Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበድብርት የሚጠቁ ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ተገለጸ

በድብርት የሚጠቁ ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ተገለጸ

ቀን:

በድብርት (ድባቴ) የሚጠቁ ሰዎች እየበዙ እንደሆነ ባለሙያዎች በጥናት አመለከቱ፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ አዎንታዊ ለውጦች ቢኖሩም ማኅበረሰቡ አሁንም ስለ አዕምሮ ጤና ያለው ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የተወሰኑ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም የአዕምሮ ጤና ችግሮችን በአንድ ጠቅልሎ የመመልከትና ይህ ድብርት፣ ጭነቀት ነው? ወይስ ሌላ የአዕምሮ ችግር? ብሎ ነገሮችን ለመከታተልና ለመለየት ያለመሞከር ነገር መኖሩን ሳይኮ ቴራፒስት ናርዶስ ማሞ ይናገራሉ፡፡ በተወሰነ መልኩ ችግሩን ሲደርሱበት ወደ አዕምሮ ሕክምና ባለሙያ ከሚሄዱ የማይሄዱ እንደሚበዙም  አመልክተዋል፡፡ እሳቸው ወደ ሚያገለግሉበት ማዕከል ከሚሄዱ ድብርት (ድባቴ)፣ ጭንቀትና የሱስ ችግር ያለባቸው እንደሚበዙም ጠቁመዋል፡፡

በድባቴ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በአገራችን እየጨመረ እንደሆነ እንደሚያምኑ የሚናገሩት ወይዘሮ ናርዶስ ችግሩ በይበልጥም ወጣቶች ላይ እየታየ እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹የአኗኗር ዘዬያችን እየተቀየረ ሕይወታችን ይበልጥ ውስብስብ ሲሆን ውጥረት ይኖራል፤›› የሚሉት ባለሙያዋ ችግሩ የተማረ ያልተማረ፤ ገንዘብ ያለው ያልተሳካለት ሳይባል በሁሉም የሕይወት መስመር ላይ የሚገኙትን እያጠቃ እንዳለ ያስረዳሉ፡፡

በሕይወታቸው ይህ ቀረ በማይባል መልኩ ሁሉን ያሳኩ በድባቴ ተጠቅተው እሳቸው ዘንድ እንደሄዱም ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳ ድባቴን ሁኔታዎች ሊያባብሱ ቢችሉም በመጀመሪያ ደረጃ የሚከሰተው በአዕምሮ ውስጥ ካሉ ኬሚካሎች ጋር በተያያዘ ነውና፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በድብርት የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፣ ይህም እ.ኤ.አ. ከ2005 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ ቁጥሩ የ18 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ድብርት በብዛት የሚታይ የአዕምሮ ጤና ችግር ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ 300 ሚሊዮን ሰዎች በችግሩ ይጠቃሉ፡፡

ድብርት ከመደበኛ የስሜት መለዋወጥ እንዲሁም ለአጭር ጊዜ ከሚቆይ የስሜት ጥሩ አለመሆን ይለያል፡፡ ድብርት አነስተኛ ወይም ከባድ ሊሆን የሚችል ሲሆን፣ ከባድ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከባድ የጤና እንከን ይሆናል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደረስ ተጠቂዎች ሥራና ትምህርት ላይ ውጤታማ እንዳይሆኑ ቤተሰባዊና ማኅበራዊ መስተጋብራቸውም አስቸጋሪ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ሲከፋም ተጠቂዎች ራስን ወደ ማጥፋት እንዲያመሩ ሊያደርግ እንደሚችል ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

ድብርት በሚገባ ሊታከም የሚችልበት መንገድ ቢኖርም ችግሩ እንዳለባቸው አውቀው ሕክምና የሚያገኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተጠቂዎች ግማሽ ያህሉ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የሚቀመጡት ስለ አዕምሮ ጤና ያለ የተሳሳተ ግንዛቤ፣ ቢፈልጉ እንኳን በቀላሉ የባለሙያ እርዳታ ማግኘት አለመቻል እንዲሁም የሠለጠነ የባለሙያ አለመኖር ናቸው፡፡

ባለፈው ዓመት የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው እንደ ሌሎች ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ እንዳላቸው አገሮች ሁሉ ድብርት በኢትዮጵያም በስፋት እየተስተዋለ ያለ የአዕምሮ ጤና ችግር ነው፡፡ ያላገቡ፣ ገቢያቸው አነስተኛ የሆነ፣ የሚያጨሱ ዕድሜያቸው የገፋና ኑሯቸውን በብቸኝነት የሚመሩ ሴቶች በብዛት ለድብርት ተጋላጭ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በተመሳሳይ ካጋጠሟቸው በድባቴ የተጠቁ ሰዎች የሴቶች ቁጥር ከፍ እንደሚል ወ/ሮ ናርዶስም ጠቁመዋል፡፡

ጥናቱ ግኝቱን መሠረት በማድረግ ድብርት በኢትዮጵያ ጉልህ የኅብረተሰብ ጤና ችግር እየሆነ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚያስፈልግ ይደመድማል፡፡ እንደ ማጨስ ያሉ ሌሎች ሱሶችም ከግንዛቤ ሊገቡ እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡ እንደ ወ/ሮ ናርዶስ ያሉ ባለሙያዎች ደግሞ ድባቴ ላይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የአዕምሮ ጤና ችግር በአገሪቱ ትኩረት እንደሚሻ ይገልጻሉ፡፡

ድብርትን ጨምሮ የአዕምሮ ጤና ችግር በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሳደረ ያለው ጫና እየጨመረ በመሆኑ አገሮች የአዕምሮ ጤና ችግርን በሚመለከት የተቀናጀ ሥርዓት እንዲዘረጉ የዓለም ጤና ድርጅት ይመክራል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአዕምሮ ጤና አማካሪ ዶ/ር ተድላ ወልደ ጊዮርጊስ እንደሚሉት ከአዕምሮ ጤና አገልግሎት ጋር በተያያዘ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለውጦች መታየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ብሔራዊ የአዕምሮ ጤና ስትራቴጂ መቀረፅ (ስትራቴጂው የአምስት ዓመት የነበረ ሲሆን አሁን ጊዜውን ጨርሶ ለቀጣዩ አምስት ዓመት ሌላ እየተቀረፀ ነው)፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የአዕምሮ ጤና አገልግሎት በሆስፒታል ደረጃ ብቻም ሳይሆን በጤና ጣቢያ ደረጃ እንዲሰጥ መደረጉ፤ ለዚህም ለባለሙያዎች ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአዕምሮ ጤና ትምህርት እየተሰጠ መሆኑም ለአዕምሮ ጤና ትኩረት እየተሰጠ መሆኑን እንደሚያሳይ ይገልጻሉ ዶ/ር ተድላ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...