Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 31 ሲፈተሽ

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 31 ሲፈተሽ

ቀን:

 በዘለቀ ገብረሐና

1.መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥልጣን የመያዝ ጉዳይ

ይህ  ነጥብ  በዓለም  ታሪክ  ውስጥ  ለጦርነቶች  መንስዔ፣ ለሰው ልጆች  የጅምላ  ጭፍጨፋ፣ የዘር ማጥፋት  ተግባሮች፣ ለስደት፣ ለረሃብና ለእርዛት  በማጋለጥ በድምሩ  ለሰው ልጆች  እልቂትና  ንብረት መዉደም ዋናው ምክንያት ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ለወደፊቱም በቀላሉ የሚቀር ጉዳይ አይሆንም፡፡

- Advertisement -

1.1.መንግሥታዊ  የፖለቲካ  ሥልጣን  የመያዝ  አካሄድ  በኢትዮጵያ

ረጅም ዘመናትን ወደኋላ  ብንቆጥር መንግሥታዊ  የፖለቲካ ሥልጣን  ለመያዝ  በኢትዮጵያ  ሲደረጉ  የነበሩ  ሁኔታዎችን  በአጭሩ  ስናስቀምጥ፣

          -በዘር ሐረግ (በንጉሣዊ  ዘር)

          -በኃይል (በጦርነት) ነበር፡፡

መንግሥታዊ  የፖለቲካ ሥልጣንን  ለሕዝቦች  ተጠቃሚነት (ዴሞክራሲያዊ) ለማድረግ የፖለቲካ  ትግል ለማካሄድ  ለሚነሱ ዜጎች ወቅቶቹ  ምቹ ስላልነበሩ፣ ዜጎች ለትግላችን ያመቸናል ያሉዋቸውን አማራጮች ማለትም  በአካባቢ ስም፣ በብሔር ስም፣  ወዘተ በመደራጀት ረጅምና እልህ አስጨራሽ ትግሎችን አካሂደዋል፡፡ በዚህም  ምክንያት  አገራችን ቁጥር ሥፍር የሌላቸውን የውድ ዜጎቿን ሕይወት መስዋዕትነት  ከፍላለች፡፡ ዳሩ ግን  የታሰበውን  ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት  በኢትዮጵያ ማስጀመር ተችሏል፡፡

     የትግሎቹ ዋና ዋና ዓላማ  ከሚባሉት ውስጥ የአርሶ አደሩ የመሬት ይዞታ ጥያቄ በአስተማማኝ ሁኔታ መፍትሔ አግኝቷል፡፡

       የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጉዳይም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ላይ በተሟላ ሁኔታ በመቀመጡ ጠቃሚ ውጤት ተገኝቶበታል፡፡ ምንም እንኳ ከጅምሩ እስካሁን ድረስ ተቃውሞ ባይለየውም፡፡ ይኼ አንቀጽ የብዙዎች ሥጋት እንደነበረው ለመበታተንም አላጋለጠንም፡፡ 

1.2  ከ1983 ዓ.ም  ወዲህ  ያለው  መንግሥታዊ  የፖለቲካ  ሥልጣን  አያያዝ

በተከፈሉት መስዋዕትነቶች  ዴሞክራሲያዊ  የሆነ  ሕገ መንግሥት  በኢትዮጵያ  ሲፀድቅ፣  ይኼን  መንግሥታዊ  የፖለቲካ  ሥልጣን  መያዝ የሚቻለው  በሕዝቦች ፈቃድ  በምርጫ  ውጤት መሠረት ብቻ  መሆኑ  ሲቀመጥ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች  መደራጀትም  በሕገ መንግሥቱ  በአንቀጽ 31 ላይ  እንዲህ  በማለት  ተደንግጓል

  ’’ማንኛውም ሰው ለማንኛዉም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው ሆኖም አግባብ ያለውን ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሠረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ  ድርጅቶች  የተከለከሉ  ይሆናሉ፤’’ ይላል፡፡

እንግዲህ ለዚህች አገር የመበታተን አደጋ ዋና መንስዔ ሊሆን የሚችለው አንቀጽ 39 ሳይሆን ይህ አንቀጽ 31 ሊሆን እንደሚችል፣ ቀጥሎ የተመለከቱትን ዝርዝር ሁኔታዎችን መመልከት በቂ ይሆናል፡፡

 

                                                                                                         

እንግዲህ ይህን አንቀጽ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ከማናቸውም ነጥቦች በላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊብራራ፣ መብትና ገደቦች  ሊቀመጡለት፣  ወይም አሟልተን  በማስቀመጥ  የአገራችንን  የወደፊት  የእልፍ ዘመናት የህልውና ማረጋገጫ ዋስትና  ማድረግ  ሲገባን፣  ዝም ተብሎ  ገደብየለሽ  መብት በመሰጠቱ  ወይም ክፍት  እንዲሆን  በመደረጉ  የችግሮቻችን ዋና መሠረት ሆኗል፡፡

 ገደብ አያስፈልግም የሚል ድምዳሜ ግን ግርድፍ አባባል ወይም ማስተዋል የጎደለው አመለካከት ከመሆን አያልፍም፡፡ ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲባል  ገደብ የለሽ ሥርዓት ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለሁሉም ነገር ልክ፣ መጠን፣ ገደብ፣ ሥርዓት አለው ወይም ሊኖረው ይገባል፡፡ የረጅም ዘመናት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤቶችም ቢሆኑ ሕገ መንግሥታቸውና ሌሎችም ሕጎቻቸው ልክና ገደብ አላቸው፡፡ የአገራችንም ሕገ መንግሥት አብዛኛዎቹ አንቀጾቹ ላይ፣ እንዲሁም ሌሎችም ሕጎቻችን ልክና ገደብ እንዲሁም ግዴታዎች አሉዋቸው፡፡

 ይህ አንቀጽ ግን ድፍን ተደርጎ  ያለገደብ መቀመጡ ሲታይ መቼም ሕዝባችን ሕግና ሥርዓትን እስካልጣሰ ድረስ በፈለገው ሁኔታ ይደራጅ ከሚል ቀና አመለካከት የመነጨ ወይም ገደብ ካስቀመጥን በሌሎች ዘንድ በመጥፎ ሁኔታ እንታያለን ከሚል ሥጋት የመነጨና እንዲሁ ለታይታ ወይም ለስም ብለን ያደረግነው ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳቱ አስተያየት ለሚሰጡን ሳይሆን ለእኛው ነው የዓለም አቀፉን በጎ በጎ ነገሮችን ተቀብለን በጋራ በሚያራምዱ ጉዳዮች አብረን መጓዝ  ብዙ ጥቅሞች  እንዳሉት ይታወቃል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በራሳችን መንገድ መጓዝ በብዙ መልኩ የጠቀመን ስለመሆኑ ብዙ ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ምንም ተባለ ምን አገራችንን የሚጠቅም ነገር መምረጥ የእኛ ኃላፊነት ይሆናል (በመገደብም ይሁን ነፃ በመልቀቅ)፡፡

ይህን ካላደረግን ለችግሮቻችን ሁሉ መሠረታዊ መፍትሔ የምናገኝበትን ጉዳይ አንፈልግም ብለን እንደወሰንን ልናውቅ ይገባል፡፡ እንኳን 60 እና 70 የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀርቶ ለምን ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በየመንደሩ አይደራጁም? የእነሱን የመደራጀት መብት ሊነካ አይገባም፡፡ ውጤት ማምጣት እንደማይችሉ ብናውቅም ይህ መብታቸው ብቻ መከበሩ ይበቃናል ካልን ስለተለዋጭ የአገር የፖለቲካ አመራር፣ ስለሙስና መንሰራፋት፣ ስለመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ወዘተ ችግሮች ማውራት መፍትሔ የለውም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብትና ተጠቃሚነትን ቁጥር ሥፍር በሌላቸዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመቋቋም መብት ለውጠናልና፡፡

 2. የሕገ መንግሥታችን  አንቀጽ 31  ክፍት  በመደረጉ  ያጋጠሙ  ችግሮች

በመሠረቱ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ራሱን  ይወዳል፡፡ ይህን ባሕሪውን  ከግምት ውስጥ ሳናስገባ አንቀጹን ክፍት በመተዋችን በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ  የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድነትም ይሁን በተናጠል ከዚሁ የሰዎች ባሕሪ በመነጨ ሁኔታ ወጥነት ያለው አቋምና ጥንካሬ ይዘው መቀጠል የሚችሉበትን ዕድል  አሳጥቷቸዋል፡፡ የተጠናከረ አቋም ወይም አንድነት ኖሮአቸው ለዚህች አገር ጠቃሚ ነገር ለመሥራት ይበቃሉ ተብለውም ሊጠበቁ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እስከ ዛሬ በተጨባጭ  ያየነው እውነታ ስለሚመሰክር፡፡

 እስካሁን ባለው ሁኔታ ማናችንም የምንረዳው ነገር አለ (ከአዲሱ ሕገ መንግሥት  በኋላ ማለት  ነው) አብዛኛዎቹ  የፖለቲካ ፓርቲዎች   ለግል  ጥቅምና ዝና ፍለጋ  በተነሱ  ሰዎች  ሲቋቋሙ  እንደነበር  ከድርጊታቸዉ አይተናል፡፡ ነገር ግን  ምንም የገንዘብና ዝና ፍላጎት የሌላቸው አገራቸውን በእውቀታቸዉና በጉልበታቸው  ለማገልገል የተነሱ ዜጎች ነበሩ፡፡ አሁንም አሉ፡፡ ለወደፊቱም ይኖራሉ፡፡ ይሁን እንጂ  እነዚህ ጠቃሚ ዜጎች ትግሉን ብቻቸውን ከዳር ማድረስ ስለማይችሉ ከሌሎች ጋር አብሮ ለመሥራት ሁኔታው ግድ ስለሚላቸው ይህን ይፈጽማሉ፡፡ በሒደትም ዓላማቸውን በሚመለከት፣ ስላሉበት ሁኔታ፣ የወደፊት አቅጣጫ፣ ስለተፈጠሩ ስህተቶችና ምክንያቶቻቸው፣ እንዲሁም  መፍትሔዎቻቸውን  በማስመልከት  በሚደረግ ውይይትና  እንቅስቃሴ ውስጥ በሁሉም አባላት ዘንድ አንድ ዓይነት አቋም ላይኖር ይችላል፡፡ 

በመሆኑም  በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መተጋገል ይፈጠራል፣ ተጠያቂነትም ይመጣል፡፡ ነገር ግን ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የሚያግዝ በሕገ መንግሥቱ ወይም በሌሎች ሕጎች የተቀመጠ ጥብቅ ነገር ባለመኖሩ ምንም አቅም በሌለው የፖለቲካ ፓርቲው ደንብና መመርያ ላይ መመሥረት ግድ ይሆንባቸዋል፡፡  በዚህ ምክንያት  ቀድሞውኑ ለግል ጥቅምና ዝና ፍለጋ ብሎ የገባው አካል ተጠያቂነት ሲመጣበት ወይም ጥቅሙን የሚነካ ነገር ሲፈጠር አባላቱን በመበጥበጥ፣ በሌሎች ላይ መግለጫ በመስጠትና ሌሎች አላስፈላጊ ነገሮችን በመፈጸም ፓርቲውን ጥሎ እስከ መውጣት ይደርሳል፡፡ ወጥቶም አርፎ መቀመጥ የለም፡፡ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ወደ ማቋቋም ያመራል፡፡ ታዲያ ይህ ሁልጊዜ የምናየውና የማይቆም ጉዳይ ነዉ፡፡ ለዚህ ችግር ዋናው ምክንያት ደግሞ አንቀጹ ክፍት መደረጉ ነው፡፡

ኢሕአዴግም ቢሆን ሥልጣን ላይ በመሆኑ እንጂ በዚህ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ልክ እንደ ጫካዉ ትግል አብሮ የመጓዙ ሁኔታ አይሳካለትም ነበር፡፡ መበጣበጡ፣ ፓርቲውን ጥሎ ወጥቶ  ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋሙ ሁኔታ ፈታኝ ይሆንበት ነበር ፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ይህ ሁኔታ ገጥሞታልና፡፡ የጫካ ትግል ውስጥ በመበጣበጥ ከአባልነት መውጣትና ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ቀላል ተግባር አይደለም፡፡ አደጋው የከፋ ስለሚሆን፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ የግለሰቦች ጉዳይ ሳይሆን የአገር ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ ነገር ግን ትኩረት ስላልተሰጠው የተፈጠረ ስህተት ነው፡፡ ለመሆኑ እኛ ምን የተለየ ነገር ስላለን ነዉ 60 እና 70 አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚኖሩን? እውነት ለአገራችን ይህን ያህል አማራጮች ያስፈልጋታል? እነ አሜሪካ ሁለትና ሦስት አማራጮች ብቻ እንዲኖራቸው ያደረጉት የእኛን ያህል ግንዛቤና የዴሞክራሲ እውቀት  ስለሌላቸው ነው? እነዚህ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነን በማለት የተቋቋሙት  አብዛኛዎቹ በዓላማ ወይም በፕሮግራማቸው ይዘት የተለያዩ ሳይሆኑ፣ ከግል  ጥቅማቸውና ዝና ፍለጋ ጋር በተያያዘ ያቋቋሙዋቸው ናቸው ለዚህም ነው አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ከተቀሩት የፖለቲካ  ፓርቲዎች የሚለይበትን ተጨባጭ ነጥብ  ማቅረብ ቀርቶ  የፓርቲዎችንም ስም እንኳ ጠንቅቆ መግለጽ የማይችለው፡፡

 ስለዚህ አንቀጽ 31 ለይስሙላ  የተዘጋጀ  በመሆኑ  ምንም ነገር ማሳካት  አይችልም፡፡ ይልቁንም ያሳካው አንድ ትልቅ ነገር አለ፡፡ እሱም በዚህ አንቀጽ ምክንያት በአገሪቱ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ እየተቆጠረ ነገር ግን ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስም ብቻ ይዘን ገዢው ፓርቲ ያለ ተቀናቃኝ  ተደላድሎ  እንዲቀጥል ዕድል ፈጥሮለታል፡፡ ሕዝቡም  አማራጭ  የሚያገኝበት ዕድል በዚህ አንቀጽ ዝግ ሆኖበታል፡፡ ምክንያቱም ይኼ አንቀጽ ሽባ ያደረጋቻውና የውስጥ ትግል የማይታይባቸው እንዲሁ አሉ ሲባሉ የሚበተኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አምኖ አገሩን እንዲመሩ መስጠት አስቸጋሪ ስለሚሆንበት፣ እያዘነ ገዢው ፓርቲ አገርን የሚዘርፉ ኃላፊዎችና አባላቶቹን ይዞ እንዲቀጥል ከማድረግ የተሻለ አማራጭ አጥቷል፡፡

 ይህ ሁኔታ ውሎ አድሮ ጠቅሞናል የሚሉትንም ጨምሮ አገሪቱን ከማትወጣበት አደጋ ውስጥ ሊከታት እንደሚችል በቅርቡ ያየነው አዝማሚያ ሊያስተምረን ይገባል፡፡ በዚህ ላይ አንድ ግልጽ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህ አንቀጽ 31 በተሟላ ሁኔታ ተዘጋጅቶና  ገደቦች ተቀምጠውለት ቢሆን ኖሮ አገራችን እስካሁን ከመጣችበት አካሄድ እጅግ በተሻለ ሁኔታ በተራመደች ነበር፡፡ ምክንያቱም  ኢሕአዴግ ይህ ገደብ ቢኖር ኖሮ ተጠንቅቆና በርትቶ በመሥራት አሁን ከሚያስወቅሱት ጉልህ ጥፋቶች ፀድቶ በዓለም ላይ ስሙ ገናና የፖለቲካ ፓርቲ ይሆን እንደነበር አልጠራጠርም፡፡ ምክንያቱም እስካሁን ባለው ሁኔታ ምንም የሚፈራው ነገር በሌለበት የሠራቸው አርዓያነት ያላቸው ሥራዎቹን መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡

 3. ጠንካራ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ                                                                                                

ጠንካራ ወይም አንድነታቸውን የጠበቁ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች  እንፈልጋለን፡፡ ለምን አይኖሩም የሚለው በየመድረኩና በየቦታው የሚነሳው ተደጋጋሚ ፍላጎትና ጥያቄ የማን ነው? ከገዢው ፓርቲ በስተቀር የሰፊው ሕዝባችን፣ የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ አገሮች ተወካዮች፣ ወዘተ መሆኑ ሁላችን የምንስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ ለምን ጥያቄያችንና ፍላጎታችን ለረጅም ዘመናት  ሳይመለስና ሳይሟላ ቀረ? መልሱ አንቀጽ 31 የፈጠረብን ጣጣ ነው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን እስከ ዛሬ ድረስ በዚህ አንቀጽ ላይ ምንም ነገር አለማለታቸው  እንቆቅልሽ ነው፡፡ አንቀጹ ካልተሻሻለ በስተቀር ለህልውናችን እጅግ አደገኛ ነገር መሆኑን  ልንረዳ ይገባል፡፡ የውጫሌው ስምምነት አንቀጽ 17 እንኳ በውስጡ የደበቀውን አደገኛ ነገር አያቶቻችን በጋራ ተሠልፈው በመስዋዕትነት አስተካክለውታል፡፡ ይህ አንቀጽ 31 ግን ለችግሮቻችን በጋራ እንዳንቆም የሚያደርገን ውስጡ በመርዝና በእሳት የተሞላ ስለሆነ አሳዛኝ ነው፡፡

    ለረጅም ዘመናት ስናየው የነበረና አሁንም ያለ ለወደፊቱም አንቀጹ ካልተሻሻለ በስተቀር  የሚቀጥል  የአማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ፣

        -እገሌ የሚባል  የፖለቲካ ፓርቲ በዚህ አካባቢ ውጊያ ጀመረ፣

  – በውጭ አገር እነ እገሌ የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋቋሙ፣

  -አገር ውስጥ ይህን ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች  ተቋቋሙ፣ ተወሀዱ፣ ተለያዩ፣ ተካሰሱ፣ ፈረሱ፣….

   -መንግሥት እገሌ ከሚባል የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ተደራደረ፣

    እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚነዙትና በሚያደርጉት ድርጊት የአገሪቱ ሰላምና አንድነት አደጋ ላይ የሚወድቅበትን ሒደት በመስማትና ግራ በመጋባት  ከማሳለፍ የዘለለ፣ ይህች አገር በአንቀጽ 31 የተጠቀመችው ነገር የለም፡፡ ለወደፊቱም  አይኖርም፡፡ በተጨማሪም ምንም ያህል የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገብን ብንጓዝም፣ ይህ አንቀጽ በሚሰጣቸው ክፍተት የሚጠቀሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚፈጥሩት ጣጣ  የተገኘው ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዳልነበረ የሚደረግበትና ወደኋላ  የመመለሳችን  ሁኔታ  ክፍት ነው፡፡ 

  4.   የፖለቲካ  ፓርቲዎች እንዴትና በምን ሁኔታቢደራጁ ነው አገራችን ዘላቂ ዋስትና የሚኖራት?

አገራችን  በሰላም ጎዳና ዕድገቷን እያስቀጠለች ለመሄድ መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥልጣን የሚያዝበት ሁኔታ ከጥንስሱ እስከ ፍፃሜው ድረስ ያሉት ወይም መኖር የሚገባቸው ዝርዝር ሁኔታዎች ተመቻችተው በሕገ መንግሥቱ ላይ ባልተቀመጡበት  ሁኔታ  አገር  ሰላም ሆና ትቀጥላለች ማለት  ቀልድ ይሆናል፡፡

    የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲታሰቡ (ይህ አንቀጽ ከተሻሻለና በዚያ መሠረት የሚቀርቡትን  ለማለት ነው) ምትክ ወይም አቻ የማይገኝላቸው  የአገሪቱ የወደፊቱ ዕጣ ፋንታ ወሳኞች ወይም የህልውና መሠረቶች ወይም የዴሞክራሲ አቅጣጫ ቀያሾችና መሪዎችን ምናገኝባቸው ተቋማት መሆናቸውን፣ እያንዳንዱ ዜጋ አውቆ ከማንኛውም ተቋም በማስበለጥ እንደ ዓይኑ ብሌን  ሊጠብቃቸውና ሊንከባከባቸው ይገባል፡፡

     እስካሁን ካለው ሁኔታ የተገነዘብነው ነገር ቢኖር ግን አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ከእነርሱ ሥራና አስተሳሰብ በስተቀር እዚህ ምድር ላይ የተፈጠረ ሰው ሁሉ የሚሠራው ሥራም ሆነ አመለካከቱ ስህተት ነው ብለው የሚያስቡ፣ በአፈጣጠራቸው  ወይም በአስተሳሰባቸው ቀና አሳቢነት ጭራሹኑ ያልተፈጠረባቸው ሰዎች የሚሰባሰቡባቸው ነው፡፡ ታዲያ አንቀጹን በማሻሻል ለእነዚህ ዓይነቶቹ የማይመች አሠራር መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡ በሕዝባችን ተጠቃሚነትና በብዙኃን ሐሳብ የበላይነት ለሚያምኑ ሰፊ ዕድል መፈጠር አለበት፡፡

5.  በሕገ መንግሥቱ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሚመለከት ቀጥሎ ያሉት ጥብቅ  የሆኑ ነጥቦች  ጥናት ተደርጎባቸውና በሕዝቡ ውሳኔ  ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው አካሄድ መሠረት ሊካተቱ ይገባል                                                                                                                 

  • ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የገባች አገር ከመሆኗም በተጨማሪ የብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት  በመሆኑም  ሕገ መንግሥታችን ዜጎቻችን  በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ተዘዋውረው የመሥራት፣ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት እንዳላቸው  ደንግጓል፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ መንግሥቱን  አክብሮና አስከብሮ የአገሪቱን አንድነትና ሰላም  አስጠብቆ መምራት የሚችለው  ኅብረ ብሔራዊ አመለካከትና አደረጃጀት ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ መሆን ስለሚገባው በብሔር ስም፣ በአካባቢ ስም፣ ወይም ሌሎች  አምባገነናዊ  ስያሜዎችን  መሠረት በማድረግ  የፖለቲካ ፓርቲን  ማቋቋም  ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ፈፅሞ የማያስፈልጋት መሆኑን  ታሳቢ በማድረግ፣  ለአገራችን የሚያስፈልጉ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛትና ስያሜ  በሕገ መንግሥቱ ላይ  መሥፈር እንዳለበት፣
  • መንግሥት እንደ ሌሎቹ መንግሥታዊ ተቋማት በሕገ መንግሥቱ ላይ ለሠፈሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና መሥሪያ ቤታቸውንና በየክልሉ ቅርንጫፍ  ጽሕፈት ቤቶችን  ገንብቶ ወይም  በኪራይ  እንደሚያቀርብ፣
  • መንግሥት  በጀት እንደሚመድብ፣ 
  • የበጀት አጠቃቀማቸው በሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ቁጥጥር  እንደሚደረግበት፣   
  • በእነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አባል የሆነ ሰው በፓርቲው የውስጥ ደንብና መመርያ መሠረት ወይም በራሱ ፍላጎት ከፓርቲው ከተሰናበተ ዳግመኛ  በየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አባል የመሆን ዕድል የማይሰጠው ስለመሆኑ (ይህ ነጥብ የሚያስፈልግበት ዋናው ምክንያት ለአገሪቱ ጥቅም እታገላለሁ ያለ አካል  በሕገ መንግሥቱና  በፓርቲው የውስጥ አሠራር መሠረት በፓርቲው ውስጥ  ትግሎችን በማካሄድ ዓላማን ማሳካት  ይጠበቅበታል፡፡ ችግሮች ካጋጠሙም  በእነዚሁ አሠራሮችና  ሕጎች  መጠቀም አለበት፡፡ ከዚያ ያለፈ ነገር ከሆነና ከፓርቲው መሰናበት ግድ ከሆነ  ከአንዱ ወጥቶ  ሌላው ዘንድ በመሄድ  ተመሳሳይ  ችግሮችን  የመፍጠር  ዕድልን  ዝግ  ማድረግ  አስፈላጊ  ስለሚሆን ነው)፣ ይህም ሲጠቃለል  ባሉበት ጠንክሮ  መተጋገልና  ዓላማን  ከግብ ማድረስን ያጠናክራል፡፡ ካልተሳካ ደግሞ አርፎ  መቀመጥን  ግድ ማለት ስላለበት ነው፡፡
  • የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠሪነት  በግልጽ  ሊሠፍር  ይገባል፡፡                                                                
  • ገዢዉ ፓርቲም ይሁን ሌሎች አካላት በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ  ወይም በአባላቶቻቸዉ ላይ  ስለሚያደርሱት ጫና  የሕገ መንግሥቱ  ከለላ እንዳላቸው  በግልጽ ሊቀመጥ ይገባል፡፡                                                                   
  • በሕገ መንግሥቱ  ላይ ከተቀመጡ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጪ በአገሪቱ ውስጥ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም የማይፈቀድ መሆኑን፣ በውጭ አገር ለኢትዮጵያ ብለን የፖለቲካ ፓርቲ  አቋቁመናል  ወይም እናቋቁማለን  ከሚሉ  ጋር አባል መሆን ወይም መተባበር ወይም  ድጋፍ መስጠት  የማይቻል ስለመሆኑ፣                                                           
  • እነዚህ ሁሉ የሚያስፈልጉበት ዋናው ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲዎች  የአገር አለኝታነታቸው እየተዘነጋ እየተዋከቡ የግለሰብ ቤት  በመከራየትና በበጀት እጥረት ይህን አገራዊ ጉዳይ በአባላት መዋጮ ብቻ ይወጡ ማለት  ፈጽሞ ተገቢ  ስለማይሆን፣ በተረጋጋ  ሁኔታ ጽሕፈት ቤቶችና  በቂ  በጀት ኖሮአቸው ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች  በመቅጠር  በማንኛውም  የሥራ ዘርፍ ላይ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሥራ በማከናወን ለፖለቲካ አመራር ብቃት ያለው ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግና  ብቃት ያላቸውን የፖለቲካ መሪዎች ማግኘት እንዲያስችለን ነው፡፡ እስኪ አንድ ምሳሌ እንውሰድ፡፡ መንግሥት ለተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንድሁም ለዕምባ ጠባቂ፣ ለሰብዓዊ መብት፣ ለሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና፣ ወዘተ ከበጀት ጀምሮ  ማንኛውንም አስፈላጊ ነገሮችን እንደሚያሟላላቸው የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ዳሩ ግን እነዚህን መሥሪያ ቤቶች እንዲመሩ ዕድሉን ልንሰጣቸው፣ ምርጫ የሚጠባበቁ  የፖለቲካ  ፓርቲዎች  የተሟላ ቁመና ላይ እንዲደርሱ ከጅምሩ አንስተን አስፈላጊውን ነገር ሁሉ አሟልተንላቸው ተንከባክበን ብናሳድጋቸው አገራችን ትጎዳ ይሆን? አንድ ሙሰኛ በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር የአገር ሀብት በሚዘርፍበትና አገራችንን ወደ ቁልቁለት ለማስገባት ሰፊ ጎዳና የያዘበትን ሒደት እያየን ዝም እንድንል የሚፈልጉ የአዛኝ ቅቤ አንጓቾች እንዴት ተደርጎ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ይህ ሁሉ ነገር ይደረግላቸዋል  ማለታቸው የማይቀር ነው፡፡ በመሆኑም እነርሱኑ ተከትለን ይህ ሳይደረግ  ይቀርና በሚፈጠሩ ቀውሶች  የዜጎቻችን  ሕይወት ይጠፋል፣ ንብረት ይወድማል፣ አገር  ሰላም ታጣለች፡፡ ስለዚህ በአሠራርና በገንዘባችን የወደፊቱን ጉዞአችንን ማሳመር  እየቻልን ለአደጋ የሚያጋልጠንን  መንገድ መከተል ለምን አስፈለገን?                                                     
  1. ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱትን በመከተል ፈጸምን ማለት አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ማንኛውም መንግሥታዊ ተቋም በሕገ መንግሥቱ  የተረጋገጠ  ጽሕፈት ቤትና  በጀት  ስለሚኖራቸው፣ ገዢው የፖለቲካ ፓርቲ  ወይም የፖለቲካ ፓርቲው አባላት ወይም ማንም እንዳስፈለገው እየተነሳ የሚያዋክባቸውና የሚያፈርሳቸው አይሆኑም፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥታዊ ናቸውና፡፡ በውጤቱም  አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደምናገኝ አረጋገጥን ማለት ነው፡፡ ይህ ሲሆን የጫካ የፖለቲካ ትግል  እንዲያከትም፣ ለብጥብጥና ሁከት የምንጋለጥበት ሁኔታ እጅግ ውስን  እንዲሆን የሚያደርግና ሕዝቡ ካሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የትኛው ይሻላል ከማለት ውጪ  ኃላፊነት ለመስጠት የሚቸገርበት ሒደት ያበቃል ማለት ነው፡፡

     ይህን ነጥብ ለማጠቃለል ያህል ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች መሠረት  የሚደራጁ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገር ያላቸው ጠቀሜታ ከማንኛውም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ወይም  መንግሥታዊ  ተቋም ያልተናነሰ ወይም የሚበልጥ መሆኑን ልንጠራጠር  አይገባም፡፡   

ወደ ማጠቃለያ ከመሄዴ በፊት አንድ በጣም አስፈላጊ ነገር መጥቀስ ተገቢ  ነው ይኸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ አስቀድሞ መበላሸቱን የሚያውቀዉ ገዢው  የፖለቲካ ፓርቲ ማንም የፖለቲካ ፓርቲ  ጠንከሮ  በመገኘት ሊተካው  እንደማይችልና  የሚቆጣጠረውም አካል አለመኖሩን ስለሚያውቅ፣ የፈለገውን አሠራር በመከተሉ በቀላሉ ሊፈታው ከማይችልበት  ችግር  ውስጥ  ገብቷል፣ የሙስና ጉዳይ፡፡                                                                                                                                                   

      ለብዙ ነገሮች የዓለም ምርጥ ተሞክሮዎችን  እያመጣ ተግባራዊ  በማድረግ የሚታወቁው ኢሕአዴግ ለሙስናውም መፍትሔ ጠፍቶት አይደለም ዙሪያ ጥምጥሙን የሚዞረው፡፡ የቸገረው ነገር እንዳለ እንውቃለን፡፡ እሱም ሳይገምተው ቀስ በቀስ የራሱ አባላትና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሙስና ውስጥ በመዘፈቃቸውና የሙስናው ኔትወርክ እጅግ በመስፋቱ የተነሳ፣ ማን ማንን ተጠያቂ እንደሚያደርግ ግራ ስለገባው ነው፡፡ በሌላ ወገን ‹‹ደግሞ ሙስናን የሚጠየፍ ዜጋ እንፈጥራለን›› ተብሎ ሲገለጽ እንሰማለን፡፡ ይህ አባባል ግን የፌዞች ሁሉ ፌዝ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙሰኛው በዚህች አገር ውስጥ እንዴት የተንደላቀቀ ኑሮ እንደሚኖር፣ የሚያፈራቸው ሀብቶች (ትልልቅ ሕንፃዎች፣ ፋብሪካዎች፣ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች፣ በየወቅቱ  የሚቀያየሩ  ውድ ተሸከርካሪዎች፣ ወዘተ) በተለያዩ  የዓለም ውድና እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ከተሞች በመዝናናት አብዛኛውን ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ፣ ዘመዶቻቸውም በዚሁ ሁኔታ ተንደላቀው እየኖሩና ማንም የሚነካቸው ስለሌለ ሌላው ዜጋ እንደ እነርሱ ለመሆን መንገዱን በየት ባገኘሁት በሚልበት አገር ውስጥ፣ ሙስናን የሚጠየፍ  ዜጋን  እንፈጥራለን ማለት ሕዝቡን አላዋቂ ማድረግ ነው፡፡

   ለምሳሌ ሌብነት በሳዑዲ ዓረቢያና  በቻይና ሙስናን እንመልከት፡፡ መፀየፍ የሚኖረው እንደዚያ ዓይነቱ ዕርምጃ ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ ሁሉ ችግሮቻችን ጠንካራ አመራር የምናገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ መፍትሔ ካገኘ ብቻ ነው፡፡

ማጠቃለያ

 ለዚህች አገር የወደፊት ዕጣ ፋንታ የዜግነቴን ግዴታ ልወጣ የሚል ማንኛውም ዜጋ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ በግልም ይሁን  በተደራጀ መልኩ ይህ የሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 31 በሚሻሻልበት ሁኔታ ላይ ቁርጠኛ አቋም ይዞ ሊታገል ይገባል፡፡ አሁን ባለው አካሄድ መቀጠል ማለት ግን መንግሥታዊ የፖለቲካ  ሥልጣን ለመያዝ አፈር ድሜ ትበላለህ፣ አንተን በተራህ ከሥልጣን የሚያወርድህ  አካል አፈር ድሜ በልቶ ያወርድሃል፣ ከወረድክ በኋላም አፈር ድሜ  ትበላለህ፣ አገርም ቁም ስቅሏን ታያለች (እንደ አገር መቆየት ከቻለች)፡፡ ይህ የማይቆም ሒደት ይሆናል ማለት ነው፡፡

እናንተ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን የፖለቲካ መስመር  ለአንዴና  ለመጨረሻ  ጊዜ  የምታስተካክሉበት  ቁልፍ  አሁንስ  አይታያችሁም?

እስኪ እባካችሁን እስከ ዛሬ ድረስ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ትክክል ነው ብላችሁ የተጓዛችሁበትና ዘመናት ያስቆጠራችሁበትን የፖለቲካ መንገድ ባለበት ደረጃ አንዴ ቆም በማድረግ፣ መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥልጣን የሚያዝበት ቁልፍ በኢትዮጵያ  ሕዝብ እጅ እንዲገባ አንድ ሆናችሁ ታገሉ፡፡

      በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አድዋ ጦርነት፣ እንደ ህዳሴዉ ግድብ፣ እንደ ሻዕቢያ ጦርነት፣ ወዘተ መቶ በመቶ ከጎናችሁ ይሰለፋል፡፡

እሰኪ እነማን ተነሳሽነት ወስደው ይህን አገራዊ ጉዳይ መስመር እንደሚያስይዙት ይታያል፡፡ ይህ ሰነድ  በተቻለ መጠን ለሁሉም አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች  እንዲደርስ  ይደረጋል፡፡

ከዚያ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴትና በምን ሁኔታ መደራጀት እንዳለባቸው  በኢትዮጵያ  ሕዝብና በሕገ መንግሥቱ ላይ ይወሰናል፡፡ በዚህ  ነጥብ  ላይ የምትወስዱት ዕርምጃ እውነት ለአገራችሁ የምታስቡ መሆን አለመሆናችሁ የሚረጋገጥበት ነው እንደ ሌላው ጉዳይ ዙሪያ ጥምጥም ለመሄድ ዕድል የሚሰጥ  ባለመሆኑ፡፡

አመሰግናለሁ!  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]ማግኘት ይቻላል፡፡      

       

     

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...