Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየግብፅ መንግሥት በዓባይ ጉዳይ ላይ መለሳለስ እያሳየ ነው

  የግብፅ መንግሥት በዓባይ ጉዳይ ላይ መለሳለስ እያሳየ ነው

  ቀን:

  የግብፅ ፕሬዚዳንት በኬንያ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት አገራቸው በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ከተፋሰሱ አገሮች ጋር ለመተባበር፣ ከአባልነት ራሷን ካገለለችበት የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ጋር ደግሞ በድጋሚ ለመነጋገር የሚያስችል የተለሳለሰ አቋም አሳዩ፡፡

  ግብፅ በፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲና በሌሎች ባለሥልጣናት አማካይነት በአፍሪካ ቀንድም ሆነ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ አገሮች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጥበቅ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኗ ተገልጿል፡፡

  የአውሮፓውያን አዲሱ ዓመት ከገባበት ካለፈው ወር ጀምሮ ከደቡብ ሱዳንና ከኡጋንዳ ጋር ግንኙነት ለማጠናከር አዳዲስ ስምምነቶችን ያደረጉት ፕሬዚዳንት አልሲሲ፣ ቅዳሜ የካቲት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በኬንያ የአንድ ቀን ይፋ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጉብኝታቸው ወቅት ከኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ከሌሎች የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው በመወያየት በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ተፈራርመው ወደ ካይሮ ተመልሰዋል፡፡

  የግብፁ መሪ በናይሮቢ ቆይታቸው ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በንግድና በኢንቨስትመንት ለመሥራት ስምምነት ላይ ከመድረሳቸው በተጨማሪ፣ በቀጣናዊ ጉዳዮችና ሽብርተኝነትን በጋራ መዋጋትን በተመለከተ ለመተባበር መስማማታቸውን የሁለቱ አገሮች መሪዎች አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን የሁለቱ መሪዎች ውይይትና ስምምነቶች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ብቻ የተወሰኑ አልነበሩም፡፡ ይልቁንም የዓባይ ውኃ ሀብት አጠቃቀምን በተመለከተ ተወያይተዋል፡፡ በተለይም ፕሬዚዳንት አልሲሲ የውኃ ሀብቱንና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ የኬንያ አቻቸው በተፋሰሱ ተጋሪ አገሮች መካከል ያለውን አንድነትና ልዩነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እገዛ እንዲያደርጉ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡

  ከናይሮቢ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የግብፅ ፕሬዚዳንት የዓባይ ውኃን ፍትሐዊ አጠቃቀምን በተመለከተ ከኬንያው አቻቸው ጋር መነጋገራቸው ታውቋል፡፡

  ‹‹ኬንያና ግብፅ በዓባይ ውኃ አማካይነት በአንድ የደም ዝውውር የተገናኙ ያህል የረጅም ዓመታት ታሪካዊ ትስስር ያላቸው አገሮች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

  ‹‹በተፋሰሱ ውስጥ ያለውን አጋጣሚ ሁሉ ወደ ተሻለ ልማት ለማሳደግ ድጋፋችንን እናጠናክራለን፡፡ በተፋሰሱ ውስጥ የምንገኝ ሁላችንም አገሮች የእዚህን ታላቅ ወንዝ መልካም በረከቶች ወደ ላቀና የጋራ ተጠቃሚነት ደረጃ ማሳደግ አለብን፤›› በማለት ማሳሰባቸው ተሰምቷል፡፡

  ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኝ አባል አገሮችን ከያዘው የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ግብፅ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ ራሷን ከአባልነት ማግለሏ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ ግንባር ቀደምነት የተዘጋጀው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በታንዛኒያ በስድስት የተፋሰሱ አገሮች በመፈረሙ ምክንያት፣ ግብፅና ሱዳን ሲያኮርፉ ግብፅ ከኢኒሼቲቩ አባልነት ራሷን ማግለሏ አይዘነጋም፡፡

  ነገር ግን ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ የፕሬዚዳንት አልሲሲ መንግሥት በድጋሚ ወደ አባልነት ለመመለስ ሐሳብ እንዳለው ገልጾ ነበር፡፡ በኬንያ ጉብኝታቸው ፕሬዚዳንት አልሲሲ ይህንኑ ማንፀባረቃቸው ግብፅ ቀደም ብላ ይዛው ከነበረው አቋም መለሳለስ ያሳየችበት ስለመሆኑ ከወደ ናይሮቢ እየተነገረ ነው፡፡

  አንድ የግብፅ መሪ ኬንያን ሲጎበኝ እ.ኤ.አ ከ1984 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል፡፡ የአሁኑ የፕሬዚዳንት ኤልሲሲ ጉብኝትም ከ33 ዓመታት በኋላ የተካሄደ በመሆኑ በሁለቱም ወገኖች ታሪካዊ ተብሎ ተወድሷል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...