መንግሥት ለኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን 18 ቢሊዮን ብር ካፒታል ሊጨምር መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡
መንግሥት ወደዚህ ውሳኔ የደረሰው ከኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ ሀብት አብዛኛው በዕዳ የተሸፈነ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ የኮርፖሬሽኑ የተፈቀደ ካፒታል 39.9 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የድርጅቱ አጠቃላይ ሀብት 128 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በመሆኑም ይህ የተፈቀደ የ18 ቢሊዮን ብር ካፒታል ተቀባይነት ካገኘ፣ የኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ የተፈቀደ ካፒታል 57.9 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ ከዚህ አጠቃላይ ሀብት 80 በመቶ የሚሆነው ወይም ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በዕዳ የተሸፈነ በመሆኑ፣ የኮርፖሬሽኑን የፋይናንስ ጤንነት ለመመለስ የካፒታል ጭማሪው አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ማቋቋሚያ ደንብ ከአጠቃላይ ሀብቱ በላይ በዕዳ ሊጠየቅ እንደማይችል የሚገልጽ መሆኑንም በማጠናከሪያነት ተጠቁሟል፡፡
የኮርፖሬሽኑ የተፈቀደ ካፒታል 39.9 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ክፍያዎች በአሁኑ ወቅት የኮርፖሬሽኑ የተከፈለ ካፒታል ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አሁን ባለው ካፒታል መጠን ተጨማሪ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ብድር ለማግኘት ያዳግተዋል የሚሉት ምንጮች፣ ከ18 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ካፒታል መንግሥት እንዲፈቅድ በቦርዱ በኩል ተጠይቆ የመጨረሻው ሒዲት ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ መንግሥት የፋይናንስ እጥረት ያለበት በመሆኑ የካፒታል ጭማሪውን በምን ዓይነት መንገድ እንደሚደረግ ለማወቅ አዳጋች ቢሆንም፣ ምንጮች ግን ወለድ በማይከፈልበት የዕዳ ሰነድ ሊከፈል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡