Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ተሳታፊዎች ቁጥር ቀነሰ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ቱርክና ግብፅ ኩባንያዎቻቸውን መላክ አልቻሉም

በኢትዮጵያ በቋሚነት ከሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶች መካከል በርካታ የውጭ ኩባንያዎችን በማሳተፍ የሚታወቀው የአዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ዓውደ ርዕይ፣ በዘንድሮ ዝግጅቱ በተለይ የውጭ ኩባንያዎች ተሳታፎ እንደቀነሰበት ተገለጸ፡፡ በርካታ ኩባንያዎችን ሲያሳትፉ የቆዩት ቱርክና ግብፅ በ21ኛው የንግድ ትርዒት እንዲሳተፉ ሲጠበቁ የነበሩ ኩባንዎቻቸውን መላክ እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡

ንግድ ትርዒቱን በባለቤትነት ከሚያስተዳድረውና ከሚያዘጋጀው ከአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ሐሙስ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ተከፍቶ ለሰባት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ በተገለጸው 21ኛው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ወቅት 180 ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ 100 ያህሉ ከ27 አገሮች የተውጣጡ የውጭ ኩባንያዎች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ቀሪዎቹ 80 ኩባንያዎች በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

ሆኖም ‹‹የተመቻቸ ሁኔታ ለተቀላጠፈ የውጭ ንግድ ሥራ›› በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የዘንድሮው የንግድ ትርዒት ላይ ይሳተፋሉ የተባሉት የኩባንያዎች ቁጥር ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ እንደ ምክር ቤቱ መረጃ ከሆነ፣ ዓምና በተካሄደው የንግድ ትርዒት ላይ 202 ኩባንያዎች፣ በካቻምናው ደግሞ 218 ኩባንያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ዘንድሮ የሚሳተፉት ኩባንያዎች ብዛት 180 በመሆኑ ከካቻምናው 38፤ ከዓምናው ደግሞ 22 ኩባንያዎች ቀንሰዋል፡፡ በተለይ የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ ከአገር ውስጥ ይልቅ ብልጫ ቢያሳይም፣ በ2008 ዓ.ም. ተሳታፊ ከነበሩት 131 የውጭ ኩባንያዎች አንፃር ሲታይ፣ የዘንድሮው ተሳታፊዎች ቁጥር በ30 እንደቀነሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከካቻምናዎቹ አኳያ የተሳታፊዎቹ ቁጥር በ63 ቀንሷል፡፡ በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው የንግድ ትርዒት ወቅት ተሳታፊ የነበሩት የውጭ ኩባንያዎች ብዛት 163 እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኩባንያዎች ቁጥር ለምን እንደቀነሰ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ፣ ‹‹በዘንድሮው የንግድ ትርዒት ላይ የተሳታፊዎች ቁጥር ለማነሱ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ከዚህ ቀደም በተከታታይ ይሳተፉ የነበሩ የግብፅና የቱርክ ኩባንያዎች መሳተፍ ባለመቻላቸው ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከሁለቱ አገሮች የሚመጡ ኩባንያዎች አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች አገሮች ተሳታፊዎች ይልቅ ብልጫ እንደነበራቸው ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፣ ዘንድሮ መሳተፍ ባለመቻላቸው የተሳታፊዎች ቁጥር እንዲቀንስ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል፡፡

 አቶ ጌታቸው እንደሚሉት፣  በየዓመቱ በንግድ ትርዒቱ ላይ ለመሳተፍ  በርከት ያሉ ኩባንያዎች ከቱርክ ይመጡ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ከ30 እስከ 40 ያህል የቱርክ ኩባንያዎች ከአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል አዳራሾች አንዱን ለብቻቸው በመከራየት ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ ዘንድሮ ግን ኩባንያዎቹን አሰባስቦ ያመጣ የነበረው የንግድ ምክር ቤቱ ወኪል ኩባንያ በቱርክ ከተከሰተው ፖለቲካዊ ችግር ጋር በተያያዘ ኩባንያዎቹን እንዲመጡ ማድረግ እንዳልቻለ ማስታወቁን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡   

በንግድ ትርዒቱ እንዲሳተፉ በርካታ ኩባንያዎችን በመላክ የምትታወቀው ግብፅም ዘንድሮው እንደማትሳተፍ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከ25 ያላነሱ የግብፅ ኩባንያዎች ሰፊ ቦታ ይዘው ምርትና አገልግሎታቸውን ያስተዋውቁ እንደነበርም ተገልጿል፡፡ በዘንድሮ ዝግጅት ላይ ግን በተናጠል የመጡ አምስት የግብፅ ኩባንያዎች ብቻ ተገኝተዋል ተብሏል፡፡ 21ኛውን የአዲስ አበባ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት፣ የንግድ ሚኒስትሩ ዶ/ር በቀለ ቡላዶ እንደሚከፍቱት ንግድ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች