹የፍትሕ አካላት የጋራ መድረክ›› የሚባል አሠራርም ተግባራዊ ከሆነም ሰነባብቷል፡፡ የፍትሕ አካላት የሚባሉት መደበኛ ፍርድ ቤት፣ የቀድሞው የፍትሕ ሚኒስቴር የአሁኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስና ማረሚያ ቤቶች ናቸው፡፡ ከፍርድ ቤቶች በስተቀር ሦስቱም የሕግ አስፈጻሚው አካል ናቸው፡፡ አስፈጻሚው አካል የመንግሥት ፖለሲዎችንም በተለያዩ ጊዜያት በጋራ አራቱንም ያሠለጥናል፡፡ አራቱም እርስ በርሳቸው እንዲገማገሙ ሲደረግም ቆይቷል፡፡ ነገሩ በዚህ ሳያበቃ በጥር 2009 ዓ.ም. ሕግ አስፈጻሚው አንድ የፖሊሲ ሰነድ አውጥቷል፡፡ ‹‹የሕግ ምርምርን፣ ሥልጠናን፣ የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራሞችን የሚመራ ተቋም ለማቋቋም የቀረበ የፖሊሲ ሰነድ›› የሚል ርዕስ የተሰጠው፡፡ የፖሊሲውን መውጣት በተመለከተ ጥር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. የወጣውን ሪፖርተር ጋዜጣ በዜናነት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ይህ ፖሊሲ ለማሳካት ያሰበው ዓላማ የሕግ አስፈጻሚውንና የሕግ ተርጓሚውን ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተዕፅኖ የሚፈጥር ነው፡፡

- Advertisement -

ከላይ የተጠቀሱት ሁነቶች ለዚህ ጽሑፍ እንደ መነሻ ይሁኑ እንጂ የሕግ አስፈጻሚው የሕግ ተርጓሚውን ሥልጣን በሕግም በተግባርም እየቀነሰ መውሰድ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ድርጊቱም እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ፍርድ ቤቶች በራሳቸው አሳልፈው የሰጧቸውን ወይም የተዋቸውን ሳይጨምር ነው፡፡

የዳኝነት ተቋሙ ሰብዓዊ መብትን በማስጠበቅ፣ የሕግ የበላይነትን በማስረጽና ልማድ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር፣ ሕገ መንግሥታዊነትን ከማረጋገጥ አኳያ በመጀመሪያ የራሱን ድርሻና ተልዕኮ በመወጣት ቀጥሎ ደግሞ ሕግ አስፈጻሚውና አውጪውን በተራው በመቆጣጠር ረገድ በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያደርጉ እንቅፋቶች መሆናቸው ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት የሆነው ፖሊሲው በመሆኑ ወደ እሱ እንሻገር፡፡

ፖሊሲው በአጭሩ

በሰነዱ ላይ ለፖሊሲው መውጣት በርካታ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ ታስበው የተቋቋሙት የፍትሕና ሕግ ምርምር ተቋምና የፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ማዕከል የሚጠበቅባቸውን ውጤት አለማስገኘታቸው ነው፡፡ በእርግጥ ሁለቱም ተቋማት በምርምርም ይሁን በሥልጠና ረገድ የተወሰኑ ተግባራት አከናውነዋል፡፡ የምርምር ማዕከሉ በ1990፣ ማሠልጠኛ ማዕከሉ ደግሞ በ1995 ዓ.ም. ነው የተቋቋሙት፡፡ የምርምር ማዕከሉና የማሠልጠኛው ማዕከሉ ተጠሪነታቸው ለተለያዩ ተቋማት ነው፡፡ የኃላፊነት መደራረብም ይታይባቸዋል፡፡  የሕግ መረጃንም በአግባቡ በመያዝ ለሕዝቡም ይሁን ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎች ተደራሽ እንዲሆን አላደረጉም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ የፍትሕ ኦዲት ሥራም የለም፡፡ የሕግ ትምህርት ቤቶችን የፍትሕ ማሻሻያው ፕሮግራም አካል ለማድረግ ታስቦ በቀድሞው የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ሲተገበር የነበረው ኋላ ላይ በትምህርት ሚኒስቴር ሥር በሚገኝ ከሕግ ጋር ግንኙነት የሌለው ተቋም አስተባባሪ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት ማከናወን የሚችል የምርምር፣ የሥልጠና፣ የኦዲት፣ የመረጃ ማዕከል እንዲሁም የሕግ ትምህርት ቤቶችን የሚደግፍ አንድ ተቋም ማቋቋም እንደሚስፈልግ ሰነዱ ይገልጻል፡፡ የተቋሙም ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር እንዲሆን በምክንያትነት የተገለጹት ደግሞ የተቋሙ ‹‹ውጤታማነት›› እና ‹‹ነፃነት›› ናቸው፡፡ ውጤታማና ነፃ እንዲሆን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆን አለበት ይላል፡፡ ይህ የፖሊሲ ሰነድ ላይ አስተያየት ከመስጠት አስቀድሞ መወሳት ያለባቸው ነጥቦች አሉ፡፡ የዳኝነት ነፃነት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ምናልባትም ደግሞ ይህንንም ሰነድ የበለጠ ለመረዳት የሚጠቅሙም ስለሆነ ነው፡፡

መታወስ ያለባቸው ነጥቦች

ሕግ ተርጓሚው ከአስፈጻሚው ጋር የሚኖረው የግንኙነት ሚዛን ላይ ተፅዕኖ ከሚያደርሱት ጉዳዮች አንዱ መንግሥታዊ አወቃቀር ነው፡፡ ከፕሬዚዳንታዊ ይልቅ መንግሥታዊ አወቃቀሩ ፓርላሜንታዊ መሆኑ በራሱ ለሕግ አስፈጻሚው ጉልበተኛነት እንደ አንድ ጥሩ አጋጣሚ መውሰድ ይቻላል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ተፅዕኖ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሥልጣን የያዘው አሸናፊ ፓርቲ የሚወስናቸውን ፖሊሲዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ለፓርላማ በማቅረብ ለማፅደቅ ቀላል ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አመራር የሚሰጥ ፓርቲ ሲሆን ደግሞ የአስፈጻሚውን ጥረት  የበለጠ ያቀልለታል፡፡

በፓርላሜንታዊ ሥርዓት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚው አካልና በተመሳሳይ ጊዜ የፓርላማ አባል ስለሚሆኑ በፓርቲም፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤትም እንዲሁም በፓርላማም ውስጥ ስለሚሳተፉ የፈለጉትን ከማስወሰን የሚያደናቅፋቸው አካል አይኖርም፡፡ ይህ ዓይነቱ የሕግ አወጪና አስፈጻሚ መቀላቀል የሕግ ተርጓሚውን ሥልጣን በቀላሉ በሕግ ለመውሰድ የቀለለ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከፍርድ ቤት እየተነጠቁ በሕግ አስፈጻሚው ሥር ለሚተዳደሩ የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች እጅግ በርካታ ጉዳዮች ተሰጥተዋል፡፡ ይህ ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶችንና በአንዳንድ ክልሎች የተቋቋሙትን ከተማ ነክ ፍርድ ቤቶችን ሳይጨምር ነው፡፡ በተጨማሪም አንዳንድ ጉዳዮችን ፍርድ ቤቶች መቅረብ የሚችሉበትን ሁኔታም የገደቡ ሕግች አሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን በመመናመን ላይ ይገኛል፡፡

ፍርድ ቤቶችም በራሳቸው ሕገ መንግሥትን እንዳይነኬ ጣኦት መውሰደቻውም ሌላው ችግር ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን የማስጠበቅ ኃላፊነት የፍርድ ቤቶችም ጭምር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ መብትን ለማስከበር የሚቀርቡ ክርክሮችን ሙሉ በሙሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን አድርጎ በመቁጠር፣ ዳኝነት ሊሰጥባቸው የሚችሉ ጉዳዮችን ፍርድ ቤቶች ወደ መተው ያዘነብላሉ፡፡ ይባስ ብሎም በሕግ ተለይቶ ለፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን እስካልተሰጠ ድረስ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ የዳኝነት ሥልጣን (Inherent Judicial Power) የላቸውም በማለትም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ወስኗል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ መነሻው ኢትዮጵያ ትከተለዋለች የሚባለው አውሮፓዊው (Continental Legal System) የሕግ ሥርዓት ነው፡፡ በመሆኑም ከሕገ መንግሥት ይልቅ ለሕግ ሥርዓት ታማኝ ለመሆን መሞከር ሌላው የዳኝነት ሥልጣንን ለመተው ማበረታቻ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡

ሌላው መነሳት ያለበት ነጥብ ደግሞ ገዥው ፓርቲ በትግል ወቅትም ሆነ ኋላ ላይ የሚከተለው ግራዘመም ርዕዮተ ዓለም በፍርድ ቤቶች ሚና ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ሊያስከትል የመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ በሶሻሊስት አገሮች አተያይ ሕግም ይሁን ፍርድ ቤቶች የቡርዣውን መደብ ለመጥቀም፣ ሠርቶ አደሩን ለመበዝበዝ የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ይህን አተያይ በመገልበጥ ለሠርቶ አደሩ እንዲጠቅሙ ማድረግ፣ ብሎም ግራዘመም ፓርቲዎች ማኅበራዊ መሠረታችን ሠርቶ አደሩ ነው ስለሚሉ የሕግና የፍርድ ቤቶች ሚና የፓርቲውን ፕሮግራም ማቀላጠፊያ ተደርገው ይታያሉ፡፡ በዚህ አተያይና አዝማሚያ ላይ ቅድሚያ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚል ልማታዊ መንግሥትነት ሲታከልበት ገዥው ፓርቲ ፍርድ ቤቶች እንዲኖራቸው የሚጠብቀው ሚና ሕገ መንግሥቱ ላይ ከተቀመጠውም ውጭ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ አገላለጽ ሕግ አስፈጻሚው አካል ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ከሰብዓዊ መብት፣ ከሕገ መንግሥታዊነት፣ ከዴሞክራሲ፣ ከፍትሕና ከሕግ የበላይነትም ቅድሚና የሚሰጠው ዕሴት ሊያደርገው ይችላል፡፡ ስለሆነም ርዕዮተ ዓለምም ሕግ ተርጓሚው ከአስፈጻሚው  ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ሊያዛበው ይችላል ማለት ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በንጉሣዊ ሥርዓት መተዳደሯም አሁንም ቢሆን ሕዝቡም ይሁን ራሱ መንግሥትም በሕግም ጉዳይ ቢሆን እንኳን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ አስፈጻሚው እንደሆነ የመቁጠር አዝማሚያ አለ፡፡ በንጉሣዊ አገዛዝ የመጨረሻ ፍርድ የሚሰጠው ንጉሠ ነገሥቱ ሲሆን፣ ይኼው ባህል ሳይለቀን በደርግ ዘመን ፕሬዚዳንቱ አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሆኑ ይቆጠራል፡፡ በንጉሣዊ ሥርዓት ይህ እንደሚሆን የሚጠበቅ ሊሆን ቢችልም፣ በዴሞክራሲያዊ አስተደዳር ግን መርሑም ሆነ የዴሞክራሲያዊነት አንዱ መለኪያው በመንግሥት አካላት መካከል የሚኖረውን የሥልጣን ክፍፍልና አንዱ ሌላውን የሚቆጣጠርበት የተመጣጠነ ሥልጣን መኖርና ይህን አሠራር አክብሮ መሥራት ነው፡፡

እንግዲህ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች የዳኝነት ነፃነቱ ላይ የራሳቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ቢኖራቸው እጅግ ተቋማዊና ሕጋዊ ሽፋን በመስጠት ሕግ ተርጓሚውን ከዓቃቤ ሕግ፣ ከፖሊስና ከማረሚያ ቤት ጋር ማቀናጀት፣ በአንድ ማዕከል ከሹመት በፊትና የሥራ ላይ ሥልጠና ለዳኞች መስጠት፣ የፍትሕ ኦዲተርን በአስፈጻሚው አካል ሥር ማድረግ፣ የተቋሙንም ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን ማድረግ  በአጭሩ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም፡፡ ዝርዝሩን ቀጥለን እንመለከታለን፡፡

የሥልጠና ነገር

ለሕግና ፍትሕ ምርምር ተቋምና የፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ማዕከል መቋቋሚያ እንደ ቅደም ተከተላቸው ደንብና አዋጅ ሲወጣ አብነት ያደረጉት የፈረንሣይን አሠራር እንደነበር የፖሊሲ ሰነዱ ይገልጻል፡፡ አብነት ሲያደርጉ ግን በትክክል አለመቅዳታቸውን ይኼው ሰነድ ይገልጻል፡፡ በተለይ የፈረንሣዩ አንድ ተቋም ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያው ግን ይህንን አለመከተሉ እንደ እንከን ተወስዷል፡፡ የፖሊሲ ሰነዱ ነጠላ የሕግ ምርምርና ሥልጠና ተቋም መኖርን በተጨማሪ አስረጅትነት ያነሳው ጃፓንና ደቡብ ኮሪያን ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ ደግሞ የአማራ፣ የትግራይ፣ የደቡብ፣ የሐረርና የኦሮሚያ ክልሎችን ነው፡፡ በእርግጥ ከእነዚህ ክልሎች በስተቀር ሌሎቹ ከላይ የተገለጹት ተቋማት የሏቸውም፡፡

ፈረንሣይ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ የሕግ ሥርዓት ይከተላሉ፡፡ በመሆኑም እንደ አርዓያ ቢወሰዱ የሚያስነቅፍ አይሆንም፡፡ የሚያስነቅፈው አሁንም ቢሆን በትክክል አርያነታቸውን አለመውሰዱ ላይ ነው፡፡ በጃፓን ማንኛውም የሕግ ምሩቅ ጠበቃ፣ ዓቃቤ ሕግ ወይም ዳኛ ለመሆን በቅድሚያ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን ፈተና ማለፍ ግድ ይላል፡፡ ቀጥሎ ያለፉት በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሥር በሚተዳደረው በሕግ ምርምርና ማሠልጠኛ ተቋማት አምስት ትምህርቶችን ይወስዳሉ፡፡ በዳኞች የሚሰጡትን የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ክርክር ሥርዓትን፣ በዓቃቤ ሕግ፤ የወንጀል ክስን አመሠራረትንና ክርክርን፣ በተግባር ያለውን የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ክርክር በጠበቆች ይሰጣል፡፡ ይህን ሲያጠናቅቁ ለዓቃቤ ሕግ ወይም ለዳኝነት ያመለክታሉ፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ በግሉ ዘርፍ ይሰማራሉ፡፡ ወይም በሌላ መሥሪያ ቤት ይቀጠራሉ፡፡ ዳኛ የሚሆኑትን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንደገና ለብቻቸው ያሠለጥናቸዋል፡፡ ይህንን ሥልጠና ሲያጠናቅቁ ነው የዳኝነት ሥራቸውን የሚጀምሩት፡፡ ዳኞች፣ በሥራ ላይ እያሉ የተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎችንም በዋናነት በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አማካይነት ሊወስዱ ይችላሉ፡፡

በደቡብ ኮሪያ ደግሞ፣ የሕግ ምሩቃኖች የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር የሚያዘጋጀውን ፈተና ካለፉ በሕግ ምርምርና ሥልጠና ተቋም የሚሰጠውን የሁለት ዓመት ሥልጠና በመውሰድ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበርን መቀላቀል ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዓቃቤ ሕግ ወይም ዳኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የተቋሙ ተጠሪነት ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነው፡፡ የፈረንሣዩም ቢሆን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነው፡፡

አገሮች ዳኞችና ዓቃቤ ሕጎች የሚያሠለጥኑ ተቋማት ከአራቱ በአንደኛው ዓይነት እንደሚያቋቁሙ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የመጀመሪያ አገር አቀፍ የማሠልጠኛ ተቋም እጅግ በተደራጀ ሁኔታ በማቋቋም ተጠሪነቱንም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚደርጉት ናቸው፡፡ ምልመላውንም ሆነ ሥልጠናውን የመምራትና የማስተዳደር ኃላፊነቱም የፍርድ ቤቱ ነው፡፡ በምሳሌነት ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ስፔን፣ ፖርቱጋል፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ይህንን ሥራ የሚመራውና የሚያስተዳድረው በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምትክ የፍትሕ ሚኒስቴር የሆነበት ነው፡፡ ተግባሩ እንደመጀመሪያው ሲሆን ይህንን አካሄድ ለሚከተሉት ደግሞ ኦስትሪያ፣ ኔዘርላንድና ፊላንድን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሌላው ዓይነት የሥልጠና ሰጭ ተቋም አወቃቀር ደግሞ ራሳቸውን በራሳቸው በገለልተኝነት በሚያስተዳድሩ ተቋማት የሚሰጡት ናቸው፡፡ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበራት ወይም ሌሎች ተቋማት ሥልጠናውን ሊሰጡ ይችላል፡፡ የተደራጀ ተቋም የለውም፡፡ ዴንማርክና ጣሊያን በዚሁ መልኩ ነው የሚያሠለጥኑት፡፡

አራተኛው ደግሞ ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር ወይም በቅንጅት ሥልጠና የሚሰጥበት አኳኋን ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጋር የተቀራረበ ቢሆንም ራሱን የቻለ ማሠልጠኛ ተቋም ከማቋቋም ይልቅ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመስማማት ይህን ኃላፊነት ለዩኒቨርሲቲዎች ሰጥተዋል፡፡ አስተባባሪዎቹ ግን ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡ የካናዳ፣ የአሜሪካና የአውስትራሊያ ፌደራል ፍርድ ቤቶች አካሄድ ለዚህ ዋቢ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያው ግን እስካሁን ድረስ የሕግና ፍትሕ ምርምር ተቋሙ ቀድሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቀጥሎ በአቅም ግንባታ፣ ከዚያ ደግሞ ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር ተዛውሯል፡፡ የፍትሕ አካላት ማሠልጠኛው ደግሞ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሥር ነው፡፡ በአዲሱ የፖሊሲ ሰነድ ላይ እንደተገለጸው ደግሞ የሕግ ምርምር፣ ሥልጠና፣ የፍትሕ ማሻሻያ ፕሮግራም፣ የፍትሕ ኦዲት ማድረግና የሕግ ትምህርት ቤቶችን በአንድነት የሚመራው ተቋም ተጠሪነቱን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን ያትታል፡፡

ከላይ እንደተገለጸው የፖሊሲ ሰነዱ ላይ የተገለጹት ሦስት አገሮችም ይሁኑ ሌሎቹ ከላይ የተዘረዘሩት የፍትሕ አካላትን በሙሉ በአንድ ተቋም ጥላ ሥር አድርጎ ጥናትና ምርምር፣ ሥልጠናና የፍትሕ ኦዲት የሚያከናውን ተቋም የላቸውም፡፡ ይህ ዓይነቱ ጠቅላይነት ለዳኝነት ነፃነት ፍጹም ተጻሪሪ ነው፡፡ የመንግሥት የሥልጣን ክፍፍልን ከመሠረቱ ያናጋዋል፡፡

የዳኝነት ነፃነት መኖር ለነፃ ማኅበረሰብ ግንባታ፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር፣ ለዴሞክራሲያ ሥርዓትና ሕገ መንግሥታዊነትን ለማስፈን የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ ከአምባገነናዊ መንግሥታት በስተቀር የማይስማማ የለም፡፡ ብዙ ጊዜ ልዩነት የሚመጣው የነፃነቱ መጠን ላይ ነው፡፡

የዳኝነት ነፃነት ሲባል ሦስት ዘርፎችን ይይዛል፡፡ የመጀመሪያው ፍርድ ቤቶች እንደ የመንግሥት አካል ከሕግ አውጭውና አስፈጻሚ ጣልቃ ገብነትና ጫና የሚኖራቸው ነፃነት ነው፡፡ ተቋማዊ ነፃነቱን ለማስጠበቅ የሚረዱ በርካታ አሠራሮች አሉ፡፡ የፍርድ ቤትን ሥልጣን እየነጠቁ ተጠሪነታቸው ለአስፈጻሚው አካል ለሆኑ ፍርድ ቤቶች አለመስጠትና ጊዜያዊ ፍርድ ቤቶችን አለማቋቋም፣ ከውሳኔ በኋላ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ አለማድረስ፣ ዳኞችን ከመንግሥት ሠራተኞች (ከሲቪል ሰርቫንት) መለየት፣ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ለፍርድ ቤት አስተዳደር በድጋፍ ሰጭነት የሚያስፈልጉ ሠራተኞችን ራሱ ፍርድ ቤቱ እንዲያስተዳድርና እንዲያሠለጥን ማድረግ ደግሞ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ የዳኞች አስተዳዳር ጉባዔም ጥንቅርና ሥልጣንም እንዲሁ!

ሁለተኛው ዳኞች ውሳኔ በሚሰጡበት ጉዳይ ላይ ከሌሎች ባለሥልጣናትም ይሁን ሌላ አካል ነፃ ሆነው በሕግ መሠረት ብቻ መመራት ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ አንድ ዳኛ በተሾመበትና ቃለ መሃላ በፈጸመበት የዳኝነትና ከዳኝነት ጋር ለተያያዘው  ተግባሩ አለቃውም፣ ታዛዥነቱም፣ ተገዥነቱም ለሕግ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ሕጉ ከሚለው ውጭ የሚያደናቅፍ ወይም ሚዛኑን የሚያስት ነገር ሲከሰት ለሕጉ ብቻ መገዛት ይቀርና ሌሎች ጉዳዮችም አብረው ይመዘናሉ፡፡ ፍርድንም ያዛባሉ፡፡ ገለልተኛ አለመሆንም ይመጣል፡፡ ፖለቲካዊ ወገንተኛነት ወይም ቢያንስ መንግሥታዊ ወገንተኛነት ይመጣል፡፡ ኢኮኖሚውን ለማገዝ የሚል አስፈጻሚውን ግብ በመያዝ፣ ፖለቲካዊ አመራር በመስጠት፣ ኦዲት አድራጊውን በመምራት፣ ለዳኞችም ሥልጠና በመስጠት፣ ለዚያውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራ ተቋም ፍርሃትን ማንገሡ አይቀሬ ነው፡፡ መፍራት ቢቀር እንኳን መንግሥትን መወገን ይከተላል፡፡ መወገን ደግሞ ነፃነትን ያሳጣል፡፡ የነፃነት አለመኖር በበኩሉ ውሳኔን ያዛባል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከአስፈጻሚው አካልም ይሁን ከሌላ የሚመጣን ፖለቲካዊ ጫና በመፍራት የሥራ ዋስትና ማጣት የሚመጣ ከሆነ፣ ግምገማ ፖለቲካን ታሳቢ ካደረገ ወዘተ ነፃነት ዋጋ ስለምታስከፍል ሥራን ላለማጣት፣ መንግሥትን ማስደሰት ብቻ የየዕለት ተግባር ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱ ነፃነት ችግር ላይ ከወደቀባቸው አሠራሮች አንዱ አጠቃላይ የዳኞች የግምገማ ሁኔታና በፍትሕ አካላት የጋራ መድረክ የሚከናወነው ግምገማና በፖለቲካ ሹመኞች የሚሰጠው ሥልጠናን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የአስፈጻሚው ፖለቲካዊው ተፅዕኖ ለዳኝነት ወይም በዓቃቤ ሕግነት ሙያ ለመሰማራት የሚፈለግ ሰው ከሚመለመልበት ጊዜ ይጀምራል፡፡ ለመመልመል ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ስለመሆኑ ከቀበሌ ማለትም ከአስፈጻሚው ከራሱ ማረጋገጫ ማስመጣት፣ በሥልጠና ወቅት የሚኖሩትን ባሕርያትና፣ ሹመት፣ ከሹመት ማንሳት ወዘተ በፖለቲካዊ ዓይን መመልከትና መለካት ይመጣል፡፡ ገለልተኛነት ሳይሆን ፖለቲካዊ ወገንንተኛነት ተፈላጊ ይሆናል፡፡ ሰነዱም ቢሆን ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን የሚያግዝና የሚያፋጥን ሥልጠናና ትምህርት መኖር እንዳለበት ይገልጻል፡፡ የዳኝነት ተቋሙ ተልዕኮ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን መደገፍ ወይም ማደናቀፍ አይደለም፡፡ ፍትሕ መስጠት ነው፡፡ ፍትሕና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚዛን ላይ ቢቀመጡ ዳኛው መምረጥ ያለበት ፍትሕን ነው፡፡

የፖሊሲ ሰነዱ ላይ በተገለጸው መሠረት ሕግ ከወጣ እነዚህን በተግባር ሲከናወኑ የነበሩትን ሙሉ በሙሉ የሕግ ማዕቀፍ በመስጠት ከተቋማዊው የዳኝነት ነፃነት በተጨማሪ ግላዊው የዳኞች ነፃነትን ብቻ ሳይሆን ፍትሕንም ጭምር የሚያናጋ ነው፡፡

የሚሰጠውንም ሥልጠና አስፈጻሚው አካል በጭራሽ ጣልቃ መግባት የለበትም፡፡ እርግጥ ነው ሥልጠና ማለት በራሱ አሻሚ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በሌሎች አገሮች የፍትሕ ምርምርና ሥልጠና ተቋማት የሚሰጧቸው ሥልጠናዎች ቀድመው የሚታወቁ፣ ወይም እንደ ነገሩ ሁኔታ የሥልጠና ዘርፎቹን በሚለይ ኮሚቴ የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ አሠልጣኞቹም፣ በአንዳንድ የተለየ ሙያዊ ዕውቀት ከሚፈልጉና ለሕግ ሥልጠናው አስፈላጊ ከሆኑ በስተቀር፣ የሕግ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ የሥልጠናው ይዘት ሕግና አንዳንዴ ትኩረት የሚሹ ማኅበራዊ ዐውዶች (የጾታ፣ የዘር፣ የአካል ጉዳት ወዘተ ጉዳዮች) ሊጨመሩ ከመቻላቸው በስተቀር ፖለቲካዊ ጉዳይ ወይም አስፈጻሚው የሚያወጣው ፖሊሲ የሥልጠና አካል ሊሆን አይችልም፡፡ ሥልጠና የሚሰጥባቸው ቦታዎችም ከሕግ አውጭውና አስፈጻሚው ሕንፃዎች ቢሮዎች ወይም አዳራሾች ውጭ መሆን አለበት፡፡ የፓርላማ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ወይም የፓርቲ አዳራሽ ውስጥ መሆን የለበትም፡፡ ሌላው ይቅርና ዓቃቤ ሕግና ፍርድ ቤት አንድ ሕንፃ ተጋርተው መሥሪያ ቤት ማድረግ አይገባቸውም፡፡ የዚህም ምክንያት የገለልተኝነት ጉዳይ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ የመንግሥትን፣ ጠበቆች ደግሞ ዜጎችን ሲወክሉ ፍርድ ቤቱ ደግሞ ዜጎችንና መንግሥትን በገለልተኝነት የሚዳኝ በመሆኑ ለገለልተኝነታቸው የሚመጥን ግንኙነትና ቀረቤታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

የዳኝነት ነፃነትን ይበልጥ ድራሹን የሚያጠፋው ደግሞ ዳኞችን ከዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስና የማረሚያ ቤት አስተዳደሮች ጋር መገምገምና የሥራ ላይ ሥልጠና መስጠት ነው፡፡ ፍትሕ የሚስጥ መምሰል አለበት፡፡ ትዕምርታዊ (Symbolic) ባሕርይ አለው፡፡ በመሆኑም ጭራሹኑ በሕግ በማስደገፍ የባሰ ማጥፋት ሕገ መንግሥታዊ አይደለም፡፡

ሦስተኛው ደግሞ ዳኛው በፍርድ ቤት ውስጥ የሚኖረው ነፃነት ነው፡፡ ተቋማዊ የውስጥ ነፃነት እንደማለት ነው፡፡ ዳኛው ከአለቃው ወይም ከሥራ ባልደረባው ወይም ከሌሎች ከፍ ካለ ዕርከን ላይ ከሚገኙ ዳኞች ከሚመነጭ ተፅዕኖ ነፃ መሆንን ይመለከታል፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የፖሊሲው ዓላማ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ተቋም ለውጤታማነቱና ለነፃነቱ ሲባል ማቋቋም ነው፡፡ ተቋሙ፣ ዳኞችንም ጭምር ያሠለጥናል፡፡ በፍርድ ቤት የተያዙ ጉዳዮችንም ኦዲት ያደርጋል፡፡ መረጃ ይይዛል፡፡ ጥናትና ምርምር ያደርጋል፡፡ ውጤቱ ለውሳኔ መሠረት ይሆናል፡፡ የሕግ ትምህርት ቤቶችም በዚሁ ተቋም ሥር ይሆናሉ፡፡ ዳኞች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር እንዲሠለጥኑ ማድረግ፣ ከሌሎች የሕግ አስፈጻሚ አካላት ጋር በተለይ ከሹመት በኋላ አብሮ ማሠልጠንና ማቀናጀት እንደምን አድርጎ ነፃነት እንደሚያመጣ ግልጽ አይደለም፡፡ ወይም ኦርዌላዊ ነው፡፡ የፍርድ ቤትን ተግባር ለአስፈጻሚው እየሰጡ ዓላማው የተቋሙን ነፃነት ለማረጋገጥ ነው ማለት ጆርጅ ኦርዌል ተግባሩ ጦርነት ማወጅ የሆነውን ሚኒስቴር የሰላም ሚኒስቴር ብሎ እንደመጥራት ነው፡፡

 

በተለይ በተለይ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 79 ከንዑስ ቁጥር አንድ እስከ ሦስት የተዘረዘሩትን ድንጋጌዎች የሚንድ ሐሳብ ነው በፖሊሲው ውስጥ የተካተተው፡፡ በየትኛውም እርከን ላይ የሚገኝ የዳኝነት አካል (እንደተቋም) ከማንኛውም ባለሥልጣን ተፅዕኖ ነፃ መሆን እንዳለበት እንዲሁም ዳኞች ከሕግ በስተቀር በሌላ ነገር አለመመራትና በነፃነት ማከናወን እንዳይችሉ እንቅፋት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍርድ ቤቶችን ነፃነትን በመቃረን ሁኔታ የመጠቅለል ተግባር ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ ጥናት ማቅረብ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ተክሌን ስለጎጃም የጻፈው ላይ እንደተቹት ‹‹ወይ ካለማወቅ ወይም ለጊዜው ነገር ለመሥራት ነው፡፡››

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...