Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅስድስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በ1960 ዓ.ም. ያስተናገደው ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም››

ስድስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በ1960 ዓ.ም. ያስተናገደው ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም››

ቀን:

ለደራስያን በሙሉ የምመክረው አንድ ነገር አለ፡፡ ንቃትም፣ ትጋትም ያጠጠበት ዘርፍ መስሎ የታየኝ ነገር ስላለ፡፡ ድርሰት ትልቅ ዝግጅትን ይጠይቃል፡፡ ከዝግጅቶቹ የአንዱና መሠረታዊው ዕውቀትን በመመልከት፣ ዙሪያን በመቃኘት፣ በተለይ ደግሞ በማንበብና ያነበቡትን አጣጥሞ ራስን በመመርመር አእምሮን ከልቡና ጋር ማዳበር ነው፡፡ ዝም ብለን፣ አንድ ቀን ወፈፍ ጨምደድ ያደረገን ዕለት ተነስተን እስቲ ወደ ገበያ ልውጣ እንደሚባለው፣ እስቲ ድርሰት ልጻፍ አይባልም፡፡ ድርሰት በባዶ ስለማይፈልቅ፣ ያለፉትን፣ የቀደሙትን ዘመናትና ደራስያን ድርሰቶችን ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ ሳል ይዞት ስርቆት ቂም ይዞ ጸሎት በሚለው ላይ ስንፍ ይዞ ድርሰት የለም የሚለውን እጨምራለሁ፡፡ አፈ ታሪኩን፣ ተረታ ተረቱን፣ ሚቶሎጂውን፣ ሃይማኖታዊ መጻሕፍቱን ታሪክን፣ ፍልስፍናን ማንበብ ለደራሲ የምርጫ ጥያቄ መሆን ያለበት አይመስለኝም፣ ሙያዊ ግዴታም፣ የሰብአዊነት መርህም እንጂ፡፡ ዕውቀታችን ግልብ ከሆነ፣ ድርሰታችን እንደዚያው ቀሊል ይሆናል፡፡ ስለዚህ የንባብ ዋጋ ከመድረስ ዋጋ ቢበልጥ እንጂ አያንስምና ቀደምት ድርሰቶች ዘርታችሁ ልታፈሩ ላሰባችኋቸው ድርሰቶች ግብአት ይሁኗችሁ፡፡

ማጠጥ ያየሁበት ሌላው ዘርፍ የሒስ ባህል ነው፡፡ እዚህ ላይ ልትወግሩኝም፣ ልትወቅሱኝም ትችላላችሁ፣ ቆረጥ! ሆረጥ! ያለ ቃል ነው እምናገረው፡፡ ደራስያን የሒስን ጥበብ መቅሰም አለባቸው፡፡ ብሂሉ ‹‹ሒስ የሚችል ሁሉ ወጥ ድርሰት መጻፍ ይችላል አይባልም፤ ደራሲ የሆነ ሰው ግን ራሱን በሒስ ጥበብ ማነጽ አለበት›› የሚል ነው፡፡ እንደ ብርቅ ነገር አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር በዚህ ረገድ ጥሩም ይሁን ደካማ ድርሰት ጽፎ በወግ የተዋቀረ፣ በሐሳብ የዳበረ ሒስ (ስለራሱም ሥራ ሆነ ስለሌላው) የሚጽፍ ገና አላገኘሁም፤ ራሴን ለዚያ ያበቃሁ አይደለሁም፡፡ የራስንም ሆነ የሌላውን ሥራ በሒስ መቃኘትና ማስተንተን ጥበብን መፈለግ፣ ዕውቀትን መቃኘትና መናኘት፣ ስለሆነም አእምሮን ማጎልመስ ነው፤ ‹‹ሰውነትን›› (ሰው መሆንን) ማጽደቅ ነው፡፡ የደራስያን ማኅበር ሌላው ተግባርና ኃላፊነት የሒስ ባህል በደራስያን ዘንድ በተለይ የሚዳብርበትን መንገድ ማበጀት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የነፍስ የመንፈስ ምግብ የሚሆነው አእምሮን ክፍት ማድረግ ነው፡፡ አንዱና ዋነኛውም የሚመስለኝ መንገድ ሒሳዊ ኅትመቶችን ሥራዬ ብሎ ማውጣት ነው፡፡ ዱሮ ዱሮ፣ አንዳንድ ደራስያን ሲተቹ ተሰደብኩ እንጂ ሒስ ቀረበልኝ አይሉም ነበር፡፡ ያ አሁንም አለ፡፡ ተሰደብኩ ብሎ ነገር ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ሒስ ስድብም አይደለም፤ ምሥጋናም አይደለም፡፡ ቢያኮርፉ እርሾ እንደበዛበት ቡሆ ገንፍለው ከቡሆቃው መፍሰስ እንደሁ እንጂ ቀና የሆነ ሒስ አድራጊ የሚሸበር ወይም የሚፈራ አይመስለኝም፡፡ እንጃ፣ እኔ፣ ከመሰለኝ፣ የመሰለኝን ከመናገር አልፈራምና ይህን ስላልኩ እንዳታኮርፉኝ፡፡ ሐያስያን ለደራስያን የሙያዊ ጉድፍ መንቀሻ መስታወቶች ናቸውና ማስፈራሪያ ጭራቅ ተደርገው አይታዩ፡፡

  • ዶ/ር ዮናስ አድማሱ ‹‹የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ›› (1999)

 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መንግሥት የኢዲ አሚንን ታሪክ ለቱሪስት መስህብነት ሊጠቀም ነው

የዩጋንዳ መንግሥት ጨካኝ፣ የሰው ሥጋ የሚበላ አገሪቱንም በብዙ መልኩ በማመሳቀል ስሙ የሚነሳው የኢዲአሚን ዳዳን ታሪክ ለቱሪስት መስህብነት ሊጠቀምበት እንደሆነ የአገሪቱን ቱሪዝም ቦርድ ዳይሬክተር በመጥቀስ ዘኒው ቪዥን ዘግቧል፡፡ ዳይሬክተሩ ስቴፋን አሲምዌ እንዳሉት ከኢዲ አሚን ጋር ግንኙነት ያላቸው ቦታዎች ሁሉ ተለይተው የቱሪስት መስህብ ይሆናሉ፡፡ በዚህ መሠረትም ኢዲ አሚን የተማረበት ትምህርት ቤት፣ የኖረበት አካባቢ የመሰሉ ቦታዎች ይለያሉ፡፡ ኢዲ አሚን ኡጋንዳን እ.ኤ.አ. ከ1971 እስከ 1979 አስተዳድሯል፡፡

* * * *

ትውስታን ለማሻሻል

ዕድሜ እየጨመረና እያረጁ ሲሄዱ ነገሮችን ለማስታወስ መቸገር ተፈጥሯዊ ሲሆን ይህን በቀላል የአኗኗር ዘዬ ለውጥና በአመጋገብ ማሻሻል እንደሚቻል ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ነገሮችን፣ ቀኖችን እንዲሁም የተፈጠሩ ነገሮችን በተለየ መልኩ የሚያስታውሱ አንዳንድ ሰዎች ያጋጥሙናል፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎች ስሞችን፣ አድራሻዎችንና የስልክ ቁጥሮችን በጭራሽ አይረሱም፡፡ የማስታወስ ችግር ላለባቸው ሕፃናት፣ ጐልማሶችም ይሁን አዛውንቶች ትውስታን ማሻሻል ያስችላሉ የተባሉ ነገሮች ይሰነዘራሉ፡፡ በዚህ ረገድ አፕል፣ ሙዝ፣ ባቄላ፣ ቲማቲምና ሽንኩርት ያሉን መመገብ እንደ ሻይና ቀይ ወይን ያሉን መጐንጨትም እንደ መፍትሔ ይጠቀሳል፡፡ አንዳንድ ቅጠላቅጠሎችና ቃሪያና በርበሬም እንደዚሁ፡፡ በተቃራኒው ትውስታን በተለይም የረጅም ጊዜ ትውስታን ከሚያደክሙ የአልኮል አደገኝነት ይነገራል፡፡ አልኮል አብዝቶ መጠቀም በከፍተኛ ሁኔታ ትውስታን ያዳክማል፡፡ ሥጋን ለመተካት ብዙዎች የሚመገቡት ሶያም ትውስታን ለማሻሻል ይጠቅማል፡፡ በአይረንና ፎሊክ አሲድ የበለጸጉ ምግቦችን መመገብም ተመሳሳይ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ጥሩ ማኅበራዊ ትስስርና መስተጋብር ያለው ሕይወት መምራትም ለትውስታ ጠቃሚ ነው፡፡ አካላዊ እንቅስቃሴም ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ 

* * *

ራሴን አጥቼ

ራሴን አጥቼ

ፍለጋ ወጥቼ

ሰው መሀል ገብቼ፣…

የሰው ጫካ ውጦኝ

የሰው አረግ ጠልፎኝ

የሰው ዳገት ዳግቶኝ

የሰው ድጥ አድጦኝ

ራሴን አዙሮ፡-

ከሰው ጉድባ ጣለኝ፡፡

ከዚያ የሰው ጉድባ

ድሄ ተነስቼ

ዳገቱን ቧጥጬ

አፋፉን ወጥቼ

በሰው ሽምጥ አጥር

በቀጋው ደማቼ

በሰው በተቦካ

የሰው ማጥ ጨቅይቼ

ተመልሼ ገባሁ፡-

ፍለጋ የወጣ ራሴን አጥቼ፡፡

  • ጌትነት እንየው ‹‹እውቀትን ፍለጋ›› (2004)

* * *

አስገራሚ የእንስሳት ባህሪያት

  • አፍሪካን ሲቬት – ይህ እንስሳ ጭራው አካባቢ በሚገኙ ሁለት እጢዎች ዘይት የመሰለ ፈሳሽ ያመነጫል፡፡ ይህ ፈሳሽ ለሽቶ ኢንዱስትሪው ዓይነተኛ ግብአት ይሆናል፡፡
  • የመሬት ትል – ይህ ደቃቃ የመሰለ ፍጥረት አምስት ጥንድ ልቦች አሉት ቢባል የሚታመን አይመስልም፡፡ ልቦቹም ከላይኛውና ከታችኛው የደም ቬስል ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ የመሬት ትል የወንድና የሴትም ፆታን የያዘ ነው፡፡
  • ሎብስተር – ሎብስተር ጥፍሩን ወይም እግሩን በተለያዩ ምክንያቶች ቢያጣ አዲስ ሊበቅልለት ይችላል፡፡ ምግቡን የሚፈጨው በስድስት ጥንድ መንጋጋ መሳይ ነገር ሲሆን እስከ 100 ዓመት መኖርም ይችላል፡፡
  • አልቅት – ይህ ትንሽ ፍጥረት ከክብደቱ አምስት ጊዜ የሚበልጥ ደም መምጠጥ የሚችል ሲሆን ያለ ምግብም ለ18 ወራት መቆየት ይችላል፡፡ አንድ የጎለመሰ አልቅት የወንድና ሴት ፆታን ስለሚይዝ ራስ በራሱ መራባት ይችላል፡፡
  • የአውሮፓውያን ካት ፊሽ – ይህ ዓሳ አንዳንዴ ዌል በሚል መጠሪያም የሚታወቅ ሲሆን ሦስት ሜትር ርዝመትና 200 ኪሎ ግራም የሚመዝን በመሆኑ በውኃ ውስጥ ከሚገኙ የዓሳ  ዝርያዎች ትልቁ አድርጎታል፡፡
  • ግመል – የግመል እበት ምንም መድረቅ ሳያስፈልገው እንደ ነዳጅ መጠቀም ይቻላል፡፡
  • ኮራን – ይህ ሥጋ በል እንስሳ በአሜሪካ ይገኛል፡፡ ያደነውን ምግብ ከመብላት በፊት ውኃ ውስጥ እየደጋገመ በማውጣትና በማስገባት ይደፍቀዋል፡፡ በጣም የሚገርመው ይህ እንስሳ ምግቡን ለምን ምክንያት እንደሚያጥብ ሁነኛ መልስ አለመገኘቱ ነው፡፡
  • የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን መጽሔት፤

(መጋቢት 2005)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...