Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ከልማዳዊና ጎታች አሠራሮች ይላቀቅ!

በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ በመንግሥት ቃል የተገባውን የአሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ የተለያዩ ክልሎችም የፌዴራል መንግሥት ከያዘው በጀት በተጨማሪ የራሳቸውን አክለው ለሥራ ፈጠራ መነሳታቸውን እያስታወቁ ነው፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እስከ ዘንድሮ መስከረም ወር ድረስ የዘለቀው ሁከትና ብጥብጥ ወጣቶች በመንግሥት ላይ የነበራቸውን ብሶትና ቂም በሚገባ ያሳየ ነው፡፡ መንግሥት ችግሮቹን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አማካይነት ካስታገሰ በኋላ፣ ፊቱን ወደ ወጣቶች  በማዞር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ መነሳቱን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ይህ መነሳሳት ግን ከልማዳዊ አሠራሮች ተላቆ ከወቅቱ የወጣቶች ፍላጎት ጋር ካልተጣጣመ ፋይዳ ቢስ ይሆናል፡፡ ፋይዳ ያለው ነገር አከናውኖ በእርግጥም ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተፈለገ መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮችን መጨበጥ ተገቢ ነው፡፡

የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የዚህ ዘመን ፓርቲ መሆን ካልቻለባቸው ተጠቃሽ ምክንያቶች መካከል፣ እስካሁን ለወጣቶች በቂ በሚባል ደረጃ ትኩረት አለመስጠቱ ነው፡፡ የኢሕአዴግ አመራር ትውልድ በወጣትነት ዘመኑ አገሪቱ ሌላው ዓለም የደረሰበት ደረጃ እንድትደርስ በማሰብ፣ በዘመኑ አዋጭ ነው ያለውን የፖለቲካ አማራጭ ተጠቅሞ የበኩሉን ሊወጣ ጥረት አድርጓል፡፡ የአሁኑ ዘመን ወጣት ደግሞ የተለመደው የፖለቲካ እንካ ሰላንቲያ ውስጥ ብቻ ራሱን ሳያጥር፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገሩን ከሠለጠኑት አገሮች ተርታ ለማሠለፍ ፍላጎት አለው፡፡ ይህ ራስን የመቻልና ከጥገኝነት የመላቀቅ፣ እንዲሁም ደግሞ በነፃነት የመሥራት ፍላጎት ደግሞ በትምህርትና በልዩ የክህሎት ሥልጠና እየዳበረ ሲሄድ፣ ወጣቱ ትውልድ አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች ይሆናል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ሞጋች ትውልድ ለማስተናገድ ደግሞ ከልማዳዊ አሠራሮች መላቀቅ የግድ ይላል፡፡

የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት ወጣቱን በሥራ ፈጠራ ለማገዝ ሲነሱ በመጀመሪያ መወገድ ያለበት የፖለቲካ ወገንተኝነት የሚባለው ነው፡፡ በሥራ ፈጠራ ዕድሉ ተጠቃሚ የሚሆኑ ወጣቶች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ መስኮች ሠልጥነው የወጡ እንደመሆናቸው መጠን፣ ኢፍትሐዊነት የሚባለው አደናቃፊ ድርጊት ያለ ምንም ማንገራገር መወገድ አለበት፡፡ በእከክልኝ ልከክልህ አጉል ግንኙነት የሚፈጸመው የሙስና ድርጊት የበለጠ ችግር ከመፍጠር ውጪ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ በሲቪል፣ በኤሌክትሪካል፣   በሜካኒካል፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምህንድስናዎችና በመሳሰሉት ሙያዎች የሠለጠኑ ወጣቶች ካፒታልና የሥራ ማስኬጃ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አግኝተው በነፃነት እንዲሠሩ ሲደረግ የምትጠቀመው አገር ናት፡፡ የተለመደው ኋላቀርና ልማዳዊ አሠራር ውስጥ ከተገባ ግን ትርፉ ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው፡፡ ይልቁንም ወጣቶች ውስጣቸው ያለውን ዕምቅ ክህሎት እንዲያወጡ ዕድሉን ማመቻቸት ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚህ በፊት አገሪቱን ችግር ውስጥ የከተቱ ሕገወጥ ተግባራት መቆም አለባቸው፡፡ ለማንም አይጠቅሙም፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በስፋት እንዲጠቀሙ ዕድሉን በማመቻቸት የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ማገዝ አለበት፡፡ በዓለም ዙሪያ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት አስገራሚ ችሎታቸውን በመጠቀም ሚሊየነር የሆኑ ወጣቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ትስስር በመፍጠር አስገራሚ የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ማከናወን የሚቻል ከሆነ፣ በተለይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በመሳሰሉት ሥልጠናዎች የተካኑ ወጣቶች እንዲጠቀሙ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያን የወጣቶች ክንፍ መመሥረቻ የማድረግ ዕቅድ ከመያዝ ይልቅ፣ ወጣቶቹ ዕድሉን አግኝተው ለአገር የሚጠቅም ሥራ ቢያከናውኑበት ይመረጣል፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ሼዶችን ከማዘጋጀት ባልተናነሰ ለማኅበራዊ ሚዲያም ትልቅ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ በአነስተኛና በጥቃቅን ተቋማት ላይ ብቻ የሚደረገው ርብርብ፣ የተሻለ ውጤት ሊያስገኙ በሚችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችም ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል፡፡

የነገዎቹ ቢል ጌትስና ማርክ ዙከርበርግ በብዛት ሊገኙ የሚችሉት፣ የሥራ ፈጠራው ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር እኩል መራመድ ሲችል ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሥርዓተ ትምህርቱና እየተሰጡ ያሉ ሥልጠናዎች በሚገባ መፈተሽ አለባቸው፡፡ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪና ውጤታማ የሚያደርግ የትምህርት ጥራት ሊኖር ይገባል፡፡ በኢንጂነሪንግና በቴክኒክ ሙያዎች የሚሰጠው ሥልጠና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን ማስቻል አለበት፡፡ በዚህ መንገድ የሚሠለጥኑ ወጣቶች ብድርና መጠነኛ ድጋፍ ሲደረግላቸውና በነፃነት የሚሠሩበት ዓውድ ሲፈጠር፣ ውጤቱ ከሚጠበቀው በላይ ይሆናል፡፡ የተለያዩ የቢዝነስ ሐሳቦችን ይዘው ሲቀርቡ የብድር ማስያዣ ከመጠየቅ ይልቅ፣ የፕሮፖዛሎቹን አዋጭነት ለማጥናት ባንኮችና የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጥረት ቢያደርጉ ከፍተኛ የሆነ ውጤት ይመዘገባል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዘመናዊ አሠራር ተግባራዊ ሲሆን በሥራ ዕድል ፈጠራዎች ላይ የሚታዩት ኋላቀርና ልማዳዊ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ ብልሹ ተግባራት የኋላቀርነት መገለጫ ይሆናሉ፡፡ የአገሪቱ ወጣቶች ክህሎታቸውን የሚያሳዩበት ዕድል ይመቻች፡፡

በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ለሥራ ፈጠራ ዕድሎች አስተዋጽኦ ያደረጉ ግለሰቦች ወጣቶች ተዓምር እንዲሠሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በናይጄሪያ 100 ሚሊዮን ዶላር ለአሥር ዓመታት ተዘዋዋሪ ፈንድ የመደቡ ኢንቨስተር ውጤታማ ወጣቶችን በማፍራት ታላቅ ስም አትርፈዋል፡፡ ከፌዴራል መንግሥት አሥር ቢሊዮን ብር በተጨማሪ ክልሎችም ከራሳቸው በጀት በማከል ለሥራ ፈጠራ ዕድሎች መነሳታቸው መልካም ዜና ነው፡፡ ውጤቱ ግን የሚሰምረው ዘመናዊ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በልማዳዊ አሠራሮች የተጠፈነገ ከሆነ ግን አይጠቅምም፡፡ ግልጽነትና ኃላፊነት የጎደላቸው ብልሹ አሠራሮችና ደካማ መንግሥታዊ መዋቅሮችን ይዞ ግዙፍ ፈንድ ለማስተዳደር መሞከር አደገኛ ነው፡፡ እንደተለመደው በበቂ ሁኔታ ያልተዘጋጀ ዕቅድ ይዞ የዘመቻ ዓይነት ሥራ ውስጥ መግባት የሌቦች ሲሳይ መሆን ነው፡፡ ብቃት የሌላቸው፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው፣ ኢፍትሐዊነት የተጠናወታቸው፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት አስተሳሰብ ያልተላቀቁ፣ አጋጣሚዎችን ለራሳቸውና ለቡድን ዓላማቸው ብቻ መጠቀም የሚፈልጉ ራስ ወዳዶች ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓት ካልተፈጠረ ጥረቱን ውኃ ይበላዋል፡፡ ነገር ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ወጣቶች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙ ከተፈለገ ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኋላቀርና ጎታች ልማዳዊ አሠራሮች በፍጥነት ይወገዱ!

 

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...