Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

‹‹አትርሱት አንርሳው …››

ትኩስ ፅሁፎች

ራስን ካንገት ላይ ቆራርጦ እየጣለ

በችንካር ቸንክሮ ሰው እየገደለ

ሰውን ከነቤቱ አብሮ እያቃጠለ

ማነው እንደ ፋሺስት በሰው ግፍ የዋለ?

ሥጋችንን ገድለው ሊቀብሩት ከጀሉ

በዚህ ያልነበሩ ሐሰት እንዳይሉ

እሊህ አስክሬኖች ይመሰክራሉ፡፡

ይህን ታላቅ ስቃይ መከራና ግፍ

ሲያስታውስ ይኖራል የታሪክ መጽሐፍ

አትርሱት አንርሳው ያስታውሰው ዘራችን

ኢጣሊያ መሆኗን መርዛም ጠላታችን፡፡

እላንት አእጽምቶች ዕድለኞች ናችሁ

በኃይለ ሥላሴ ትንሣኤ አገኛችሁ፡፡

ይህ የወል ቤት ግጥም፣ ከ80 ዓመት በፊት በፋሺስት ኢጣሊያ ጭፍራ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ አማካይነት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. አንስቶ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ፣ ሰማዕት ለሆኑት 30 ሺሕ ኢትዮጵያውያን በቆመው ሐውልት ግርጌ የሰፈረ ነው፡፡

የሰማዕታቱ አፅሞች ማረፊያ ሐውልት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰሜናዊ አቅጣጫ ላይ የታነፀው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አማካይነት በ1934 ዓ.ም. ነበር፡፡

(ሔኖክ መደብር)

***

የካቲት 12 ቀን እና ‹‹ጥቁር ሸሚዝ››

የኢጣሊያ ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ነው፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት፡፡

‹‹ጥቁር ሸሚዝ›› እየተባሉ የሚታወቁት የፋሽስት ደቀመዛሙርት መንግሥት አይዟችሁ እያላቸው አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፡፡ ቤቶች ከነነዋሪዎቻቸው ጋዩ፡፡ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፡፡ የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ፡፡ ይህ የምሁራን ጭፍጭፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፉ በመሆኑም ባገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ  የማይሽር ቁስል ጥሎ አለፈ፡፡

  • ባሕሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966›› (1989)

* * * * * * *

ድመት እና ጺሟ

ድመቶች አብዛኛውን ጊዜ በጨለማ ንቁ ናቸው። ከጨለመ በኋላ በአቅራቢያቸው ያሉ ነገሮችን ለይተው ለማወቅና አድነው የሚበሉትን እንስሳ ለመያዝ የሚረዷቸው ጺሞቻቸው እንደሆኑ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

የድመት ጺሞች የሚበቅሉት ብዙ የነርቭ ጫፎች ባሏቸው ሕብረ ሕዋሳት ላይ ነው። እነዚህ ነርቮች በአየሩ ላይ የሚፈጠረው በጣም ትንሽ እንቅስቃሴ እንኳ ይሰማቸዋል። በዚህም የተነሳ ድመቶች በአቅራቢያቸው ያሉ ነገሮችን ባያዩአቸውም እንኳ መኖራቸውን ማወቅ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ በጨለማ እንደሚጠቅማቸው ግልጽ ነው።

የድመት ጺሞች ትንሹም እንቅስቃሴ ቶሎ የሚሰማቸው መሆኑ አንድ ነገር ወይም አድነው የሚበሉት አንድ እንስሳ ያለበትን ቦታና የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለይተው እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም ድመቶች በአንድ ክፍተት በኩል ለማለፍ ሲሞክሩ ጺሞቻቸው የክፍተቱን ስፋት ለመለካት ይረዷቸዋል።

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደገለጸው ከሆነ፣ የድመት ጺም ያለውን ጥቅም በተመለከተ ማወቅ የተቻለው ከፊሉን ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ድመቱ ጺሙ ከተቆረጠበት ለጊዜውም ቢሆን እክል እንደሚገጥመው ታውቋል።

የሳይንስ ሊቃውንት፣ የድመት ጺሞችን ንድፍ በመኮረጅ በእንቅፋቶች መሃል እየተሹለከለኩ ለመሄድ የሚያስችሉ ጠቋሚ መሣሪያዎች ያሏቸው ሮቦቶች ለመሥራት ጥረት እያደረጉ ነው። ኢዊስከርስ ተብለው የተጠሩት እነዚህ ጠቋሚ መሣሪያዎች ‹‹ለተራቀቀ የሮቦት ቴክኖሎጂ፣ የተለያዩ መሣሪያዎችን ለአጠቃቀም ምቹ ለማድረግ እንዲሁም በባዮሎጂ መስክ የተለያየ አገልግሎት›› እንደሚኖራቸው በካሊፎርኒያ የሚገኘው የበርክሊ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሊቅ የሆኑት አሊ ጃቪ ተናግረዋል።

  • (ጄ ደብሊው ዶት ኦርግ)

**********

አንድ ሳያሳጣ

ታሪኩ ወደ ፓሪስ ይወስደናል፡፡ ካመታት በፊት በአንድ ቤተ ኦፔራ ውስጥ የተከሰተ ነው፡፡ አንድ ዝነኛ ዘፋኝ የሙዚቃ ኮንሰርት ሊያቀርብ ተጋብዞ አድናቂዎቹ ትኬታቸውን ገዝተው የኮንሰርቱን ቀን ይጠባበቃሉ፡፡

በኮንሰርቱ ምሽት አዳራሹ እስከገደፉ በሰው ተጨናነቀ፡፡ የኮንሰርት አቅራቢው ሰው ተጠበቀ፡፡ ፕሮግራሙን ያዘጋጀው ሰው በድንገት ወደ መድረኩ ብቅ አለና፣

‹‹ክቡራትና ክቡራን ታዳሚዎቻችን ስለ ጋለው ትብብራችሁ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡ አንድ አሳዛኝ ዜና ደርሶኛል፡፡ ጊዜአችሁን ሰውነታችሁ በዚህ ምሽት በናፍቆት የጠበቃችሁት ዝነኛው እገሌ በድንገት ታሞ ስለቀረ ኮንሰርቱን ልናቀርብ አልቻልንም፤ ይሁን እንጂ በእርሱ ምትክ ከጋበዝነው ሌላ ሰው ጋር ባልተናነሰ መልኩ ጥሩ የመዝናናት ጊዜ እንደምታሳልፉ ተስፋ እናደርጋለን›› አለ፡፡

ታዳሚው አጉረመረመ፡፡ የተተኪውን ሰው ማንነት እንኳ ለመስማት ትዕግስት አልነበረውም፡፡ የአዳራሹ ድባብ ከጋለ ድምቀት ወዲያው ጨፈገገ፡፡ የተተካው ሰው ዝግጅቱን አቀረበ፡፡ እንደ ጨረሰ፣ አዳራሹ በፀጥታ ተዋጠ፤ ከአንድም ታዳሚ ጭብጨባ አልተቸረውም፡፡

ይህን ጊዜ በድንገት ካዳራሹ ሠገነት ላይ አንድ ትንሽ ልጅ ብድግ ብሎ ‹‹ባቢ፣ አደንቅሃለሁ! ለእኔ ድንቅ ነህ! የሚል የአድናቆት ጩኸት አሰማ፡፡ አዳራሹ እንደገና ነቃ፤ ከዳር እስከ ዳር ታላቅ ጭብጨባ አስተጋባ፡፡

ሁላችንም በሕይወታችን አንዳንድ ጊዜ ብድግ ብሎልን፤ ‹‹አደንቅሃለሁ! ለእኔ ድንቅ ነህ! የሚለን ሰው አያስፈልገን ይሆን?

  • ኃይል ከበደ ‹‹ጉርሻ እና ፌሽታ›› (2006)   
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች