የካቲት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚከበረውን 121ኛው የዓድዋ ክብረ በዓል ለመዘከር ልዩ ልዩ ዝግጀቶች እየተሰናዱ ነው፡፡ መሰናዶው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው አገሮችም እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የዓድዋ ድልን ለመዘከር የተለያዩ የታሪክና የኪነ ጥበብ ማኅበራት እንዲሁም ሌሎችም ግለሰቦች መርሐ ግብሮች ማሰናዳታቸው እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተጀመረውና ፈቃደኛ ግለሰቦች ከአዲስ አበባ ዓድዋ ከተማ ድረስ የሚያደርጉት የእግር ጉዞ ተጠቃሽ ነው፡፡
የማስታወቂያና የኪነ ጥበብ ተቋማት ያላቸው ባለሙያዎች ስለ በዓሉ ታሪካዊ ዳራ በሚገልጹ ጥናታዊ ጽሑፎችና በዓሉን የሚያንፀባርቁ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ገድሉን ዘክረው ይውላሉ፡፡ ሽለላ፣ ፉከራና ቀረርቶ የታከለባቸው ቴአትሮች፣ አርበኞችን የሚያወድሱ ግጥሞች፣ የአርበኞችን ተጋድሎ የሚያሳዩ ሥዕሎችና ድሉን የሚያወድሱ ሙዚቃዎችም ሲዘጋጁ ይስተዋላል፡፡
በታዲያስ ዘገባ መሠረት፣ የዓድዋ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአሜሪካ የተሰናዳው ዝግጅት በዚህ ሳምንት ማገባደጃ ይካሄዳል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ለበዓሉ ከተዘጋጁ መሰናዶዎች መካከልም ይጠቀሳል፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የሽልማት መርሐ ግብር ሲሆን፣ ‹‹አርሚ ኤንድ ኔቪ›› በተሰኘው ክለብ የሚካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ ልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ ይመራል፡፡
ታዲያስ እንደዘገበው፣ መርሐ ግብሩ የዓድዋን ድል አስታኮ ኢትዮጵያውያንን የሚጠቅም ሥራ ያከናወኑ ሰዎች ሽልማት የሚያገኙበት ቀን ነው፡፡ ‹‹ዝግጀቱ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ድል የሚከበርበት እንዲሁም በትጋት ሠርተው ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ነገር ያበረከቱ ሰዎች የክብር ሜዳልያ የሚያገኙበት ነው፤›› በማለት ተገልጿል፡፡
‹‹ግራንድ ኦፊሰር ኦፍ ዘ ኢምፔሪያል ኦርደር ኦፍ ኢምፕረር ምኒልክ ዘ ሰከንድ›› የሚል መጠሪያ ያለው የተከበረ ሽልማት በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን እንደተጀመረ ዘገባው አስታውሶ፣ በዚህ ዓመት ሽልማቱ በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ለሚገኘው ፀሐይ ፐብሊሸርስ መሥራችና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ወንደሙ እንደሚሰጥ አመልክቷል፡፡
በልዑል ኤርሚያስ ገለጻ፣ አቶ ኤልያስ ሽልማቱ የሚበረከትላቸው የኢትዮጵያንና አፍሪካን ማንነት ለመጠበቅ ባገዘው አበርክቷቸው ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ማንነት ለመጠበቅና ከአፍሪካ አህጉር ውጭ ስለ ኢትዮጵያና አፍሪካ ያለውን አመለካከት ለማሳደግ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማቱ ይሰጣቸዋል፤›› በሚል ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኮሎራዶ የቢዝነስ ሰው መል ተዋሕደ እና ሌሎችም ‹‹ግራንድ ኦፊሰር ኦፍ ዘ ኦርደር ኦፍ ዘ ስታር ኦፍ ኦነር›› በሚል ሽልማት ይበረከትላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት (የክራውን ካንውስል ኦፍ ኢትዮጵያ) ኃላፊም በሆኑት ልዑል ኤርሚያስ የሚመራው ዝግጅት፣ በተለያየ የሙያ መስክ ኢትዮጵያውያንን ያገለገሉ ሰዎችን ዕውቅና በመስጠትና የዓድዋ ድልን በመዘከር ይከበራል፡፡ መርሐ ግብሩ መካሄድ የጀመረው ከአምስት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ ዘንድሮ ስድስተኛው ዙር እንደሚከናወን ታዲያስ በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡