Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአማራ ንግድ ምክር ቤት ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ ተሻረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ እንዳይካሄድ እንደ አንድ ምክንያት ሲጠቀስ የቆየውና መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ተካሄዶ የነበረው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ተሽሮ፣ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲደገምና አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡

የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አካሂዶት የነበረውን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ እንዲሻርና እንዲደገም የወሰነው የአማራ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቢሮው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫውን የተመለከቱ አቤቱታዎችን ከመረመረ በኋላ መሆኑን ከቢሮው ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡ በቅርቡም ንግድ ሚኒስቴር የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የምርጫ ሒደት ሕጋዊ መንገድን የተከተለ አልነበረም በሚል በቀረቡለት ተደጋጋሚ አቤቱታዎች፣ የምርጫ ሒደቱ እንዲጣራ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ ቢሮው ከዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የተደረገውን የምርጫ ሒደትና አጠቃላይ ክንውኑን በተመለከተ በዕለቱ ተመርጠው የነበሩ አመራሮች፣ ሒደቱ ምንም ዓይነት ችግር ያልነበረበት መሆኑን እንዳስረዱት ይገልጻል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎች ባስገቧቸው አምስት የሚሆኑ ነጥቦች ላይ ባካሄደው ማጣራት፣ በአራቱ ላይ ምንም ችግር አለማግኘቱን፣ በአንዱ ላይ ግን የሕግ ጥሰት ማግኘቱን በማስታወቅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ቢሮው ውሳኔ ከሰጠባቸው አምስት ነጥቦች መካከል አንዱ ‹‹ጠቅላላ ጉባዔው ምልዕተ ጉባዔ ሳይሟላ የተካሄደ ነው፤›› የተባለው ቅሬታ ይጠቀሳል፡፡ የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ምክር ቤት ኃላፊ በተገኙበት ምልዓት ጉባዔው መሟላቱ ተረጋግጦ ወደ ሪፖርት ማቅረብ የተገባ በመሆኑ፣ ይህ ቅሬታ አግባብነት የሌለው ነው ተብሏል፡፡ ‹‹ፕሬዚዳንቱ ለ12 ተከታታይ ዓመታት ሥልጣን ይዟል፤›› የተባለው ቅሬታ፣ በአዋጅ ቁጥር 341/95 አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 3 እና በምክር ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብ የቦርድ አባላት የሥልጣን ዘመን ሁለት ዓመት ስለመሆኑ እንጂ አንድ ሰው ለስንት ጊዜ ብቻ መመረጥ እንደሚችል በግልፅ ስለማያመላክት፣ ቅሬታው ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ቢሮው የጻፈው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

‹‹የዳይሬክተሮች የቦርድ አባላት አላግባብ እርስ በርሳቸው ተሸላልመዋል፤›› በተባለው ቅሬታ ላይ፣ የሥራ አመራር ቦርዱ ላለፉት ዓመታት ያገለገሉ የዳይሬክተሮች የቦርድ አባላትን እንዳይሸልም የሚከለክል ሕግ የሌለ በመሆኑ ቢሮው ቅሬታውን አለመቀበሉን ገልጿል፡፡ ነገር ግን በሽልማቱ ዙሪያ የዳይሬክተሮች የቦርድ አባላት ተሰናባች የቦርድ አባላትን ብቻ ቢሸልም ጥሩ ስለሚሆን፣ ቦርዱ የራሱን ውሳኔ እንዲወስን አስተያየት በመስጠት በሽልማቱ ላይ ለቀረበው ቅሬታ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

‹‹ምርጫው አስቀድሞ በተደራጀ ኔትወርክ በአደረጃጀት የተፈጸመው ነው፤›› የተባለውም ቅሬታ ላይ ቢሮው ባደረገው ማጣራት፣ ከቅድመ ምርጫ በፊትም ሆነ በምርጫ ወቅት እንዲሁም በድኅረ ምርጫ በአደረጃጀትና በኔትወርክ የተፈጸመ ምርጫ ስለመሆኑ ተጨባጭ ማስረጃ እንዳላገኘበት አስታውቋል፡፡

አምስተኛ ነጥብ ሆኖ ቢሮው የተመለከተውና ብዙ ሲያጨቃጭቅ የነበረው ‹‹የታችኛው ምክር ቤት ውክልና ሳይኖራቸው ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ነባር የቦርድ አባላት እንዲመረጡ ተደርጓል፤›› የሚለው ቅሬታ ላይ ግን፣ የቢሮው የሕግ ጥሰት የታየበት ሆኖ አግኝቶታል፡፡ የሕግ ባለሙያዎችና የርዕሰ መስተዳድሩ የሕግ አማካሪ ከሕግ አኳያ አስተያየት የተሰጠበት መሆኑን የሚያመለክተው የውሳኔ ደብዳቤ፣ በቢሮው በተጠየቀው መሠረት የባለሙያዎች አስተያየት ከሰጡበት በኋላ የዚህ ቅሬታ ጭብጥ የሕግ ጥሰት ያለበት ስለመሆኑ ያሳየ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በባለሙያዎቹ አስተያየት መሠረት ‹‹የአንድን ክልል የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሊያቋቁሙ የሚችሉት በዚያው ክልል ውስጥ አስቀድመው የተቋቋሙ የከተማ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችና የክልል ወይም የወረዳ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ስለመሆናቸው በአዋጅ ቁጥር 341/1995 አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ 1 ሥር በግልጽ ተደንግጓል፡፡››

በዚህ ዓይነት የሚቋቋመው የክልል አቀፍ ምክር ቤት መሥራች ጉባዔም ከአባላቱ መካከል ፕሬዚዳንቱንና ምክትል ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ከአሥራ አንድ የማይበልጡ ተወካዮችን በቦርድ አባልነት መርጦ እንደሚሰይም በአዋጁ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 1 እና አንቀጽ 17 መጠቀሱንም ያስታውሳል፡፡

በአንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 1 ሥር ‹‹ተወካዮች›› የሚለው ኃይለ ቃል ጉባዔተኛዎቹ በክልል አቀፍ ምክር ቤት ስብሰባ ለመሳተፍ፣ ለመምረጥ፣ ለመመረጥ የታችኞቹን የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን ይሁንታ ማግኘት እንዳለባቸው አመላካች ሆኖ መገኘቱን በመግለጽ ውሳኔውን ሊሰጥ ችሏል፡፡

ከዚህ ውጭ በተሰናባቹ ምክር ቤት አማካይነት ለነባር የቦርድ አባላት ተሰጥቶ ነበር የተባለው ‹‹ልዩ ውክልና›› አዋጁ ለታችኞቹ ምክር ቤቶች የሰጠውን በየራሳቸው እንደራሴ የመወከል መብት ጋር የሚጣረስ ነው ብሎታል፡፡ በታችኞቹ ምክር ቤቶች ያልተወከለ ሰው በክልል ምክር ቤት ጉባዔ ተወካይ ሊሆን ስለማይችል፣ የመሳተፍም ሆነ ድምፅ የመስጠት መብት እንደማይኖረው የባለሙያዎች ማብራሪያ እንደሚያስረዳ በቢሮው ምክትል ኃላፊ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤው ጠቅሷል፡፡

ከዚህ በመነሳትም የአማራ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ከቀረቡ አምስት ቅሬታዎች መካከል በአራቱ ላይ ችግር ያላገኘ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ሆኖም በአምስተኛውና በመጨረሻው ቅሬታ ከሕግ ባለሙያዎች ሙያዊ መብራሪያ አኳያ ከአዋጅ ቁጥር 341/95 ድንጋጌ ጋር የሚጋጭ አሠራር አግኝቼበታለሁ ብሏል፡፡ ስለሆነም መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደውን የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የጠቅላላ ጉባዔ ምርጫ ሕጋዊ ባለመሆኑ እንዳልተቀበለው አረጋግጦ፣ ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫውን የሚያግድ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫው ሕጋዊ ባለመሆኑ ቢሮው ደብዳቤ ከተጻፈበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አስቸኳይ ጉባዔ እንዲጣራም አሳስቧል፡፡ አያይዞም በሕጉ መሠረት ፕሬዚዳንቱንና ምክትል ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫ እንዲካሄድ በጥብቅ ያሳሰበው የቢሮ ደብዳቤ፣ በግልባጭ ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች አሳውቋል፡፡ ቢሮው ይህንን ውሳኔ ቢወስንም በአንድ ወር ይጠራ የተባለውን ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ ማን ያስፈጽመው የሚለውን አለመጥቀሱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ከቢሮው ውሳኔ በኋላ አንዳንድ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት እንደገለጹት፣ ምርጫውን ማን ያስፈጽመው የሚለው ጥያቄ ምላሽ ካልተሰጠው አሁንም አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በተለይ ምርጫው ይደገም ከተባለ አመራሮቹም ታግደዋል ማለት ነውና ይህ በግልጽ መገለጽ እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

እንደ አማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሁሉ ሕግን ተከትለው ምርጫ አላደረጉም እንዲሁም አመራሮቻቸው ከመተዳደሪያ ደንባቸው ውጪ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ ተመርጠዋል የሚል አቤቱታ የቀረበባቸው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና የአገር አቀፍ ዘርፍ ምክር ቤት ጉዳይም በሚመለከታቸው የመንግሥት ቢሮዎች ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል፡፡

ሕግን ተከትለው ምርጫ ማድረግ አለማድረጋቸውን እንዲሁም ከሕገ ደንባቸው ውጪ ተመርጠዋል የተባሉ አመራሮች፣ ውክልናቸው ትክክል መሆኑ አለመሆኑን እንዲያረጋግጡለት የዘርፍ ምክር ቤቱን በተመለከተ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ማብራሪያ ጠይቋል፡፡ ከዚህም ሌላ የዘርፍ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ውክልናንም በተመለከተ የትግራይ ክልል ንግድ ቢሮ ማብራሪያ ተጠይቆ ምላሽ እየተጠበቀበት ነው፡፡ በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጠው በደብዳቤ ጭምር ጠይቋል፡፡

በተለይ ከመተዳደሪያ ደንብ ውጪ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል በሚል ጥያቄ ከተነሳባቸው መካከል የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው አየነውና የአገር አቀፍ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ገብረሕይወት ገብረእግዚአብሔር ይገኙባቸዋል፡፡ ሁለቱም ከአሥር ዓመታት በላይ ቦታውን ይዘው የቆዩ እንደሆኑ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ምርጫ ፍትሐዊ አልነበረም የሚለው ትችት ከአባል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጭምር ሲቀርብ የነበረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትም አማራን ጨምሮ ከአንዳንድ አባል ምክር ቤቶች ያካሄዱት የምርጫ ሒደት ሕጋዊ አይደለም በሚል አጣሪ ኮሚቴ እስከማቋቋም መድረሱ ይታወሳል፡፡ አጣሪ ኮሚቴውም ሕግን ያልተከተሉ አባል ምክር ቤቶች ሕግ ከጣሱ ዕርምጃ ይወሰድ በሚል ውሳኔ አስተላልፎ ጠቅላላ ጉባዔውም ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቢወስንም፣ የመጨረሻ ውሳኔ ባለመሰጠቱ ችግሩን በራሱ መንገድ ለማጣራት ንግድ ሚኒስቴር ጠቅላላ ጉባዔውን እንዳገደው ይታወሳል፡፡

የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከተቋቋመበት ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም. ድረስ ስድስት ጠቅላላ ጉባዔዎችን እንዳካሄደ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች