Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለኢንዱስትሪ ባለሀብቶች የሚሰጠው ማበረታቻ ፖለቲካዊ አንደምታ የለውም አለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሁለት ዓመት በኋላ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል አለ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በማኑፋክቸሪንግ መስክ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚሰጣቸው ማበረታቻዎችና የሚያካሂዳቸው የባለሀብቶች ምልመላ ሥራዎች ፖለቲካዊ አንድምታ እንደሌላቸው ገለጸ፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በመንግሥት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ይገኛል፡፡ አዋጅ ወጥቶለት፣ አዋጁን የሚያስፈጽም ደንብ ለማፀደቅ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁንና በአምራች ኢንዱስትሪዎች መስክ ባለሀብቶች የሚመረጡባቸው አካሄዶች ላይ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሩ አቶ ፍፁም አረጋ፣ የባለሀብቶቹ ምልመላም ሆነ የማበረታቻ አሰጣጡ ፖለቲካዊ ፍጆታም ሆነ የግልጽነት ችግር እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የብድር፣ ከቀረጥ ነፃ የማሽነሪ መብት፣ የታክስ እፎይታ፣ የቴክኒክና የመሳሰሉት ሥልጠናዎች የሚካተቱበት፣ ተደማምሮ እስከ 90 በመቶ የሚደርስ የፋይናንስ ድጋፍ እየሰጣቸው እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ይህ መሆኑ የመንግሥትን አሠራር ጥያቄ ውስጥ ሊከተው አይችልም ወይ ለሚለው አቶ ፍፁም ሲያብራሩ፣ መንግሥት ማበረታቻዎቹን የሚሰጠው ባለሀብቶች ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አምራችነት መግባት የሚችሉባቸውን መንገዶች ለማመቻቸት ነው፡፡ መንግሥት የመሥሪያ ሼዶችን ከማዘጋጀት ባሻገር ኢንቨስተሮችን በመመልመል እንደሚያመጣ ሲያብራሩ በተለይ የውጭ ባለሀብቶች በዚህ መስክ ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዙ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ መሠረት አቅምና ብቃቱ ያላቸው የውጭ ኩባንያዎችና ኢንቨስተሮች ተመልምለው እንዲመጡ ሲደረግ በመንግሥት ከቀረጥ ነፃ ዕድል ካልሆነ በቀር ምንም ዓይነት ብድር ከአገር ውስጥ እንደማይሰጣቸው አቶ ፍፁም አብራርተዋል፡፡ ከውጭ የሚመጡት የራሳቸውን ፋይናንስ ይዘው የሚመጡ በመሆናቸው ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋም ብድር እንደማይሰጣቸው ጠቅሰዋል፡፡

በአንፃሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲሳተፉ የሚደረገው ለሕዝብ ይፋ በሚደረግ የማስታወቂያ ጥሪ እንደሆነና አቅም ያላቸው፣ ዝግጁ የሆኑ ባለሀብቶች ይሳተፉበታል በማለት መንግሥት ለየትኛውም ባለሀብት የፖለቲካ ድጋፍ እንደማይሰጥ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ለአራት ዙር በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትና የግል ኩባንያዎች ተሳትፎ ውይይት ሲደረግበት የቆየው የኢንዱስትሪ ፓርኮች አዋጅ ማስፈጸሚያ ረቂቅ ደንብ በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይፋ ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተመራ ውይይት፣ ሰኞ የካቲት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን ሲካሄድ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎችም መንግሥታዊ ተቋማት ውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በቅርቡ እንደሚፀድቅ በሚጠበቀው ረቂቅ ደንብ ላይ በተካሄደው ውይይት ላይ ተቋማቱ ማሻሻያዎች እንዲደረጉባቸው የሚሿቸው ነጥቦች ላይ ተነጋግረዋል፡፡

አቶ ፍፁም እንደሚገልጹት ከ40 በላይ የመንግሥት ተቋማት በአገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ ላይ የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ በአንድ ተቀናጅተው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አንድ ወጥ አሠራር የሚዘረጉበት የአንድ መስኮት አገልግሎት ማቅረብ በአዲሱ ሕግ እንደሚሠሩ አብራርተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማስተዳደር የወጣው አዋጅ ቁጥር 886/2007ም ሆነ እሱኑ ተከትለው የሚወጡና የሚተገበሩ ሕጎችን በአንድ ማዕከል እያስፈጸመ አግልገሎቶችን ለማቅረብ የሚያስችል፣ እስካሁን ያልነበረ አዲስ አሠራር በኢትዮጵያ እንዲተገበር እንደሚያስችል አቶ ፍፁም ተናግረዋል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚተገበረው ለየት ያለ ሕግ ውጤታማ መሆን ከቻለ በመላ አገሪቱ እንዲተገበር ለማድረግ እንደሚፈለግም ገልጸዋል፡፡ ሕጉ ደረቅ ወደቦችን የሎጂስቲክስ ፓርኮች በሚል ስያሜ፣ ከአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በማጣመር በአንድ ወጥ አሠራር ለማስተዳደር እንደሚያስችልም ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል በአሥር ወራት ውስጥ ተገንብቶ የተጠናቀቀውና ከጥቂት ወራት በፊት ሥራ የጀመረው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከ37 በላይ ፋብሪካዎች ምርት እንደጀመሩ ሲገለጽ፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥም ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደሚያስገኙ አቶ ፍፁም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይህ ገቢ ሊገኝ እንደሚችል ሲገለጽ ቢቆይም፣ ከሠራተኞች ቅጥርና ሥልጠና እንዲሁም ከሌሎችም መሟላት ከሚጠበቅባቸው ግብዓቶች አኳያ ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ የሚጠበቀው የጨርቃ ጨርቅ የወጪ ንግድና የውጭ ምንዛሪ ገቢ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊሳካ እንደሚችል ከአቶ ፍፁም ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ የተገነቡትም ሆኑ ወደፊት የሚገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባዷቸውን ይቀራሉ፣ የሚገባባቸው ባለሀብትም ይታጣል የሚል ሥጋት መንግሥት እንደሌለውም አቶ ፍፁም ይጠቅሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም እየታየ ባለው የኢንዱስትሪዎች ፍልሰት (ግሎባል ሺፍት ወይም ሪሎኬሽን) ምክንያት በርካታ አምራቾች አዋጭ አገሮችን በማፈላለግ ላይ መሆናቸው ለኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ትልቅ አጋጣሚ ሆኖ ቀርቧል፡፡፡ ከዚህ አኳያ ከእስያ አገሮች ጋር ትንቅንቅ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ፍፁም፣ ኢትዮጵያ ካላት ዝቅተኛ የሰው ጉልበት ወጪና ከሌሎችም ድጋፎች አኳያ የእስያ ተቀናቃኞቿን መወዳደርና እንደ ቻይና ካሉ አገሮች በመሰደድ ላይ የሚገኙ ባለሀብቶችን መሳብ ከቻለች፣ የምትገነባቸው ፓርኮች ፆም እንደማያድሩ አቶ ፍፁም ያምናሉ፡፡ ይህም ቢባል መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከመገንባት ጎን ለጎን የውጭ ባለሀብቶችን አፈላልጎ ለማምጣት ስለሚሠራ ፓርኮች ባዶ ይቀራሉ የሚል ሥጋት እንደማያሳስብ ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች