Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየ16ኛው ክፍለ ዘመን ማስታወሻ

የ16ኛው ክፍለ ዘመን ማስታወሻ

ቀን:

‹‹ . . . እኔ ከአንተ የምፈልገው ሕዝባችንን ሥርዓት የሚያስተምሩና በጦር መሣሪያ የሚያስታጥቁ ሰዎች ብቻ ነው እንጂ ሌላ የምፈልገው ነገር የለም፡፡ ይኼንን ያደረግህ እንደሆነ ፍጹም ወንድም ነህ፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን በነገሠ ጊዜ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ቢሆን ስንኳ ታላቅ ኃይልና ከአባቱ የበለጠ ዕውቀት ነበረው፡፡ እኔም አባቴ ናዖድ ሞቶ ዙፋኑን በወረስሁ ጊዜ ገና ሕፃን ብሆን ስንኳ እግዚአብሔር ከአባቴ የበለጠ ኃይል ሰጥቶኝ የግዛቴን ሕዝብ በሙሉ በእጄ ይዤ በፀጥታ ላይ ነኝ፡፡ ለዚህ ቸርነቱ እግዚአብሔርን አንድነት እናመስግነው፡፡››

በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ልብነ ድንግል ለፖርቱጋል ንጉሥ ዮን ዦኣም ከጻፉት ደብዳቤ የተቀነጨበ ነው፡፡ ደብዳቤውን የያዘው መጽሐፍ ‹‹አልቫሬጽ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት ከ1520-1527 ወደ ኢትዮጵያ የተላከ የፖርቱጋል መልዕክት›› ይባላል፡፡ በዘመኑ የፖርቱጋል መልዕክተኛ ሆነው የመጡት አባ ፍራንሲስ አልቫሬጽ የጻፉት ሲሆን፣ በአማርኛ ተርጉመው ያዘጋጁት አቶ ዮና ቦጋለ ናቸው፡፡

ደራሲው በኢትዮጵያ በቆዩባቸው ስድስት ዓመታት ውስጥ ከሰፊው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ግዛት፣ የተቻላቸውን ያህል ዙረው ለመጎብኘትና መሐመድ ኢብን ኢብራሂም ወረራውን ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አመራር የቤተ መንግሥቱንና የቤተ ክህነቱን ሥርዓትና አስተዳደር የሕዝቡን ልማድና ወግ እስከ ጥቃቅኑ የቤተሰብ ኑሮ አስገራሚ በሆነ አኳኋን መርምረው አቅርበውታል፡፡

ደራሲው ከ500 ዓመታት በፊት በንጉሠ ነገሥት ግዛቱ ውስጥ ስለነበረው የክርስቲያኖች ጾም የመዘገቡትም በመጽሐፉ ውስጥ ተካቷል፡፡

ከፊሉ እነሆ፡- ‹‹በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት የኩዳዴን ጾም ስድሳ ቀን ከፋሲካ በፊት በሚውለው ሰኞ ይጀመራል፡፡ ይኼውም የኛው ኩዳዴ ጾም ከመግባቱ አሥር ቀን ቀደም ብሎ ማለት ነው፡፡ ከልደተ ስምዖን ማግሥት ጀምሮ ካህናቱ፣ መነኮሳቱና ተራው ሕዝብ የሚጾሙባቸው ሦስት ከባድ የጾም ቀኖች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ቀኖች የነነዌ ጾም በሚል ስም ይጠሩዋቸዋል፡፡ በእነዚህ ቀኖች በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ይበላሉ፡፡ ይኼውም እህል ሳይሆን ሥር ብቻ የሚመገቡ ብዙ መነኮሳት መኖራቸውንና ከእመጫቶቹም አብዛኞቹ ሕፃናቱን በቀን አንድ ጊዜ ብቻ እንደሚያጠቧቸው ነገሩን፡፡

‹‹በጾሙ ወራት ዋና ምግባቸው እንጀራና ውኃ ነው፤ ዓሳ መብላት ቢፈቀድም ስንኳ አያገኙም፡፡ ባሕር ወይም ጅረት በሚገኝባቸው ሥፍራዎች ዓሳ በብዛት ቢገኝ ስንኳ የአያያዙን ጥበብ ስለማያውቁት ለታላላቆች መኳንንት በጥቂቱ ያመጡላቸዋል፡፡ በኩዳዴ ጾም ውስጥ ዋናው ምግብ እንጀራ ብቻ ነው፡፡ በጾሙ ወራት ዝናብ ባይዘንብ ስንኳ ውኃ በብዙ ስለሚገኝ ሕዝቡ ቢፈቅድ ልዩ ልዩ ዓይነት አትክልት ለመትከል ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በዝናቡ ወራት ብቻ ስለሚተከሉ በጾሙ ወራት የሚበሉት ቅጠላ ቅጠሎች አያገኙም፡፡ በብዙዎች ገዳማት መነኮሳቱ ኦርቶ (ሳማ) የምለውን የመሰለ ተክል ቅጠሉን ብቻ እየወሰዱ ከዓመት እስከ ዓመት የሚበሉት አንድ ዓይነት ጎመን አላቸው፡፡ የወይን ፍሬና ኮክ በሚገኝባቸው ወረዳዎች እነዚህ ፍሬዎች ከየካቲት (ፌብሩዋሪ) እስከ ሚያዝያ (ኤፕሪል) ባሉት ወራት ውስጥ ስለሚበስሉ እነዚህን አትክልቶች የተከሉ ሰዎች በጾሙ ወራት የሚበሉት አያጡም፡፡››

መጽሐፉ 450 ገጾች ያሉት ሲሆን ዋጋውም 120 ብር ነው፡፡

* * *

የዓድዋ ድል 121ኛ ዓመት

በኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ላይ በ1888 ዓ.ም.፣ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በዓድዋ ድል የተገኘበት 121ኛ ዓመት አስመልክቶ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየቀረቡ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ክብረ በዓሉን የሚመለከት ሙዚቃዊ ድራማ ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ አዘጋጅቷል፡፡ በሌላ በኩልም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ‹‹የዓድዋ ድል ብዝኃነትን ላከበረች ኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ የሚያስችል ህያው አብነት›› በሚል መሪ ቃል በዓሉ በዓድዋ ከተማ ከድሉ ጋር ትስስር ያላቸውን ታሪካዊ ቦታዎች በመጎብኘት እንደሚከበር አስታውቋል፡፡

* * *

የሮትራክት ክለብ 15ኛ ዓመት

ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 30 በሆኑ ወጣቶች የሚመራው መላ ሮትራክት ክለብ፣ የ15ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከየካቲት 19 እስከ 21 ድረስ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ያከብራል፡፡ ለማኅበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የገለጸው ክለቡ፣ የዓለም አቀፉ ሮታሪ ኢንተርናሽናል ቤተሰብ ነው፡፡ እንደ ክለቡ መግለጫ የፎቶ ዐውደ ርዕይና ዶክመንተሪ ምርቃን አካቶ በዓሉን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አትላስ አካባቢ በሚገኘው ሕንፃ ያከብራል፡፡

* * *

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...