Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት ሥርዓት ሊታሰብ አይገባም

አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት ሥርዓት ሊታሰብ አይገባም

ቀን:

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ አዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ገጽታ ተፈጥሯል፡፡ በአንድ በኩል ስማቸውና ቋንቋቸው እንኳን በወጉ ያልታወቁ አናሳ (Minority) ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ማግኘታቸው የፈጠረላችሁ መነቃቃት አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ባሉት ጊዜያት በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖትና በመሳሰሉት ሁሉንም ይጠቀልል የነበረው አሃዳዊ አስተሳሰብ ሁለንተናዊ ተፅዕኖ ቀንሷል፡፡ ቢያንስ ወደ እኩል ዕውቅና የሚያመጣ መንገድም ተጀምሯል ማለት ይቻላል፡፡

በዚህ መሀል ግን በየትኛውም ሥርዓት ሊገጥም እንደሚችለው የተለያዩ መደነቃቀፎችና እንቅፋቶች አጋጥመዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ሊከሰቱ የቻሉት ደግሞ፣ በመንግሥት የውስጥ ችግርና በማኅበረሰቡ ውስጥም ባሉ የተዛቡ አስተሳሰቦች ነው፡፡

መንግሥት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ሲያቅተው፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት አሠራሩ ሲዳከም፣ ዴሞክራሲያዊነት በገዢው ፓርቲ ውስጥ ሲኮሰምን፣ በተፃራሪው አድርባይነትና ‹‹ምን አገባኝ‹‹ ባይነት ሲንሰራፋ ለውድቀት መንደርደር ይጀመራል፡፡ በዚህ ላይ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነትና ሌብነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከቱ መምጣታቸውም ታይቷል፡፡

በሕዝቡ ዘንድም ቢሆን ኋላቀር አስተሳሰቦችን የመሸከም ነገር እያገረሸ ይሄዳል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደታየው ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት፣ አክራሪነትና ጽንፈኝነት በአገሪቱ ውስጥ ሥር እየሰደዱ ያሉ በሽታዎች ሆነዋል፡፡ ለነገሩ መንግሥታዊ አካሉም ቢሆን ከሕዝቡ ውጪ ያለ ግዑዝ ነገር ባለመሆኑ፣ የእነዚህ ዝንፈቶች ተሸካሚ መሆኑ አልቀረም፡፡ በተጨባጭም ሆኗል፡፡

ከዚህ አንፃር የትግራይ ሕዝብና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የበለጠ ተጠቃሚ፣ በሥርዓቱም አድራጊ ፈጣሪ ሆነዋል የሚለውን እሳቤ ፖለቲካዊ አንድምታ ማየት ይጠቅማል፡፡፡ ይኼ አስተሳሰብ ዛሬ ዛሬ አደባባይ ወጥቶ ለውይይት  ቢበቃም ውስጥ ውስጡን የማኅበረሰቡ አጀንዳ ሆኖ የከረመ ነው፡፡ ይኼ ከጠባብነትም ይባል ከትምክህት አስተሳሰብ የመነጨ ጉዳይ ግን መነሻ መሠረት የለውም ለማለት ያዳግታል፡፡

አንደኛው ትግርኛ ተናጋሪው ወገን ከ25 ዓመታት በፊት በነበሩት ሥርዓቶች እንደ ሌሎች ሕዝቦች የተለያዩ ጭቆናዎች ደርሰውበታል፡፡ በአንድ በኩል እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች የብሔርም ሆነ የመደብ ጭቆና ደርሶበታል፡፡ በሌላ በኩል ከዚሁ ማኅበረሰብ በወጡ የትጥቅ ትግል አራማጆች ምክንያት ወደ ሁለት አሥርት ዓመታት ገደማ አካባቢው የጦርነት አውድማ ነበር፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ሞተዋል፡፡ ከዚህ በላይ አካል ጎድሏል፡፡ የተሰደደውም ቁጥሩ ከፍ ያለ ነው፡፡

እነዚህ ቀዳሚ የመከራ ገፈት ቀማሾች በአገሪቱ አዲስ ሥርዓት ከተመሠረተበት ከ1984 ዓ.ም. ወዲህ ከፍተኛ የተሳትፎና የእኔነት ስሜት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በአንድ በኩል ለዓመታት የዘለቀው ጦርነት፣ ሞትና ስደት ሲቆም ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጋር ፊታቸውን ወደ ተረጋጋ ሕይወትና ልማት ለማዞር ችለዋል፡፡ በሌላ በኩል አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች በመስዋዕትነት የተገኘው ሥርዓት የሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች ሆኖ ፍሬ አፍርቶ ማየትን የሚሹ ለመሆናቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ ነገር ግን ከሰው ሰው ሊለያይ ቢችልም የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት አንድ የሆኑ ያህል ለሥርዓቱ የተሻለ ውግና ያላቸው ደግሞ አሉ፡፡ በአዲሱ ሥርዓት መገንባት ደስተኛ ያልሆኑና ከቀድሞዎች አገዛዞች ተጠቃሚ የነበሩ ኃይሎች ደግሞ እነዚህን ወገኖች ዒላማቸው አድርገው ለዓመታት እየዘመቱባቸው ነው፡፡

በመሠረቱ አሁን ያለው ሥርዓት አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት ሰፊ ዕድል ፈጥሯል ቢባልም፣ የትግራይ አብዛኛው ሕዝብ የተሻለ የመጠቀሙ ነገር ግን በጣም አሳሳች ነው፡፡ አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

አንደኛው በጥረትና በከፍተኛ የእኔነት ስሜት ለሥራ እየተረባረበ ያለ ወገን አለ፡፡ ለአብነት ያህል በትግራይ ክልል ያለውን አርሶ አደር መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ ይኼ ሰው ሠራሽ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮ ጭምር ጫና ያሳደረበት ማኅበረሰብ ያንጋጠጡ ተራሮችና ያልተመቹ መሬቶችን በደን እየሸፈነ፣ ጠንካራ የሚባል የመሬትና የውኃ ዕቀባ ሥራ እያከናወነ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እያየ ነው፡፡ ዛሬ ክልሉ በደን ሽፋን፣ በመስኖ ሥራ፣ በግብርና ምርታማነት ብሎም በገጠር ተጓዳኝ ሥራዎች (የንብ ማነብ፣ የእንስሳት እርባታ፣ የሳርና የመኖ ምርት፣ . . . ወዘተ) አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡ የዚህ ጥረት ውጤት ነው፡፡

ለዚህ ወሳኝ ተግባር የትግራይ ክልል አርሶ አደር የተበጀተለት የተለየ ገንዘብ ወይም ዝናብ ሊኖር አይችልም፡፡ ነገር ግን ቀድሞም በብዙ ፈተናዎች ያለፈው (እንደ ቻይናና መሰል ሕዝቦች) አርሶ አደር ቀን ከሌት የቤተሰቡን ጉልበት አሟጦ በመሥራቱና በጥብቅ ዲሲፕሊን በመንቀሳቀሱ ተራሮችን ምንጭ ማድረግ ጀምሯል፡፡ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም የፖለቲካ አመራሩና የሙያተኛው ተነሳሽነትም ቢሆን በአንፃራዊነት የተሻለ እንደነበር ሊካድ አይቻልም፡፡  

በሌላ በኩል በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ያለው ልማታዊ የሚባሉ የክልሉ ተወላጆች የሥራ ተነሳሽነትም ልምድ የሚወሰድበት ነው፡፡ ከትንሽ ጋራዥ ተነስቶ በጥረቱ መገጣጠሚያ የከፈተ፣ ከቆላማ አካባቢ ወርቅ ከማውጣት አልፎ ባለትልቅ ድርጅት የሆነ፣ ከትንሽ ግሮሰሪ ባለኮኮብ ሆቴል የገነባ፣ ወዘተ ማየት ይቻላል፡፡ ከዚህም በላይ በተለያየ አጋጣሚ ከአገር ተሰዶ በውጭው ዓለም ያጠራቀመውን ሀብት ይዞ ወደ አገር ተመልሶ በማፍሰስ ተጨማሪ ሀብት ያፈራው ተጋሩ (የትግራይ ተወላጅ) በርከት ያለ መሆኑን ማስተባበል አይቻልም፡፡

በእርግጥ ይኼ ተነሳሽነት ሥርዓቱ የፖለቲካ ዋስትና እንዲፈጠርለት ከመተማመንም ሊመነጭ እንደሚችል እርግጥ ነው፡፡ ምንም ተባለ ምን ግን በቀድሞዎቹ ሥርዓቶችም ጊዜ ቢሆን በጥረታቸው ተወዳድረው ሀብት እንዳፈሩት የአካባቢው ተወላጆች ሁሉ፣ ባለፉት 25 ዓመታትም ተበድረውም ይሁን ተጋግዘው ሕይወታቸውን የቀየሩ፣ ሀብት ያፈሩና ለአገር የሚጠቅም ልማታዊ ሥራ የጀመሩ የዚያ ማኅበረሰብ አባላት የሚበረታቱና ልምዳቸውም ትምህርት የሚቀሰምበት ነው፡፡ ዋናው ዋስትና ተገቢውን ግብርና ሕዝባዊ ኃላፊነት እየተወጡ እንዲሠሩ መደረጉ ብቻ ነው፡፡

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መራሹ መንግሥት የሕዝብ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ያዋሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ መካከለኛ መሪዎችና ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ግን አካሄዳቸው መፈተሸ አለበት፡፡ በታሪክ አጋጣሚ የደርግ ሥርዓት ሲወድቅ በትግል ላይ የነበሩ ሰዎች እስከ ከፍተኛ ባለማዕረግ መኮንንነት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ተራ ካድሬ የነበረውም ከሚኒስትርነትም አልፎ በጡረታ እስከ መተካት ደርሷል፡፡

በእነዚህ 25 ዓመታት የሕዝብ አደራ የመወጣት ጊዜያት ግን በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ አሻራቸውን ካሳረፉ ጀግኖች በተለየ ሁኔታ የግል ኪሳቸውን ያደለቡ፣ በኔትወርክና በቡድን አሠራር፣ እንዲሁም በወንዜ ልጅነት የተጠቃቀሙ የሉም ሊባል አይችልም፡፡ ከዚህ መሬት ላይ ያረበበ ሀቅ ሊወሰድ የሚችለው ትምህርት አካሄዱ አጥፊና አገር በታኝ እንደሆነ መገንዘቡ ላይ ነው፡፡ የሙሰኝነትና የሥልጣን ትስስርን መበጣጠስ እንደሚገባ ነው፡፡

በመሠረቱ አሁንም ድረስ ራሱ የሥርዓቱ አመራርና ካድሬ (በተለይ የሌላው ብሔር) ብሎም ሕዝቡ በስፋት የሚያነሳው ‹‹የብሔር ርስት የሚመስሉ አሿሿሞች ይፈተሹ›› ጥያቄ መነሻውም ይኼው ያላግባብ የመጠቃቀም አባዜ ነው፡፡ መንግሥት ራሱም እንደ አመነው የሥልጣን አተያዩ የተንሸዋረረ በሆነበት አገር ውስጥ እውቀት፣ ክህሎትና ሥነ ምግባር ብቻ ሳይሆን የብሔር ምጥጥን የሁሉም ነገር ማጣፈጫ መሆኑ አይቀርም፡፡ ለጊዜውም ቢሆን መተማመንን የሚያሰፍነውም ይኼው አሠራር ብቻ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በፌዴራሉ መንግሥት ደረጃ በተለያዩ ተቋማት የሚታየውን ገጽታ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ የሥርዓቱ መጠበቂያ ምሰሶዎች ለአደጋ  በሚጋለጡበት ደረጃ ከክህሎትና ከቁርጠኝነት ውጪ ሁሉንም ብሔር ያሰባጠሩ ናቸው ባይባልም፣ መተማመንና አገራዊ ገጽታን በሚፈጥር ደረጃ መመጣጠን እንዳለባቸው ግን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይኼን አለማድረግ ደግሞ ግልጽነትና ተጠያቂነት እየደበዘዘ ለብልሽት እንደሚያጋልጣቸው፣ አሁንም ጥገኛ በሆኑ ኃላፊዎች በግልጽ ታይቷል፡፡

በሌላ በኩል በማወቅም ይሁን ቸል በማለት የክልሉ ተወላጆች በብቸኝነት በእጅጉ በዝተው የሚታዩባቸውን ተቋማት መፈተሽ ግድ ይላል፡፡ በአንዳንድ ተቋማት የሚታየው የስብጥር መዛነፍ ተቋማቱ ምን ቢሠሩና ውጤታማ ቢሆኑ እንኳ፣ የአንድ አካባቢ ሰዎች መሰባሰቢያ እየተባሉ እሮሮ ይሰማባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሌላው ቢቀር ከጥልቅ ተሃድሶው አንፃር አሁንም ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡

በእርግጥ እዚህ ላይ ለአገር ወሳኝ የሆኑ ሥራዎችን ሁሉ ለብሔር ስብጥር እየተጨነቅን እንመድብ የሚል ኋላቀርነት ተደጋግሞ ሊቀነቀን አይገባም፡፡ ዋናው ጉዳይ ሥራዎች በግልጽነት፣ በተጠያቂነት፣ በእርስ በርስ ቁጥጥርና ብሎም በማያወላዳ ዲሲፕሊን እንዲመሩ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብቃትና ተወዳዳሪነት ዋነኞቹ የሥራው መሥፈርቶች እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ለዜጎችም እኩል ዕድል ለመፍጠር ያስችላል፡፡

በመሠረቱ ከላይ በተጠቀሱ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶችና ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ጥሩ ውጤት ሲገኝ ምሥጋና የመኖሩን ያህል፣ ጥፋትም ሲታይ ወቀሳ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ከዚህ አንፃር በሚከሰቱ የአፈጻጸም ጉድለቶች፣ ብልሹነቶችና መንገዳገዶች ሁሉ ተጠያቂው አንድ ወገን ብቻ እንዳይሆንም ተሰባጥሮ  በአንድነት መንቀሳቀሱ አስፈላጊና ተገቢ ነው፡፡

በግሌ ከወራት በፊት በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋትና ከዚያም ወዲህ በተከታታይ በተካሄደው መንግሥታዊ ማብራሪያና ስብሰባ ‹‹የትግራይ የበላይነት አለ/የለም›› የሚል ውዝግብ ሳዳምጥ ቆይቻለሁ፡፡ ጉዳዩ መነሳቱና አደባባይ መውጣቱም ይበጀናል እንጂ የሚጎዳን ነገር የለም፡፡

‹‹የበላይነቱ የለም!›› በማለት ሊያስረዱ የሚሞክሩት የመንግሥት ሰዎች አንዳንድ ማብራሪያ ‹‹ዶሮን ሲያታልሏት  . . . ›› እንዳይሆን በአግባቡ መታየት አለበት፡፡ ምክንያቱም ‹‹ሥርዓቱ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች እንዲሆን አይፈቅድም፣ ለክልሎች የበጀት ድልድል የሚደረገው በፍትሐዊነት ነው፡፡ ክልሎች ባለመሥራታቸው ወደ ሌላ ጣት መቀሰር ነው . . . ›› የሚለው አገላለጽ በራሱ ሙሉ አይደለም ባይ ነኝ፡፡  

ይልቁንም ብዙኃኑ የትግራይ ሕዝብ የሕይወት ዋጋ ባስከፈለው የትጥቅ ትግል በቁርጠኝነት ተሠልፎ በፅናት እንዲታገለው ሁሉ፣ አሁንም በድህነት ላይ በትጋት መነሳቱን ማሳየት አንዱ ጉዳዩ መሆን አለበት፡፡ በተቃራኒው በጥገኝነትና በአቋራጭ ለብልፅግና እየተንደረደረ ያለ ጥገኛም ሥርዓቱን ለብልሽት እንዳያጋልጠው ሊነጠል ይገባል፡፡ ለአብነት ያህል በጋምቤላ እርሻ ላይ እንደታየው (ከባንክና መሬት ሰጪው ጋር የተሳሰረ ነጠቃ) በአዲስ አበባ ሕገወጥ መሬት ወረራ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ የቀረጥና የግብር እፎይታ ‹‹ጨዋታ›› ላይ፣ እንደሁም የኮንትሮባንድና መሰል ዝንፈቶች ላይ በመንጠላጠል በስም የሚነግድ የለም ሊባል አይችልም፡፡

በእርግጥ ሙስናም ሆነ አጭበርባሪነት የብሔር ባርኔጣ ሊበጅለት አይችልም፡፡ አይገባምም፡፡ ሥርዓቱን ማስተካከል እንጂ ማንም ቢሆን ክፍት በር ካገኘ ዘው ማለቱ አይቀርም፡፡ የትግሪኛ ተናጋሪ ወገኖች ለእንዲህ ዓይነት ‹‹መጠርጠርና ሐሜት›› የሚጋለጡበት ሁኔታ ግን አለ፡፡ በተለይ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በማንነት ስም ለመጠቀም ዕድል ስለሚኖር ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን በቅርቡ በዚሁ ጋዜጣ ‹‹ተሟገት›› ዓምድ ላይ ‹‹የተሃድሶ መድረኮች የክርክር ከፍታዎች›› በሚል ርዕስ ሐሳባቸውን ያሰፈሩት አቶ መንግሥቱ መስፍንን ጽሑፍ መለስ ብዬ ልጠቅስ እወዳለሁ፡፡ በአንድ በኩል ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› የሚለው ፅንፈኛ ፖለቲከኛ፣ በሌላ በኩል የአገራችንን አንድነት የማይሹ ወገኖች ‹‹የትግራይና ሕወሓት የበላይነት አለ፣ ዘረፋው ተባብሷል›› ሲሉ የሚነዙትን ልብ ወለድ በጭፍን መቀበል፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ለፍቶ አዳሪ ሕዝብ ኑሮና ሥነ ልቦና ያለመገንዘብ ውጤት ነው፡፡ ትርፉም መጠራጠርና ቅሬታ ከመፍጠር ውጪ አይሆንም፡፡

ይኼ ማለት ግን ተስፋዬ ገብረአብ የተባለው ጸሐፊ እውነቱን ይሁን ውሸቱን ‹‹የጋዜጠኛው ማስታወሻ›› (2001) በሚለው መጽሐፍ ገጽ 24 አካባቢ ሕወሓት በትጥቅ ትግሉ ወቅት የከፈለውን ዋጋ ያህል ልዩ ተጠቃሚ፣ ሰፊ የሥልጣን ቦታና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩለት የሚለው የሞኝ ብሒል ውስጥ መቀርቀር ትርጉም የለውም፡፡ ይህ ዓይነቱን አገር የሚበትን አካሄድ ከወዲሁ መገንዘብ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡

በአጠቃላይ በተለያዩ መድረኮች እየተደመጠ እንዳለው የዘንድሮው ተሃድሶው አንዱ አንኳር ጉዳይ ይኼው ነው፡፡ ግን ኢትዮጵያውያን እውነታውን  በማጤን፣ ግድፈታችንን በመተራረም፣ የአባባሉን ፖለቲካዊ አንድምታ በማጤን ‹‹የትግራይ የበላይነት›› ቅላፄን በሚዛናዊነት ልንፈትሽ ይገባል፡፡ በውጤቱም ይበልጥ መተማመን የሚጥር ደረጃ ላይ መድረስ ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ያለባቸውን ትልቅ ኃላፊነት ያህል ማንም ሊኖርበት አይችልም፡፡ ምክንያቱም አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት ሥርዓት ሊታሰብ አይገባምና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

    

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...