Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርኢፍዴኃግ በ11 ተደራዳሪ ፓርቲዎች ቡድን ውስጥ የለበትም

ኢፍዴኃግ በ11 ተደራዳሪ ፓርቲዎች ቡድን ውስጥ የለበትም

ቀን:

ሪፖርተር ጋዜጣ በቅጽ 22 በቁጥር 1752 የካቲት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ዕትሙ ገጽ 5 እና 6 ላይ ‹‹ከኢሕአዴግ ጋር ለሚደረገው ድርድር በሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲሆን 11 ፓርቲዎች ጠየቁ፤›› በሚል ርዕስ መግለጫ የሰጠ ቡድን መሰብሰቡን ዘግቧል፡፡

በዚህ ቡድን ውስጥ ‹‹የኢትዮጵያ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር/ኢፍዴኃግ›› ተሳታፊና አባል እንደሆነ ጋዜጣው ገልጿል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴኃግ) ስለተሰጠው መግለጫም ሆነ  ግንባር ስለተባለው ቡድንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ከዚህ ቡድን ጋር ተሳትፎም አላደረገም፡፡ ይህ ቡድን ኢፍዴኃግ በሌለበት የራሱን ደካማ ጐን ለመሸፈን ወይም ፍላጐት ለማሟላት ሲል ኢፍዴኃግ የቡድኑ አባል እንደሆነ አድርጎ ማቅረቡና ስሙን መጠቀሙ ሕገወጥ ተግባር ነው፡፡

የጋዜጣው ዝግጅት ክፍልም ኢፍዴኃግ የዚህ ቡድን አባል ለመሆኑ ወይም በተሰጠው መግለጫ ላይ ተሳትፎ ስለመኖሩ የሚገልጽ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ሳይኖረው፣ በኢፍዴኃግ ማህተም ወይም በኢፍዴኃግ አመራሮች ፊርማ የተደገፈ ሰነድም ሳይኖር የግንባሩን ስም ጠቅሶ ዜና ማሰራጨቱ ተገቢ አይደለም፡፡

ኢፍዴኃግ ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚደራደርበትና የሚከራከርበት አገራዊና ሕዝባዊ አጀንዳ ያለው፣ አጀንዳዎችን በራሱ መንገድና አቋም ማቅረብ የሚችል፣ የራሱን የድርድርና የክርክር አቋምና ዓላማ ቀርጾ የሚንቀሳቀስ ግንባር እንጂ ድንገት ተነስቶ የእገሌ ቡድን በሚል ስያሜ ከዚያም፣ ከዚህም አጀንዳ ለመዋዋስ የሚሯሯጥ ድርጅት አይደለም፡፡

ስለዚህ በሪፖርተር ጋዜጣ የኢፍዴኃግ ስም ተጠቅሶ የተሰራጨው ዜና በዚህ መልኩ እንዲታረም፣ የዚህ ዓይነት ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ክፍሎችም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እንጠይቃለን፡፡

(የኢትዮጵያ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር)

* * * * * * *

ተፈጥሯዊ ራስ ወዳድነትን በምክር ማስወገድ አይቻልም

እሁድ ጥር 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ታዋቂው የኢኮኖሚክስ አምደኛ ጌታቸው አስፋው፣ ‹‹መሥራትና ማትረፍ በሥነ ምግባር ካልተደገፈ ለአገር ጠንቅ ነው፤›› በሚል ርዕስ የኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብን ታሪካዊ ዕድገት ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ተነስቶ፣ በፊዚዎክራቶችና መርካንቲሊስቶች አስተሳሰብ በኩል አቆራርጦ፣ ወደ ካርል ማርክስና አዳም ስሚዝ ከወሰደን በኋላ፣ ኬንዝን ጠቀስ አድርጎ፣ ወደ ዘመን አመጣሹ ‹‹ከራስ በላይ ንፋስ ጥሎ የማለፍንና የሞት ሽረትን ኢኮኖሚያዊ የግብግብ ሥርዓት›› አድርሶን፣ ከዚያም ወደ አገራችን ሁኔታ በመመለስ የጄነራል ጃጋማ  ኬሎን የ1,300 ብር የጡረታ አበል ሲያነሳ፣ እኔም ይህቺን አጭር አስተያየት ለመክተብ ብዕሬን አነሳሁ፡፡

ጌታቸው በስተርጅና ዘመናቸው ለሁሉም ዜጐች በተለይም የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ለከፈሉ ለእነ ጄነራል ጃጋማ ኬሎ ዓይነቶቹ ስመ ጥር ባለታሪክ አረጋውያን ተገቢው ክብካቤና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ብሎናል፡፡ በዚህ የተቀደሰ ሐሳቡ እኔም ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡፡ የጀግናው ጄነራል ጃጋማ ኬሎ የ1,300 ብር የጡረታ አበል በጊዜው ዋጋ የመግዛት ኃይሏ 43 ብር ገደማ ብቻ ሆኗል፡፡ ድሮ (በደርግ ዘመን ጭምር) ሃያ ሁለት ኩንታል ጤፍ ይገዛ የነበረው 1,300 ብር፣ ዛሬ አንድ ኩንታል አይገዛም፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በተለይ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ በታየው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ምክንያት ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ሰማንያ በመቶ የመንግሥት የተሳሳተ የገንዘብ ፖሊሲ (ሞኒተሪ ፖሊሲ) ነው፡፡ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር በአጠቃላይ የመንግሥት በተለይ ደግሞ የብሔራዊ ባንክ (ማዕከላዊ ባንክ) ኃላፊነት ነው፡፡

ለዋጋ ንረቱ ዋናዎቹ ተጠያቂዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የመንግሥት የልማት ባንክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዱሮ በአዋጅ  የተቀመጡትን የመንግሥት ብድር ገደቦች አንስቶ፣ ዛሬም በዳይሬክት አድቫንስ፣ በትሬዠሪ ቢልና በቦንድ ሰነዶች ለመንግሥት እንደሚያበድር ይታወቃል፡፡ ንግድ ባንክ ከመደበኛ የንግድ አሠራር ውጪ በመንግሥት ትዕዛዝ ከፍተኛ ብድር ያቀርባል፡፡ በትዕዛዝ ብድር ይሰርዛል፡፡ ከመንግሥት የ25.6 ቢሊዮን ብር የዕዳ ሰነድ ገዝቶ ካፒታሉን ወደ 40 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የፈለገውም ለዚህ ይሆናል፡፡ ይህ እንግዲህ ነገ የምንደርስበት ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡  

የተሰጠ ብድር ምርት ወይም አገልግሎት አስመርቶ፣ ለአበዳሪው በጊዜው ከተመለሰ ችግር አይኖርም፡፡ በሪፖርተር ጋዜጣ ተደጋግሞ እንደተዘገበው፣ ብዙዎቹ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች በቅደም ተከተል፣ የጥቅምና ጉዳት፣ በአጠቃላይም የአዋጭነትና የአትራፊነት ጥልቅ ጥናት ሳይደረግባቸው ወደ ትግበራ ስለሚገቡ፣ ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው ይገኛሉ፡፡ ለዚህም የስኳር፣ የባቡር፣ የነፋስ ኃይል ማመንጫ፣ የአንዳንድ የሃይድሮ ኃይል ማመንጫዎች፣ የሕንፃ ግንባታ ሌሎች ፕሮጀክቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የስኳር ፕሮጀክቶቹ ሳይጀመሩ ወደ 77 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንዳስከተሉ የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ይህ የሚያሳያው የኢሕአዴግ መንግሥት የረባ የፕሮጀክት ጥናት ድርጅት እንደሌለው ነው፡፡

የዱሮውን ለምናስታውስ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ታዋቂዎቹ ቴክኖክራቶች እነተስፋዬ ዲንቃና ኃይሉ ይመኑ የሠሩበት ቴክኒካል ኤጀንሲ የሚባል የፕሮጀክት ጥናት ተቋም ነበር፡፡ በደርግ ዘመንም እነጌታቸው ማመጫ ይሠሩበት የነበረው፣ በእንግሊዝኛ ምህጻረ ቃሉ ዴፕሳ ተብሎ የሚታወቀው ተቋም ነበር፡፡ ለመሆኑ ለዚህ መንግሥት ፕሮጀክት የሚያጠናለት ማነው? የቻይና መንግሥት ኩባንያዎች ይሆኑ?

ይህን ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡ በጥልቀት ላልተጠኑ የልማት ፕሮጀክቶች የሚሰጠው ብድር፣ ምርት ወይም አገልግሎት አስመርቶ ስለማይመልስ፣ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ውጤት የዋጋ ንረት ማስከተል ይሆናል፡፡ ይህ የዋጋ ንረት ግን የጀግናውን የጄነራል ጋጃማ ኬሎን 1,300 ብር የጡረታ አበል ሸርሽሮ የመግዛት ኃይሉን ወደ 43 ብር እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል፡፡ እዚህ ላይ የመቶና የሁለት መቶ ብር የደመወዝና የጡረታ አበል ጭማሪ ብዙም የሚፈይደው ነገር እንደሌለ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም የጄነራሉ የጡረታ አበል ሰላሳ እጥፍ ካልጨመረ በቀር ወደ ቀድሞው የመግዛት ኃይሉ ሊመለስ አይችልም፡፡  

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ከፍተኛ በሚባል መጠን ስለጨመረ፣ ጡረታ ሲወጡ የሚያገኙት አበል ከጄነራሉ ጡረታ ጋር ሲነጻጸር፣ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ ለምሳሌ ዕውቁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካፒቴን ዓለማየሁ የጡረታ አበል 1,800 ብር እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ በቅርብ ጊዜ ጡረታ የወጡ አብራሪዎች ግን ከ50,000 ብር በላይ እንደሚያገኙ ተነግሮኛል፡፡ 50,000 ብር ማግኘታቸው እሰየው ነው፡፡ ነገር ግን ካፒቴን ዓለማየሁ በ1,800 ብር መወሰናቸው በየትኛው አመክንዮ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ካፒቴን ዓለማየሁ በሚያበሩት አውሮፕላን ለመጓዝ ዕድል አግኝቼ፤ ለንደን ላይ ሲያርፉ ኮሽታ እንኳ ባለማሰማቱ በቅድሚያ አድናቆታቸውን ለመግለጽ ያጨበጨቡት ፈረንጆቹ መንገደኞች ነበሩ፡፡ ታዲያ፣ ጄነራል ጃጋማ ኬሎና ካፒቴን ዓለማየሁ እንዲራቡ የተፈረደባቸው ለምንድን ነው? ለመሆኑ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ብሔራዊ ባንክ ምን ይላል? ዜጐችን በማስራብ የኢኮኖሚ ወንጀል ሊከሰስ አይገባውምን?

ሙሰኞችም ለዋጋ ንረቱ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ባንኮች ምንም እሴት ላልፈጠሩና ለመፍጠርም ችሎታውና ክህሎቱ ለሌላቸው ግለሰቦች ትላልቅ ፎቆች መሥሪያ የሚሆን ብድር በትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ እዚህ ላይ ትዕዛዝ ሰጪው፣ የባንክ ባለሥልጣኖችና ብድሩን የሚወስዱት ሦስቱም ወገኖች በሙሰኛነት ይፈረጃሉ፡፡ ፎቅ ሠሪዎቹ ድሆችን ከቀያቸው አፈናቅለው (በልማት ስም)፣ ከመንግሥቱ መሬቱን በከፍተኛ ዋጋ በሊዝ ገዝተው፣ ፎቆቹን ይሠራሉ፡፡ ለምሳሌ አንዱ ትልቅ ፎቅ መቶ ሚሊዮን ብር ፈጅቶ ከሆነ፣ ፎቅ ሠሪው ተመጣጣኝ እሴት ሳይፈጥርና በምርት ወይም በአገልግሎት መልክ ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አስተዋጽኦ ሳያደርግ፣ መቶ ሚሊዮን ብር ኢኮኖሚው ውስጥ ስላስገባ፣ የዚህ ውጤት የዋጋ ንረት ነው የሚሆነው፡፡ ይህ የዋጋ ንረት ነው የጀነራል ጃጋማ ኬሎንና የካፒቴን ዓለማየሁን የጡረታ አበል የመግዛት ኃይል ሸርሽሮ፣ እነሱንም ለረሃብ የዳረገው! ታዲያ፣ ሙሰኞች የኢኮኖሚ ወንጀለኞች ናቸው ማለት አንችልምን? በዚህ መንገድ፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለረሃብና ለእርዛት ተጋልጠዋል ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም፡፡

ጌታቸው አስፋው ለችግሩ የሚሰጠው የመፍትሔ ሐሳብ ግብረገባዊ ምክር ይመስላል፡፡ ‹‹መሥራትና ማትረፍ በሥነ ምግባር የተደገፈ ይሁን›› ይለናል፡፡ በዚህ መንገድ ችግሩን መፍታት ቢቻል ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ግን አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖታዊ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ በዓለማዊ ግለሰባዊ ራስ ወዳድነት ከተተካ በኋላ፣ ችግሩ በሞራላዊ ስብከት የሚፈታ አልሆነም፡፡ የሰው ልጅ ሳይንሳዊ ዕውቀት እየጨመረ  በመሆኑ፣ ግለሰባዊ ራስ ወዳድነት ተፈጥሯዊ መንስዔ እንዳለው በርካታ ማረጋገጫዎች እየተገኙ ነው፡፡ በኢኮኖሚክስም አንድ ሰው በራሱ ጥረት የፈጠረውን እሴት (በምርት ወይም በአገልግሎት መልክ) ለራሱ ብቻ የማድረግ ተፈጥሯዊ ዝንባሌ እንዳለው ተደርሶበታል፡፡ አንድ ግለሰብ በራሱ ጥረት የሠራው ጠረጴዛ በነፃ ገበያው ላይ መቶ ብር ካወጣ፣ መቶ ብሩ ሙሉ በሙሉ ጠረጴዛውን ለሠራው ሰው መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ ያለፈቃዱም ከዚህ ገንዘብ ላይ ማንም ሰው ቀንሶ ሊወስድበት አይችልም፡፡ ይህ የተፈጥሯዊ የራስ ወዳድነት መግለጫ ስለሆነ ትክክል ነው፡፡ ይኼው ሰው ያመረታቸውን ጠረጴዛዎች በከፊል ደብቆ፣ በሚፈጠረው እጥረት ምክንያት የጠረጴዛው ዋጋ ሁለት መቶ ብር ቢገባ ግን፣ የመቶ ብር ዋጋ ጭማሪው ኢተፈጥሯዊ ግለሰባዊ ስግብግብነትን ስለሚያሳይ፣ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ መወገዝ ብቻም አይደለም፡፡ በሕግ መቀጣትም አለበት፡፡

በመሆኑም፣ ትክክለኛ ኢኮኖሚያዊ ሥነ ምግባር ሊከበር የሚችለው በሞራላዊ ምክር ሳይሆን፣ በሕግ ነው፡፡ በመጀመሪያ፣ ሕጐች በሳይንሳዊና ትክክለኛ መርሆዎች ላይ ተመሥርተው ይወጣሉ፤ ከዚያም ሕጐቹን የጣሱ ዜጐች ነፃ በሆነ የዳኝነት ሥርዓት ተፈርዶባቸው ይቀጣሉ፡፡ አለበለዚያ፣ ተፈጥሮአዊ ራስወዳድነት ወደ ኢተፈጥሮአዊ ስግብግብነት፣ ይህም ወደሚያስከትላቸው ሌብነት፣ ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ወዘተ እንደሚለወጥ በየቀኑ የምናየው እውነታ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የሚከተሉት መሠረታዊ ሕጐች ሊወጡ ይችላሉ፤

 1. የፖለቲካ ሥልጣን የሀብት ማግኛ መሣሪያ ሊሆን አይችልም፤
 2. የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ የሚቻለው በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ ብቻ ነው፤
 3. ማንም ሰው በምርት ወይም በአገልግሎት መልክ ተመጣጣኝ እሴት ሳይፈጥር ገንዘብ ማግኘት አይችልም፤
 4. በነፃ ውድድርና በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ ዋጋ በፍላጎትና በአቅርቦት መስተጋብር መሠረት ይወሰናል፤
 5. ከሕጋዊ ሥልጣን ውጪ፣ በነፃ ውድድርና ነፃ ገበያ ውስጥ ያለአግባብ ጣልቃ በመግባት ዋጋ ያዛባ ሰው ወይም ድርጅት ወይም ማኅበር በሕግ ይቀጣል፡፡

ለምሳሌ፣ እነዚህን ሕጐች ተግባራዊ በማድረግ ብቻ በኢትዮጵያ አያሌ ዜጎችና ድርጅቶች በሕግ ፊት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ እንደሚታወቀው፣ ብዙ ባለሥልጣኖች የፖለቲካ ሥልጣንን የሀብት ማግኛ መሣሪያ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው፡፡ በበኩሌ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን የያዘው በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አይደለም፤ አለበለዚያ መላው የአማራና የኦሮሚያ ክልል ‹‹ሕዝቦች›› አይነሱበትም ነበር (ሕዝቦች ያልኩት የዘመኑን ቋንቋ ለመጠቀም ብዬ እንጂ፣ ለእኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው)፡፡ እሴት ሳይፈጥሩ ገንዘብና ሀብት ማካበት ደግሞ በመንግሥት ባለሥልጣኖች ብቻ የተገደበ ድርጊት አይደለም፤ ብዙ ነጋዴዎች ሥራዬ ብለው የተሰማሩበት ምዝበራ ነው፡፡ እንዲያውም፣ ሙስና ተቋማዊ ገጽታ ከያዘ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

እናም፣ ለጀነራል ጃጋማ ኬሎ 1,300 ብር እና ለካፒቴን ዓለማየሁ 1,800 ብር የጡረታ አበል የመግዛት ኃይል መሸርሸር ተጠያቂዎቹ እነማናቸው? ምን እነሱ ብቻ፣ የደመወዝና የጡረታ አበል የመግዛት ኃይል ክፉኛ ለተቦረቦረባቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ችግርና ስቃይ በተጠያቂነት ሊጠቆሙ የሚችሉት የትኞቹ ወገኖችና ተቋማት ናቸው? በእኔ ግምት፣ በአጠቃላይ መንግሥት ተጠያቂ ነው፤ በተለይም የሚከተሉት አካላትና ተቋማት

 • የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
 • የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር
 • የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪዎች
 • የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት
 • የፕላን ኮሚሽን
 • የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
 • የኢትዮጵያ ልማት ባንክና

እነዚህን ሁሉ በበላይነት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይጠየቃሉ፡፡ ነገር ግን ማን ይጠይቃቸዋል? ተጠያቂነቱን እንተወውና፣ መንግሥት ራሱ የእርምት ዕርምጃዎች ይውሰድ፡፡ ለዚህ እንዲረዳው የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

 • ጠቅላላ ኢንቨስትመንት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ያለው መቶኛ ድርሻ ወደ 40 በመቶ ደርሷል ተብሏል፡፡ ሕዝብ እያስራቡ፣ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ተገቢ ስላልሆነ፣ ይህ ምጣኔ ወደ 30 በመቶ ተቀንሶ፣ ለደመወዝና ለጡረታ አበል ጭማሪው ይዋል፤
 • የደመወዝና የጡረታ አበል ጭማሪው ከፍተኛ መሆን ይገባዋል፤
 • ሙስናንና ኪራይ ሰብሳነትን ማጥፋት፤
 • አዋጭነታቸው ላልተረጋገጠ ፕሮጀክቶች የባንክ ብድር አለመስጠት፤
 • የመንግሥትን የመሬት ሽያጭ ማቆምና ፍትሐዊ የመሬት ክፍፍል ማስፈን፡፡

በመጨረሻም ጌታቸው አስፋውን ላቀረቡልን ጠቃሚ ጽሑፍ ላመሰግናቸው  እወዳለሁ፡፡ በጎ አስተሳሰባቸውንም እጋራለሁ፡፡ ነገር ግን ወደ ኢተፈጥሯዊ ስግብግብነት የተቀየረን ተፈጥሯዊ ራስ ወዳድነት በግብረገባዊ ምክር ብቻ መመለስ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ መፍትሔው በሳይንሳዊ መርሆዎችና ንድፈ ሐሳቦች ላይ የተመሠረቱ ሕጐች አውጥቶ፣ አጥፊዎችን መቅጣት ብቻ ነው፡፡

በዚህ መንገድ እስካሁን ዘመን የማይሽራት ሆና የቆየችዋን ስንኝ አብረን እንሻራት፤ ጌታቸው አስፋውም ጠቅሷታል፡፡ እኔም ልድገማትና እንሰነባበት፡፡

ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝነሽ ተላላ፣

የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!

ቸር ይግጠመን!

(ተክለብርሃን ገብረሚካኤል፣ ከአዲስ አበባ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...