Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች በጋራ ባረቀቁት የክርክርና የድርድር ደንብ ይዘት ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዙ

ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች በጋራ ባረቀቁት የክርክርና የድርድር ደንብ ይዘት ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዙ

ቀን:

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና 22 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ባረቀቁት የድርድርና የክርክር ደንብ ይዘት ላይ በጥልቀት ለመወያየት ለመጪው የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ያዙ፡፡

ፓርቲዎቹ ድርድር የሚከራከሩበትና የሚደራደሩበት ረቂቅ ደንብ፣ የሚገዙበትን የአሠራር ሥነ ሥርዓት ራሳቸው ባቀረቧቸው ሐሳቦች የተጠናከረና 22 ገጽ ያለው ነው፡፡

ረቂቅ ደንቡ ‹‹የፓርቲዎች የክርክርና የድርድር አሠራር ደንብ›› የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል፡፡ መድረክን ወክለው የተገኙት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በረቂቅ ደንቡ ርዕስ ላይ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የረቂቅ ደንቡ ርዕስ ድርድር እንጂ ክርክር ሊሆን አይገባም በማለት ያነሱት ጥያቄ፣ የዕለቱን ውይይት በመሩት የኢሕአዴግ ተወካይና የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በሆኑት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተቋርጧል፡፡

አቶ ሽፈራው እንደሚሉት የዕለቱ ውይይት ሁሉም ፓርቲዎች የሥነ ሥርዓት ደንቡን ለማዘጋጀት ያስገቧቸው ሐሳቦች ተጠቃለውና ተስማምተው ስለመቅረባቸው መግባባት ለመድረስ እንጂ፣ ይዘቱ ላይ ጥልቅ ውይይት ለማካሄድ አይደለም፡፡ አቶ ሽፈራው በሰጡት ማብራሪያ መሠረትም የተጠቃለለው ረቂቅ ደንብ ሙሉ ለሙሉ እንዲነበብ ተደርጓል፡፡

ደንቡ ከያዛቸው ነጥቦች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ክርክርና ድርድሩ የሚደረግበት ዓላማ ምን ሊሆን ይገባል የሚለውን የተመለከተ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት በርካታ ሐሳቦች የቀረቡ ሲሆን፣ ‹‹በድርድሩ ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ሐሳቦችን እንደ ግብዓት በመጠቀም የሚሻሻሉ ሕጎች ካሉ ማሻሻል፣ እንዲሁም የአፈጻጸም ጉድለቶች ካሉ ማስተካከል፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡

የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ማዳበር የሚል ዓላማ ያለው የቀረበ ሌላ ሐሳብ ተቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል፣ ‹‹በአጠቃላይ ይህ ድርድር በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሥልጣን ሽግግር ከመሣሪያ አዙሪት ወጥቶ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ በምርጫ ብቻ አሸናፊ ለሆነው ፓርቲ የሚተላለፍበት ወሳኝ ምዕራፍ እንደሚሆን በመገንዘብ፣ ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር የድርሻችንን በሀቀኝነትና በቁርጠኝነት መወጣት፤›› የሚል ሐሳብ በዓላማነት ተቀምጧል፡፡

ተሳታፊዎችን በተመለከተ በደንቡ ሊካተት ይገባል የተባሉ ነጥቦችንም ረቂቁ ይዟል፡፡ ከእነዚህም ሐሳቦች መካከል ድርድርና ክርክሩ መካሄድ ያለበት በኢሕአዴግና በ22 አገር አቀፍ ፓርቲዎች መካከል እንዲሆን የሚል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢሕአዴግና መሪ ተደራዳሪ ፓርቲዎች እንዲሆን የሚጠይቅ ይገኝበታል፡፡

ረቂቅ ደንቡ አደራዳሪዎችን በተመለከተም ያስቀመጣቸው በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ከእያንዳንዱ ፓርቲ በዙር የሚወከሉ ድርድሩን እንዲመሩት በማለት የቀረበ ይገኝበታል፡፡

በሌላ በኩል ድርድሩ ገለልተኛና ነፃ በሆኑ 11 አደራዳሪዎች እንዲመራ የሚጠይቅ ተቀምጧል፡፡

በድርድሩ ላይ ታዛቢዎች እንዲገኙ በረቂቅ ደረጃ በማስቀመጥ የአገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች እንዲገኙ፣ የአገር ውስጥ ታዛቢዎች ብቻ እንዲገኙ የሚሉ ሐሳቦችን ረቂቁ አካቷል፡፡

የሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ ሚዲያዎች ድርድሩን መከታተል  እንደማይችሉና መግለጫ እንደሚሰጣቸው፣ ፎቶና ቪዲዮ ብቻ አንስተው እንዲወጡ የሚሉ ሐሳቦች ተካተዋል፡፡

በይዘቱ ላይ ለመወያየት ለመጪው የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዟል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...