Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘንድሮ የአዳዲስ የባቡር መስመሮች ዝርጋታ አይኖርም

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ከአዋሽ-ወልዲያ-መቀሌ የባቡር መስመር ዝርጋታ እያካሄደች ቢሆንም፣ ዘንድሮ አዳዲስ የባቡር መስመሮች ዝርጋታ እንደማይጀመር ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አገሪቱ ሁለት የባቡር መስመር ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ቢሆንም ዘንድሮ የሚጀመር ፕሮጀክት የለም፡፡ ከመቼ ጀምሮ የአዳዲስ የባቡር መስመሮች ዝርጋታ እንደሚጀመር አይታወቅም ብለዋል፡፡

የአዋሽ-ወልዲያ (ሃራ ገበያ) የባቡር መስመር ፕሮጀክት በጥቅምት 2007 ዓ.ም.  እንደተጀመረ፣ ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ ያለው የባቡር መስመር ዝርጋታ 60 በመቶ መድረሱን አቶ ደረጀ ተናግረዋል፡፡ 398 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአዋሽ ወልዲያ የባቡር ፕሮጀክት 1.7 ቢሊዮን ዶላር በጀት ተይዞለት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የአዋሽ-ወልዲያ (ሃራ ገበያ) የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት አካል የሆነው ከኮምቦልቻ እስከ ወልዲያ የሚከናወነው የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክትም፣ የመሬት ማስለቀቅ ሥራው በቅርብ ቀን እንደሚጀምር አስረድተዋል፡፡

ከወልዲያ እስከ ኮምቦልቻ ያለው የባቡር መስመር 120 ኪሎ ሜትሮችን ብቻ የሚያካትት እንደሆነ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚታሰብም ገልጸዋል፡፡

በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ የተጣለለት ሌላው ፕሮጀክት የመቀሌ-ወልዲያ የባቡር መስመር ዝርጋታ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ አጠቃላይ አፈጻጸሙ 48 በመቶ እንደደረሰ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ 216 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን እንደሆነና 1.54 ቢሊዮን ዶላር እንደተመደበለት ገልጸዋል፡፡ በመሬቱ ወጣ ገባነት የተነሳ በፕሮጀክቱ ላይ ችግር እየተፈጠረ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ የተማረ የሰው ኃይል ውስንነት፣ የመሬቱ ወጣ ገባነትና የመሬት ባለቤት አርሶ አደሮች ካሳ ጉዳይ ለፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያቶች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የመቀሌ-ወልዲያና የአዋሽ-ወልዲያ የባቡር መስመር ፕሮጀክቶችን ለማከናወን አገሪቱ ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ ከአበዳሪዎች እንዳገኘች መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከቻይና የተበደረችውን ብር በጊዜው መመለስ ባለመቻሏም፣ በባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቶች ላይ መስተጓጎል እየተፈጠረ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አቶ ደረጀም ‹‹የገንዘብ እጥረት ትልቁ የፕሮጀክቶች ፈተና ነው፤›› ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባቡር መስመር ፕሮጀክቶች በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፐ አማካይነት በራሳቸው ወጪ ወይም ከመንግሥት ጋር በጥምረት እንዲከናወኑ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

በአዲሱ በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ አማካይነት ይከናወናሉ ተብሎ በዕቅድ ከተያዙት የባቡር መስመሮች መካከልም የሞጆ-ሞያሌ የባቡር መስመር ይገኝበታል፡፡

አቶ ደረጀ ወደፊት ይሠራሉ ተብለው የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠላቸው አዳዲስ የባቡር መስመሮች መካከል ከአምቦ-ጂማ-በደሌ፣ ከሞጆ-ሻሸመኔ-ሐዋሳና ከወልዲያ-ወረታ-ባህር ዳር-ሱዳን እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡ የእነዚህ የባቡር መስመሮች ፕሮጀክቶች የመስመር ዝርጋታ መቼ እንደሚጀመር ግልጽ ያለ ጊዜ አለመቀመጡንም ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች