Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘመኑን ምሰሉ!

የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች) ከደረሱበት የዕድገት ደረጃና ካሉበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲቃኙ ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ በአብዛኛው ማለት ይቻላል ‹‹ዴሞክራሲ›› የሚባለውን ጽንሰ ሐሳብ በስያሜም ሆነ በዓርማነት ያነገቡ ቢሆንም፣ ከዴሞክራሲ እሴቶችና ትሩፋቶች ጋር ያላቸው ቅርርብ ግን በጣም አጠያያቂ ነው፡፡ ያለፈውን ግማሽ ክፍለ ዘመን የአገሪቱን የፖለቲካ ኃይሎች አሠላለፍና መስተጋብር በአንክሮ ለሚታዘብ ሰው፣ የተጓዙበት መንገድና በመሀላቸው የዘለቀውና ያለው ግንኙነት ጤናማ እንዳልሆነ በቀላሉ ይገነዘባል፡፡ ሥልጣን ላይ ካለው ኢሕአዴግ ስንጀምር የጉልበተኛነትና ሁሉንም ጠቅልሎ የመያዝ አባዜ የተጠናወተው ሲሆን፣ በተቃራኒው ጎራ ያሉት ደግሞ በአብዛኛው የሚያመሳስላቸው ከአጉል እልህና ብልጠት ከጎደለው አስተሳሰብ ያልተላቀቁ ናቸው፡፡ ያለፉት 25 ዓመታት የሚያሳዩንም አንድ ግዙፍ ኃይልና  ብዛት ያላቸው የተበታተኑ፣ ክንዳቸው የዛለ፣ ግራ  የተጋቡና የኮሰመኑ ፓርቲዎችን ነው በዚህች ምድር ማፍራት መቻሉን ነው፡፡ ከዚህ ዘመን ትውልድ ፍላጎትና ምኞት አንፃር ሲታይ ሁኔታው በጣም ያሳዝናል፡፡ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይቻልም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሠረቱት የመንግሥት ሥልጣንን በምርጫ አሸንፎ ለመያዝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ ፕሮግራሞችንና የማስፈጸሚያ ሥልቶችን ለመራጮች በማሳወቅ ፍላጎታቸውን ያሳካሉ፡፡ ይህ በዓለም የሚታወቅ መሠረታዊ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕውቅና በማግኘት ደጋፊዎችንና አባላትን ማፍራት የሚችሉት የፖለቲካ ምኅዳሩ በተመቻቸበት ዴሞክራሲያዊ ዓውድ ውስጥ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ነፃ፣ ፍትሐዊና ትክክለኛ ምኅዳር እንዲፈጠር ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መሆን የግድ ይላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማንኛውንም ዓይነት ርዕዮተ ዓለም ይከተሉ ወይም የፖሊሲ አጀንዳ ይኑራቸው የሚዳኙት በመራጩ ሕዝብ እስከሆነ ድረስ ራሳቸውን ለዴሞክራሲ ማስገዛት አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲ በብዘኃን ይሁንታ የሚነገነባ ሥርዓት ስለሆነ፡፡ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለከት ግን ገና ብዙ ይቀራል፡፡ ከተስፋ ሰጪ ነገሮች ይልቅ ተስፋ የሚያስቆርጡት ይበዛሉ፡፡

በተደጋጋሚ እንደተባለው ባለፉት 25 ዓመታት በዴሞክራሲው መስክ የታየው ጉዞ እጅግ በጣም አዝጋሚ ነው፡፡ በአምስቱም ጠቅላላ ምርጫዎች የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የበላይነት የነገሠበት፣ አልፎ አልፎ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለፓርላማ መቀመጫ ቢበቁም ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የጠፉበትና የፖለቲካው ምኅዳር ጨርሶ የተዳፈነበት ነበር፡፡ ኢሕአዴግ መንግሥት የሚመራ ፓርቲ በመሆኑ ጡንቻው የፈጠረመ፣ ሁሉም ቦታ በቀላሉ መድረስ የሚችል፣ አቅም የሌላቸውን የሚደፈጥጥና የማይቋቋሙት ባለጋራ ነው፡፡ በዚህ ላይ ወትሮም እንደ ነገሩ የሆኑትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መበታተን ቀላል ስለሆነ፣ ለፍትሐዊ ምርጫ አለመኖርና ለምኅዳሩ መዘጋጋት አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ እጅግ በጣም ከዘገየ በኋላ የምርጫ ሥርዓቱን በማስተካከል ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለ ዕድል የሚያገኙበት መደላድል ለመፍጠር ቃል ተገብቷል፡፡ በዚህም መሠረት ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመደራደር በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ይጠቅሙናል ያሉዋቸውን ሐሳቦች በማካተት ፕሮፖዛል አቅርበው ወጥ የሆነ የመደራደሪያ ደንብ ለማዘጋጀት ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ደግሞ አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮች ካልታዩ ውጤቱ ወደነበሩበት መመለስ ሊሆን ይችላል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘመኑን ምሰሉ ሲባል ከዘመኑ አስተሳሰብና ፍላጎት አንፃር ራሳችሁን አዘጋጁ ማለት ነው፡፡ ይህ ዝግጅት ምርጥ የሚባሉ ተሞክሮዎች ከዓለም ዙሪያ የሚቀሰሙበት ሲሆን፣ ከትናንት ድክመቶችና ውድቀቶችም መማር ያስፈልጋል፡፡ ተመሳሳይ ስህተቶችን ለዓመታት እየደጋገሙ ውጤት ማግኘት እንደማይቻል በሚገባ ታይቷል፡፡ የአገሪቱ ዕድገት የሚለካው በቁሳዊ ሀብት ብቻ አይደለም፡፡ የሰዎች አስተሳሰብና ሥነ ልቦናም ማደግ አለበት፡፡ ሰብዓዊ መብቶች በማይከበሩበትና ከሕግ በላይ የመሆን አባዜ በበረታበት አገር ውስጥ ሕንፃ ቢደረደር፣ ባቡር ቢርመሰመስ፣ ፋብሪካዎች እንደ እንጉዳይ ቢፈሉና መንገዶች በስፋት ቢዘረጉ መግባባት ከሌለ ዋጋ ቢስ ነው፡፡ በፖለቲካው መስክ የሚታየው ቅያሜና ቅዋሜ እየበረታ የሚሄደው በሕጉ መሠረት የተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲዋከቡ፣ መሥራት ሲያቅታቸውና ከዚያም የባሰ ጉዳት ሲያጋጥማቸው ነው፡፡ ሕዝብ እንዲህ ዓይነቱን ጭቆና ሲያይ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ለስደት ይነሳል፡፡ ከዚህ ዘመን ጋር የማይመሳሰሉ ድርጊቶች ሲከናወኑ እንደ አገርም ያሳፍራል፡፡

ከዚህ መሰሉ ማጥ ውስጥ በመውጣት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንደገና መነሳት ያስፈልጋል፡፡ የተበላሹ ነገሮችን አስተካክሎ ለአገር ሰላምና መረጋጋት የሚበጅ ነገር ላይ መምከር ተገቢ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎቹ ያለፉትን ዓመታት አስከፊ ጉዞዎች ፋይል ዘግተው መነጋገር ሲጀምሩ፣ ከዚያ ብልሹ ግንኙነት ጋር ተያይዘው የመጡ የማይረቡ እንካ ሰላንቲያዎችን ማራገፍ አለባቸው፡፡ በጥላቻና በመናናቅ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት አይጠቅምም፡፡ ውይይትም ይሁን ክርክር፣ ጭቅጭቅም ይሁን ድርድር ለማድረግ ሲዘጋጁ ለመነጋገር እንቅፋት የነበሩ ዘመን ያለፈባቸውን መሰናክሎች ማስወገድ ግድ ይላቸዋል፡፡ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ተደራዳሪ አካል ከቅርፅ ይልቅ ይዘት ላይ፣ ከታይታ ይልቅ ተግባር ላይ ያተኩሩ፡፡ ቃላትን በመሰንጠቅና ከአጀንዳ ጋር የማይሄዱ ነገሮችን በመደንቀር ተደራዳሪ መሆን አይቻልም፡፡ ከልቡ የፖለቲካ  ምኅዳሩ እንዲከፈት የማይፈልግ ተደራዳሪ በቅድመ ሁኔታዎች አማካይነት አጥር ማበጀት ሲጀምር ችግር አለ፡፡ አንድም ለመደራደር በቂ የሆነ ዝግጅት የለውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሚፈለገው ዓላማ ግቡን እንዲመታ አይፈልግም፡፡ ዘመኑ በድርድር የጋራ ተጠቃሚነት የሚገኝበት እንጂ፣ አንዱ ጠቅልሎ ሌላው በዜሮ የሚወጣበት አይደለም፡፡ እልህ መጋባትና ጨለምተኝነት አይሠሩም፡፡ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር አይሄዱም፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ ድርድር ስታመሩ በመጀመሪያ ሕዝብን አክብሩ፡፡ የአገሪቱ የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብ እየተገፋ አገሪቱ ምን ደረጃ ላይ ደርሳ እንደነበር ፍፁም መዘንጋት አይቻልም፡፡ ኢሕአዴግ ከሕዝብ ጋር ተጣልቶ ምን አተረፈ? ምንም፡፡ ተቃዋሚዎች በምሬት የገነፈለውን ሕዝብ አመፅ እንኳን መምራት ባለመቻላቸው ምን ተጠቀሙ? ምንም፡፡ ይልቁንም በሩቅ ርቀት ያሉ ኃይሎች የማይቆጣጠሩትን አመፅ አቀጣጥለው አገር ሊያወድሙ አልነበረም? አዎ፡፡ ይኼ ይካዳል? በፍፁም፡፡ ስለዚህ ይህ እየተጀመረ ነው የሚባልለት ድርድር ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ቢራመድ ለአገር ይበጃል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣኑን ብቻ የሚያይ ከሆነ አሁንም ጭልጥ ያለ ስህተት ውስጥ እየገባ መሆኑን ማጤን ይገባዋል፡፡ ከሥልጣን በላይ የአገርና የሕዝብ ህልውና አለ፡፡ ይህ ሕዝብ ተከብሮ የሥልጣን ባለቤት መሆኑ በተግባር መረጋገጥ አለበት፡፡ በተለመደው መንገድ አገር ማስተዳደር ፈፅሞ አይቻልም፡፡ ፈፅሞ አያዋጣም፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህ ድርድር እንዲሳካና የነበረው ጨፍጋጋ የፖለቲካ ገጽታ እንዲለወጥ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ጊዜ ባለፈባቸው መከራከሪያዎችና መደራደሪያዎች ሳይሆን፣ ዘመኑን የሚመጥኑ ሙግቶችንና መፍትሔዎችን ይዘው ይቅረቡ፡፡ እርስ በርስም ከመሻኮት ወጥተው የጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲ ባህሪ ይላበሱ፡፡ የኮሰመነውን ገጽታቸውን በፍጥነት ይቀይሩ፡፡ እጅ መጠምዘዝ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ሳይሆኑ በቅድመ ሁኔታዎች ላይ መሟዘዙን ይተው፡፡ ወደ ፍሬ ነገሩ ይግቡ፡፡ አሁን ሕዝብ ይህንን ድርድር ይጠብቃል፡፡ ብቁና ንቁ ተደራዳሪዎችን ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘመኑን ምሰሉ!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...