Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መስተዋት እያዩ የገዛ ራስን መልክ መርሳት ምን ይሉታል?

ሰላም! ሰላም! ሁዳዴ እንደ ምንም ድሆ ገባ። እኛም ሁለት ወር ኑሮን በፈቃደኝነት  ጭር ልናደርገው ተሰናዳን። አቤት ሆድና ሰው ተባለ። ከውስጥ የሚወጣ እንጂ ወደ ውስጥ የሚገባ ሰውን አያረክሰውም እንዳላለን ቃሉ ብሎ ብሎ ትዝብትም ወደ ሆድ ገባ። ሰውና አፉ የማይገባበት የለም አትሉም። መቼስ እንደ ዘንድሮ አልተዛዘብንም። ለነገሩ ሁሌም እንደተዛዘብን ነው። ጥሎብን በየዓመቱ ትዝብታችን ከኑሮ ውድነት እኩል ሽቅብ ይጎናል እንጂ። በነገራችን ላይ ‹ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል› ሆኖ እንጂ የኑሮ ውድነት አልበረደም እሺ። ላስታውሳችሁ ብዬ እኮ ነው። አስታዋሽም የሚታወስም ጠፍቷላ። ‹‹ሆድ ሆዴን ካለ ድሮስ ማን ማንን ሊያስታውስልህ ኑሯል?›› የሚሉኝ ባሻዬ ናቸው። የሰሞኑን የሥጋ ግርግር ዓይተው። ‹‹ባሻዬ ቅበላ የዘንድሮን ካምና ምን ይለየዋል?›› ስላቸው፣ ‹‹ወይ ጉድ?›› ብለው ቱግ አሉ። ‹‹ሰው ከአምላኩ ዘንድ በሚወጣ ቃል ጭምር እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም፤›› ብለው ቃል ሲጠቅሱ፣ እኔ ደግሞ በእንጀራና በማባያው መሀል ሰፊ ልዩነት እንዳለ መተንተን ጀመርኩ።

እንዲያው ለጨዋታ እንጂ ጠበቃ መቆሜ አልነበረም። ባሻዬ ግን ገላመጡኝ። በበኩሌ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ማዕቀብ ሥጋ ላይ ለመጣል ይኼን ያህል ጭንቅ ማየቴ  ደንቆኛል። ‹ወድቄ ነበር ከእሳት ላይ፣ ሥጋ ሥጋዬን ሳይ ያሉት› መነኩሴ ወደው አይደለም ስል ነበር። ከሁሉ ከሁሉ ድንቅ ድንቅንቅ ያለኝ ይኼን ያህል ሰው የሥጋ ፍቅር ካለው ምቀኝነት፣ ትዕቢት፣ ፀብና ጥላቻ ለምን ተበራከተ? ለሚለው ጥያቄ የጥያቄና የጠያቂ ትንሽ የለውም የሚሉት ባሻዬ እንዲህ ስል ሰምተው፣ “አይ አንበርብር ሞኙ ፍቅር እኮ ከነፍስ ነው። ሥጋማ የሥጋ ነው። ዘንድሮ መንፈሱን በመንፈስ የሚመግብ ሰው አንሷል። ሥጋ ሥጋውን ሲመግብ እያየህ ከዚህ በላይ ጉድ አለመታዘብህም ፈጣሪ በዙፋኑ ላይ ቢኖር ነው፤” ብለው አበረዱኝ። ባሻዬ እኮ ነፍስ ነገር ናቸው!

ጨዋታ እንደ አጨዋወቱ አይደል? ያው አላድለን ብሎ የእኛ ቻምፒዮንስ ሊግ ወሬ ነው። ወሬም አያልቅብን እኛም አይደክመን ይኼው ይዘነዋል። እና ዛሬ የማጫውታችሁ በሆድ ዙሪያ ይሆናል። ተረቱ ‹ሆድ ካገር ይሰፋል› ይላል። ዛሬ ላይ ቆማችሁ ልትተረጉሙት ካሰባችሁ ማበዳችሁ ነው። ምክንያቱም ቻይነት፣ ታጋሽነት፣ ለመስማት መፍጠን፣ ለመናገር መዘግየት. . . ደብዛቸው ጠፍቷል። ባንመዘገብም እያንዳንዳችን የወሬ ጣቢያ አለን። የወሬ ስላችሁ ይገባችኋል ብዬ ነው። እና እኔ የተነቋቋሪውን ብዛት፣ የአጥፊቶ ጠፊውን ቁጥር ቁጭ ብዬ ሳሰላ መቼ ይሆን የሚሰለቸን ብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር ወሬ ጀምራለሁ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ለዛው ሳይሟጠጥ ይቀጥልልኛል። በመቼ ይሆን የምንጠግበው? አትልም። ‹ሆድ ካገር ይሰፋል› የሚለው ተረት እኮ ሲተረት መብልን ማዕከል አድርጎ ሳይሆን ወሬንም ነው፤›› አለኝ። ደርሶ ግራ ሲያጋባኝ ፊቴ መጠየም ጀመረ፡፡ ‹‹ምንድነው የምታወራው?›› ስለው፣ ‹‹በዚህ በኖርከው ዕድሜ ቢያንስ እንዴት ይኼ አልተገለጠልህም?›› ብሎ አሁንም ወደ እኔ አፈጠጠ።

ይኼ ሰው እንዴት ነው ነገሩ? ስላፈጠጡና ስላጉረጠረጡ ብቻ እንደመጣለን ብለው ከሚያስቡት ወገኖች ዘንድ መዋል ጀመረ እንዴ? እያልኩ፣ ‹‹በላ ግለጥልኝ!›› ስለው፣ ‹‹የዘመኑን ፈሊጥ ታውቃለህ። ዋናው ድፍረት ይሰኛል። ድፍረት ምንድነው? ስትል ድፍረት በዘመኑ መዝገበ ቃል አፈታት ማንበልብል መቻል ማለት ነው። ስለዚህ መማር ድሮ ቀረ። ዕውቀት አፈር ቃመ። ዋናው ድፍረት ነው። ድፍረት ያበላል ሲሉህ በአጭሩ ወሬ መቻል ማለት ነው። ልብ አድርግ ማንበልብልና አንደበተ ርዕቱነት የተለያዩ ናቸው። ስለዚህ ተረቱ ሲተረት ይኼን ዘመን ዓይቶ ነው በሚለው መስማማት አለብህ። በዚህ ከተስማማህ ብዙ አገር ሻጭ ብዙ ክብር ሻጭ ብዙ እምነት ሻጭ ስታይ የሆድ ነገር በሆድ ብቻ እንደማይፈታ ሳታልመው ሊፈታልህ ይገባል። ስለዚህ. . .›› ብሎ ምን ብሎ ቢቋጨው ጥሩ ነው? ‹‹ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም በወሬም እንጂ!›› ወይ አገርና ሆድ አያ!

እናላችሁ ሰሞኑን ሁዳዴ ኪሴን ጭር ሲያደርግብኝ እቅበጠበጥ ጀመር። ዝም ብዬ የናቅኳቸውን ደንበኞቼ (ቻፓ የላቸውም ብዬ ማለቴ ነው) ዘንድ እየደዋወልኩ ሁሉ አለኝ እላለሁ። አንዱ መልሶ ደውሎ፣ ‹‹ያ ባለፈው የነገርከኝ ካሪና ተሸጠ?›› አለኝ። ዕፎይ አልኩ። ሻጭና ገዥ እኮ ዘንድሮ መልክ እየሠሩብን ከምንጠቀም የምጎዳው ብሷል። እውነቴን ነው። ታዲያ እኔ ቀልጣፋው ያቺን ካሪና ላሻሽጥ ጥድፍ ጥድፍ ስል መቼ ዕለት ባሻዬ ያጫወቱኝ ተረት ትዝ ብሎ መሀል መንገድ ተገትሬ ከራሴ ጋር ማውራት ጀመርኩ። ሰውዬው አህያውን ሊሸጥ ገበያ ይዞ ይወጣላችኋል። ገበያተኛው ሌላ ሌላ ነገር ሲያይ ቆይቶ ይመጣና ባለአህያው ጋ ሲደርስ እንዳላየ ያልፈዋል። ግራ ገባው። ‹‹ምንድነው ዛሬ ሰው ወደ እኔ የማይመጣው?›› ብሎ ፈጣሪን ማማመር ይጀምራል። ቆያይቶ፣ ‹‹ዛሬማ ይህን አህያ ሳልሸጥ ቤቴ አልገባም፤›› ብሎ ዘዴ ይዘይዳል። ዘዴው ሰውዬው አንጎንብሶ እንደ አህያ ማናፋት መሆኑ ነው።

ወዲያው የገበያተኛው ቀልብ ወደ እሱ ዞረ። ገበያተኛው ተሰብስቦ እንደ ትንግርት ያየው ጀመር። ኋላ አንዱ ነገሩ ገብቶት ‹‹ለመሆኑ ዋጋህ ስንት ነው?›› ይለዋል። ‹‹ምኑን አውቄው ጌታዬን ጠይቁት፤›› ብሎ ይመልሳል። ‹‹ጌታህ ማን ነው?›› ሲለው፣ ‹‹ምኑን አውቄው? ጌታዬን የሚያውቀው ጌታዬ ነው፤›› ብሎ ይመልሳል። ‹‹እሺ የጌታህ ጌታ የት ነው ያለው?›› ሲለው፣ ‹‹እርስዎ ኪስ ነዋ፤›› ይላል። ሰውዬው ኪሱን ዳበስ አድርጎ ዋጋ ጠራ። ይኼን ዓይቶ ሌላውም ኪሱን እያየ ዋጋ መጥራት። አህያውን በጨረታ ያሸጠ ብቸኛ ሰው መሆኑ አይደል? ምን ልላችሁ ፈልጌ ነው? ዘንድሮ ወይ ባለ አራት እግር ወይም ባለ አራት ዓይን ካልተሆነ በቀር ሙያ፣ ችሎታና ዕውቀት ገደል ገብተው እንስሳት ጎትተው እያወጧቸው ነው ለማለት ነው። ‹ፉገራ› አይምሰላችሁ ሰው አራት እግሩን ይብላ ተብሎ ሲረገም! 

እናላችሁ ጠላልፎ ያሰረን ነገር መዓት ነው። ሰንሰለት ይሁን ገመድ እዚያው እናንተ አጣርታችሁ ድረሱበት። እኔ የማውቀው ‘ሥውር’ መሆኑን ብቻ ነው። መቼ ዕለት ከባሻዬ ልጅ ጋር ስለዚሁ ሥውር ትብታብ እስር ስናወራ (ትብታብ ማለት ምን ማለት ነው?’ እንዳትሉኝና ከደላላነት ወደ መዝገበ ቃላትነት እንዳልቀየር) ምሳሌውን ያነበበት መጽሐፍ ርዕስ ጠፋውና ለማስታወስ እየሞከረ የሚከተለውን አጫወተኝ። ኑሮ ራሱን እያስረሳው ርዕስ ጠፋህ ተብሎ መውቀስ ግፍ ነውና ተውት። እንዲያው እኮ! እና ምን አለኝ፣ “በአንድ መንደር ውስጥ በልብስ አጣቢነት የሚተዳደር ሰው ነበር። የአካባቢውን ነዋሪዎች የቆሸሸ ልብስ ይቀበልና በአህዮቹ ጭኖ ወንዝ ይወርዳል። አጥቦ አድርቆ ሲያበቃ ለየባለቤቶቹ ይመልሳል። ‘ላውንደሪ በስሎው ሞሽን’ በለው፤” ሲል ሳቅን። ቀጠለ፣ “እና አንድ ቀን ሰው ተሰባሪ ነውና በጠና ታሞ ከአልጋው መነሳት አቃተው። ልጁን ጠርቶ ‘በል ዛሬ እኔን ተክተህ ያልታጠቡ ልብሶች አሉና አህዮቹን ጭነህ ወንዝ ውረድ’ አለው። ልጁም እንደታዘዘው አህዮቹን ጭኖ ቅደሙ ሲላቸው ሊነቃነቁ ነው? እግራቸው በችንካር እንደተቸነከረ ከረገጡበት አልነቅል አሉት። ቢታገል አልሆነም። አባቱ ዘንድ ሄደና የሆነውን ሲያስረዳው ‘ውይ! እረስቼው ሳልነግርህ። እግራቸውን አስሬዋለሁ’ አለው።

‹‹ልጅዬው ግራ ተጋብቶ ‘ምንም ገመድ የሚባል አላየሁም’ ሲለው ‘ይኼውልህ ማታ ማታ ወደ ማደሪያቸው አስገብቼ እግሮቻቸውን ተራ በተራ በእጄ ዳሰስ ዳሰስ አደርገዋለሁ። እንደታሰሩ ያስባሉ። ጠዋትም እንደዚያው ሳደርግ እንደ ፈታሁዋቸው ያምናሉ። እንዲያ አሠልጥኛቸዋለሁና አሁን ሄደህ እግሮቻቸውን ስትዳስሰው እስራታቻውን እንደተፈታላቸው ያምናሉ’ አለው። ልጁም አባቱ እንዳለው አደረገና ወደ አጠባው ሄደ። በላ ይፍቱኝ በል፤” ብሎ ቀላለደ። ወዲያው ግን የመጽሐፉን አርዕስት ለማስታወስ ትግሉን ሲቀጥል ሳየው ትከሻውን ቸብ እያደረግኩ፣ “በቃ እርሳው ፈትቼሃለሁ!” ብዬ አሾፍኩበት። የምር ግን ከምሳሌው ብዙ ተማርኩ። ብዙ ነገር አያያዝኩበት። ባልተያዘና ባልተጨበጠ ነገር እውነት መስለው፣ ገሃድ መስለው የተበተቡን ገመዶችን በጣጥሼ መጣል አሰኘኝ። ግዳይ መጣል እንደለመደ ጀግና አዳኝ ሸልል ሸልል አለኝ። ምን ዋጋ አለው ገመዱ አሁንም አልታኘክ እንዳለ ነው። እስኪ ካያችሁት ጥሩኝና ተባብረን እንበጣጥሰው። እስከዛው ‘መሃረቤን ያያችሁን’፣ ‘እስራቴን ያያችሁ’ በሚለው ተክተው ልጆቻችን ሲጫወቱ እንዲያድጉ መረባረብ አለብን። እኛም መሃረብ እነሱም መሃረብ ስንፈልግ ከኖርንማ፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ መሠለፍ ብቻውን ምን ዋጋ አለው? . . .  እ?  . . . ፍታት ላይ ናችሁ መሰል ዝም አላችሁ።

በሉ እንሰነባበት። እንግዲህ ፆም አይደለም? ስቆም ስቀመጥ ስሄድ ስመለስ ከማየው ነገር ይችን ለማለት ብወድ መቼም አታሳፍሩኝም። ምን? በሉ። የታይታ ኑሮ፣ የታይታ መልክ፣ የታይታ እሴት ለቀቅ ያለ አልመሰላችሁም? ነገር ከሥሩ ውኃ ከጥሩ መባሉ ቀርቶ ‹ወደ ገደለው ግባ› የሚሏት አባባል ከመጣችሁ ወዲህ ብዙ ነገር አጓጉል ሲያዘም እያየሁ፣ በቀን በረዥሙ ከምራመደው በረዥሙ የምተነፍሰው እያደከመኝ ነው። አላንዛዛባችሁና ወደ ገደለው ስገባ፣ ትርጉሙን የሳተ አዋዋልና አኗኗር እየተላመድን ያለን ይመስለኛል። ወግና ባህል እየተፈተሸ እየተራመደ እንዲቀጥል ባናምንም አሁን ቸግሮ የማያው ነገር ጭራሹን የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን ዓይነት ሆኗል።

ፆም መያዣ ተብሎ ይሰከራል፣ ፆም መፍቻ ተብሎ ይደለቃል፣ ቅዳሜ ነው ተብሎ ይቃማል (ዕድሜ ለስፖርታዊ ክንውኖችና ፓርኮች ዕጦት መፈረሹ እንደሆነ ከሰኞ እስከ ሰኞ ሆኗል)፣ ይጠጣል፣ ይሰከራል። እንደ አቅሚቲ እንደ ኪስ ፈቃድ ይታደራል። የባሻዬ ልጅ ሁሌ እንደሚለኝ ይኼ የምላችሁ ነገር መላዋን ኢትዮጵያ ባይገልጽም፣ መዲናና መዲነኛ የተቀበለውን ሌላው መቀበሉ የሚቀር አይመስለኝም። ነፍስ አባት ሆንክብን እንዳትሉኝ ብቻ አጠር ሳደርገው የባሻዬን አባባል ለመዋስ እገደዳለሁ። ደስ የማይል ነገር  . . .  ደስ አይልም! ለምን ይሆን ይኼን ያህል ራስን መፈተሽ የከበደን ግን ጎበዝ? መስታወት እያዩ የገዛ ራስን መልክ መርሳት ምን ይባላል? መልካም የጥሞና ሳምንት! መልካም ሰንበት!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት