የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በበርበራ ወደብ ዙሪያ የጦር ሠፈር ለመገንባት መንቀሳቀሷ ሕገወጥ ነው በማለት፣ በዓለም አቀፍ ሕግ ክስ እንደምትመሠርት ሶማሊያ አስታወቀች፡፡
ከ25 ዓመታት በፊት ከታላቋ ሶማሊያ በራሷ ፈቃድ ነፃ የሆነችውና እስካሁን ከአንድም አገር የዓለም አቀፍ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ፣ የተባበሩት የዓረብ ኤምሬትስ በበርበራ ዙሪያ የጦር ሠፈር ለመገንባት ፈቃድ አግኝታለች፡፡ የሶማሊያ መንግሥት ግን ውሳኔውን በመቃወም ክስ ሊመሠርት መሆኑ አሳውቋል፡፡
የሶማሊያ መንግሥት ዋና ኦዲተር ኑር ጀማል ፋራህ ለፕሬስ ቲቪ እንደተናገሩት፣ ሶማሊያ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ላይ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ክስ ለመመሥረት ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡
በቅርቡ ከሶማሊላንድ መንግሥት ጋር ስምምነት በመፈራረም በአገሪቱ ትልቁ ወደብ በሆነው በበርበራ ዙሪያ የጦር ሠፈር ለመገንባት እየተንቀሳቀሰች ያለችው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ድርጊት ሕገወጥ እንደሆነ፣ የሶማሊላንድ ባለሥልጣናትም ቅሌት እንዳለበት ዋና ኦዲተሩ አክለዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት ስምምነቱ የተፈጸመው የሶማሊያ መንግሥት ሳያውቅ ዓለም አቀፍ ዕውቅና በሌለው መንግሥት ስለሆነ፣ ሕገወጥና የሙስና ቅሌት ያለበት ነው፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ያደረገችውን ስምምነት በአስቸኳይ እንድታቋርጥ በማስጠንቀቅ፣ የሶማሊያ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም የጣሰ ድርጊት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ (የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ በበርበራ ለመገንባት ያሰበችው የጦር ሠፈርና በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ በተመለከተ የተሰናዳውን ዘገባ ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡