Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ልጆች ባሉበት ቦታ ሁሉ ምግብ ይኑር ነው የምንለው››

ወ/ሮ ፍሬዓለም ሽባባው፣ የኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢኒሼቲቭ መሥራችና ዋና ዳይሬክተር

     ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው የኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢኒሼቲቭ መሥራች ባለቤትና ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የተወለዱት አዲስ አበባ ሲሆን ያደጉት ደግሞ ቻግኒ ነው፡፡ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በባህርዳር ከተማ አጠናቅቀው ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ አቅንተው ከካሊፎርኒያ ሜሪት ኮሌጅ በቢዝነስ ማኔጅመንት፣ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ በሂውማንና ሶሻል ስተዲስ የመጀመሪያ ዲግሪና በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በዴቨሎፕመንት ስተዲስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ የሦስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ በኢኒሼቲቩ ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሮዋቸዋል፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢኒሼቲቭን ለመመሥረት ያነሳሳዎት ወይም ምክንያት የሆነው ምንድነው? የተቋቋመውስ መቼ ነው?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡- የሕፃናት አዕምሮ (ብሬይን) በምግብ ዕጦት የተጎዳ ከሆነ አምራች፣ ፈጣሪ፣ አሳቢና ችግር ፈቺ አይሆኑም፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ የማሰብ፣ ችግር የመፍታትና የመመራመር ችሎታው በቀጥታ ከምግብ ጋር ይያያዛል፡፡ የምግብና የአዕምሮ ሳይንስ የሚለውም ይህንኑ ነው፡፡ ምግቡ ይበልጥ የሚፈለገው ደግሞ ገና በሕፃናት ዕድሜ ላይ እያሉ ነው፡፡ ካደጉ በኋላ የተጎዳውን አካል በምግብ መጠገን አይችሉም፡፡ ይህም በምርምር የተረጋገጠ ነው፡፡ ሕፃናት እየተጎዱ ሌላ ሀብት ፈጠራ የሚባል ሊኖር አይችልም፡፡ ስለመብታቸው የሚሟገቱ ሕፃናትን ይዞ የማይሄድ ሀብት ወይም ሥርዓት (ሲስተም) መጨረሻው አያምርም፡፡ በዚህም የተነሳ በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ምግብ መኖር አለበት ከሚል በጎ አመለካከት የተነሳ የኢትጵያ ስኩል ሚል ኢኒሼቲቭ በሚል መጠሪያ የሚታወቅ የበጎ አድራገጎት ማኅበር ኅዳር 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ተቋቋመ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢኒሼቲቭ በስንት ክልሎች ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡- እስካሁን የሠራነው በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ በተጠቀሱት ክልሎች በሚገኙ 23 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርተ ቤቶች የሚማሩ ሕፃናት በየቀኑ ወተት ይጠጣሉ፡፡ ለዚህም የሚሆን በድምሩ 233 የወተት ላሞች በትምህርት ቤቶች ተመድበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በአማራ ክልል በሚገኙ 13 ትምህርት ቤቶች 124፣ በኦሮሚያ ክልል ባሉ አራት ትምህርት ቤቶች 39፣ በትግራይ ክልል ሦስት ትምህርት ቤቶች 30. በአዲስ  አበባ ሁለት ትምህርት ቤቶች 20፣ በደቡብ ክልል አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ አሥር ላሞች ተመድቦላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮግራሙን የሚያስተዳድረው ኢኒሼቲቭ ነው ወይስ ለትምህርት ቤቶቹ ተላፎ ነው የተሰጠው?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡- ፕሮጀክቱን የቀረጽነው አስተዳደሩ በትምህርት ቤት እንዲመራ በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም ሠርተን፣ ሥልጠና ሰጥተን፣ እስረክበን በሰው ኃይል አደራጅተን ነው የምንወጣው እንጂ አናስተዳድረውም፡፡ የሚያስተዳድሩት ትምህርት ቤቶቹ ናቸው፡፡ ራሳቸውን እስከሚችሉ ድረስ ግን ለአንድ ዓመት ያህል ውጭ ሆነን እንደግፋቸውና ከዛ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ችለው ይመራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ልጆቹ ወተት ብቻ ነው የሚጠጡት?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡- ወተትና ዳቦ ነው የሚሰጣቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ልጆቹን ማን ነው የሚመርጣቸው?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡- ትምህርት ቤቱ ራሱ እንዲመርጥ ነው የምናደርገው፡፡ ብዙ ጊዜ የምንመክረው ግን ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት የሚመጡም ካሉ ከሕፃናት ጀምረው ወደ ላይ እንዲሄዱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለፕሮግራሙ ስኬታማነት ምን ዓይነት ሞዴል ነው የመረጣችሁት?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡- ኤስኤስኤም ማለትም ሲምፕል፣ ሰስተነብል፣ ማኔጀብል የተሰኘ ሞዴል ፕሮግራም ነው የመረጥነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሞዴል ለሁሉም ነገር ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ ማለትም የኢመርጀንሲ (የአደጋ ጊዜ)  ዕርዳታ ዓይነት አቀራረብ የሌለውና ወይም ዘላቂ የሆነ፣ ውስብስብ የሆኑ ማሽኖችን የማይጠይቅ፣ ዓይነት ሞዴል ነው እየተጠቀምን ያለነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሞዴል ፕሮግራም የሚጀምረው የሰው ኃይል አደራጃጀቱ፣ ገቢና ደጋፊ ማግኘቱ ወይም ራሱን መደገፉ ተረጋግጦ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አዲስ ነገር ሳይሆን የአካባቢውን ሕብረተሰብ ዕውቀት መሠረት አድርጎ የተነሳ መሆን ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ካወቁት ያስቀጥሉታል ካላወቁት ግን ይቋረጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን ዓይነቱ አካሄድ በቅድሚያ ሙከራ ደረጃ ሠርታችሁ ነው ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ የገባችሁት? ወይስ በአንድ ጊዜ ለሁሉም አድርሳችሁ ነው የጀመራችሁት?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡- በመጀመሪያ በሙከራ ደረጃ ሠርተን ነው ወደ ሙሉ ትግበራ የገባነው፡፡ በተግባር የተደገፈ የሙከራ ሥራ የተከናወነውም ሰበታ ከተማ በሚገኝ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ የሙከራ ሥራው የተከናወነው ለአራት ወራት ያህል የነበረ ሲሆን መጀመሪያ ጊዜያዊ በረት ሠራን፣ ላሞችን አስገባን፣ በዚህም የተገኘው ውጤት በጣም ጥሩና ያልተጠበቀ ሆነ፡፡ ወዲያው ታልቦ ለሕፃናቱ ስለሚሰጥ ፍሪጅ አላስፈለገም፡፡ በትራንስፖርት ችግር ምክንያትም አይቋረጥም፡፡ ምክንያቱም ላሞቹ ያሉት በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ወተቱ ከበረት በቀጥታ ወደ ክፍሎች ነው የሚሄደው፡፡ በበረቱና በመማሪያው ክፍሎች መካከል ያለው ርቀት በጣም ትንሽ ነው፡፡ ምግብ በራቀ ቁጥር በጥራትና በተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖራል፡፡ ምግብ ቅርብ በሆነ ቁጥር ርካሽና ትኩስ (ፍሬሽ) ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ወተቱን አፍልተውና ዳቦ የሚያቀርቡት እነማን ናቸው?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡- አዘጋጅቶ የማቅረቡን ሥራ የሚያከናውኑት በደመወዝ የተቀጠሩ የተማሪዎች ወላጆች ናቸው፡፡ ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ዳያሪ ፋርም ዓይነት ነው ያቋቋምነው፡፡ በየዳያሪ ፋርሙ አንድ የእንስሳት ሐኪም፣ አምስት አላቢዎችና ወተቱን አፍልተው ለልጆች የሚሰጡ አሉ፡፡ እነዚህ ደመወዛቸው ከየት ይከፈል ስንል ወተት መሸጥ አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስን፡፡ ልጆቹ ተጠቅመው የተረፈውን እንዲሸጥ ለማድረግ በቀን ስንት ሊትር ወተት መመረት አለበት የሚለው ጥያቄ ተነሳ አንድ የፈረንጅ ላም በቀን በአማካይ 20 ሊትር ትሰጣለች፡፡ ስለዚህ ከአሥር የወተት ላሞች በቀን ከ100 ሊትር በላይ ወተት ይመረታል፡፡ ከዚህ አንፃር በቀን 35 ሊትር ያህሉን ለማኅበረሰቡ ብንሸጥ፣ የቀረውን ለልጆቹ ቢሰጥ ጥሩ ነው ብለን ነው ያሰላነው፡፡ አንድ ሊትር ወተት ደግሞ ለስድስትና ለሰባት ልጆች በቂ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በአንድ ትምህርት ቤት 10 የወተት ላሞች ቢገቡ በቀን  500 የሚሆኑ ልጆች ወተት እንዲያገኙ በማድረግ የዓመት ወጪ መሸፈን ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ለአንድ ትምህርት ቤት ስንት ላሞች ነው የተመደበው?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡ የሙከራው ሥራ ከተጠናቀቀ በኃላ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚተገበር ደረጃ (ስታንዳርድ) አወጣን፡፡ በዚህም ደረጃ ዳይሪ ፋርሙ በደንብ የተደራጀ እንዲሆን፣ አሥር የፈረንጅ ላሞች እንዲኖሩት፣ የምግብ ማብሰያውና የወተት ማፍያው ቤት፣ ስፋት፣ ቁመትና ርዝመት፣ እንዲሁም የሚቀጠሩ ሰዎች፣ የምን የምን ባለሙያዎች እንደሚሆኑ ትምህርት ቤቱ ደግሞ እዚህ ውስጥ ገብቶ ለመምራት ምን ዓይነት ሥልጠና ያስፈልገዋል የሚያደራጀውስ ኮሚቴ ምን መምሰል አለበት፣ የሚለውን በሚመለከት አንድ ዓይነት ደረጃ (ስታንዳርድ) አውጥተን በተንቀሳቀስንባቸው ክፍሎች ሁሉ ተግባራዊ አደረግን፡፡

ሪፖርተር፡- በወተት ላይ ብቻ ለምን ትኩረት ተደረገ? እንዳይሰለች ማለዋወጥ አይሻልም ነበር?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡- ልጆች ወተት በየቀኑ ቢጠጡ አይሰለቻቸውም፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ብዙ ንጥረ ነገር ያለው ነው፡፡ ሌላ ምግብ ቢቀርብላቸው ለአንድና ለሁለት ቀናት ያህል እሺ ብለው ሊመገቡ ይችላሉ፣ ዋል አደር ሲል ግን ይሰለቻቸዋል፡፡ የልጆች ባህሪ እንደዚህ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ምርጫችን ትክክል ነው፡፡ አዮዳይዝድ የሆነ ወይም በአዮዲን የበለፀገ ጨው ተጨምሮበት ከዳቦ ጋር ይሰጣቸዋል፡፡ ዳቦው የሚዘጋጀው በየአካባቢው ከሚገኘውና ከተለያዩ ጥራጥሬ ከተፈጨ ዱቄት ነው፡፡ ልጆቹ ወተቱ የሚሰጣቸው በቀን አንዴ ጠዋት ብቻ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶቹ እየተጠናከሩ ሲሄዱ ቁርስና ምሳ የማብላት አቅም ይኖራቸዋል፡፡ በተለይ ከሦስት ዓመት በኋላ ትምህርት ቤቶቹ ምሳ መስጠትና ሌላም ነገር መጨመር ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ቀጣዩ ዕቅዳችሁ ምንድነው?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ከ23,000 በላይ የሚሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ምግብ እንዲኖር ማድረግ እናስባለን፡፡ ይኼንንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠይቀው በክልሎቹ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የምግብ ፕሮግራሞችን ዲዛይን ማድረግ  ነው፡፡ ይኼም ማለት እኛ በየክልሉ እየተንቀሳቀስን የምግብ ፕሮግራም እንጀምራለን ማለት ሳይሆን የሚመለከታቸውን ተቋማት ማለትም ዩኒቨርሲቲዎች፣ የትምህርት ቢሮዎችንና የግሉን ዘርፍ ሁሉ በመቀስቀስ ወደ የሚፈለገው ፕሮግራም የማምጣት ጥረት ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በእንቅስቃሴያችሁ ውጤት ላይ ያገኛችሁት ግብረ መልስ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ፍሬዓለም፡- ወተቱ በተጀመረ በወሩ ዘግይተውና እየቀሩ የሚመጡ ልጆች ቁጥር ቀንሷል፡፡ ልጆች በትምህርት አቀባበላቸው ላይ ንቁ ሆነዋል፡፡ ትምህርት የመቀበል ፍላጎታቸው ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ትምህርት ቤቶች በየቤቱ እየተዘዋወሩና ቅስቀሳ እያደረጉ ነበር ወተት የሚጠጡትን ልጆች የሚመዘግቡት፡፡ አሁን ግን ምንም ዓይነት ቅስቀሳ ሳይደረግና የምዝገባውም ጊዜ ሳይደርስ ወተት መጠጣት የሚፈልጉ ልጆች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ልጆች ትምህርት ቤት ከመጡ በኋላ ወተት መጠጣታቸው የአዕምሮ እድገታቸው (ብሬይን ዴቨሎፕመንት) ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል? ወይስ አያደርግም የሚሉ ክርክሮች አሉ፡፡ አንዳንድ ሳይንቲስቲስቶች ልጆቹ እስከ 11 ዓመታቸው ምግብ ካገኙ የማስታወስ ችሎታቸው እንደሚሻሻል የተረጋገጡ መረጃዎች አለንም ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በዋናነት ጉዳት የሚደርሰው በ1,000 ቀናት ላይ ስለሆነ ከእነዚህ ቀናት ካመለጡ ለአካላቸው አስዋጽኦ አለው እንጂ የአዕምሯቸው ዕድገት ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም የሚሉ አሉ፡፡ እኛ በዚህ ምግብ ፕሮግራም በተጨባጭ ያየነው ውጤት ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም አንድ ብርጭቆ ወተትና አንድ ዳቦ ተሰጥቶ ነው፡፡ ይኼ ሊሆን የቻለው ወተቱ ተፅዕኖ አድርጎ ነው ወይስ ሳይቀሩ ክፍል በመገኘታቸው ብቻ የተገኘ ውጤት ነው የሚለውን ደግሞ በሌላ ምርምር ማረጋገጥ ይጠበቅብናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...